ከ30 ዓመታት በኋላ ‘ሸብተው’ የተገናኙት የ‘ዓለማያ’ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Haramaya University
ጊዜ ክንፍ አውጥቷል።
ካላመናችሁ የ’ብላቴ’ ተመራቂዎችን ጠይቋቸው።
የዛሬ ምናምን ዓመት ጎረምሶች ነበሩ። ነሐሴ 30፣ ሺ ዘጠኝ መቶ 84 ተመረቁ፤ እየሳቁ።
ከ30 ዓመት በኋላ ነሐሴ 30፣ 2014 እዚያው ቢገናኙ ጊዜ ሆድ ባሳቸው።
የዓለማያ ትዝታ ናጣቸው። የጊዜ ጉልበት አስደመማቸው።
አንዳንዶቹ ተረሳስተዋል፤ የዶርም ደባሎቻቸውን ስም ሁሉ ዘንግተዋል።
ሲሶዎቹ ሸባብተዋል፣ ሲሶዎቹ ተመልጠዋል፤ ሲሶዎቹ ቦርጭ አውጥተዋል።
ደግነቱ አብዛኛዎቹ ዶክተር ሆነዋል። አንዳንዶቹ ዩኒቨርስቲዎች ፕሬዝዳንቶች ናቸው። አንዳንዶቹ በውጭ አገር ፕሮፌሰር ናቸው።
አንዳንዶቹ ከአገር ቤት ወደ ውጭ አበባ ላኪ ናቸው። ሌሎች ደግሞ የእጽዋት ተመራማሪዎች።
አንዳንዶቹ በተባበሩት መንግሥታት አለቆች ናቸው።
ኧረ አምባሳደር የሆነም አለ።
ለምሳሌ የቀድሞው የግብርና ሚኒስትር፣ የአሁኑ የጃፓን አምባሳደር ተፈራ ደርበው የዚህ የ’ብላቴ ባች’ ተመራቂ ናቸው።
በቀደም ግን ሌሎች ሲገኙ እሳቸው አልተገኙም። መልዕክት ግን ከጃፓን-ባቲ ልከዋል።
ሩቅ ምሥራቅ ከዓለማያ ስንት ሺህ ማይልስ ይሆን?
በልጅ ሠርግ መሀል የተያዘ ቀጠሮ
የትውልድ ጅረት ቀጥሏል።
የጊዜው መክነፍ በኬጂና በኮሌጅ መሀል ያለን የጊዜ ስፋት ያጠባል።
ብቻ ይህ የ30 ዓመት ቀጠሮ የተያዘው እንደ ዋዛ ነበር።
ዶ/ር አዱኛ የሚባሉ ሰው ልጃቸውን ይድራሉ።
እሳቸውም የ’ብላቴ ባች’ ናቸው።
ለሠርግ ከጠሯቸው ታዳሚዎች አንዳንዶቹ ታዲያ የድሮ የኮሌጅ ወዳጆቻቸው ነበሩ።
‘ለምን ግን አንገናኝም?’
መቼ?
‘ነሐሴ 30’
የት?
‘እዚያው ነዋ፣ ሐረማያ’
‘ሸጋ ነው!’ (ሸጋ ነው ማለት ወደ አሁን ትውልድ ሲተረጎም ‘cool!’ እንደማለት ነው)
ቀጠሮው ሰመረ።

የፎቶው ባለመብት, Haramaya University
‘500 ሆነን ገብተን፣ 250 ሆነን ተመረቅን’
ጃንሆይ ዓለማያ ኮሌጅን በ’ቸርነታቸው’ ሲከፍቱ ለአፍሪካ ይተርፋል ያሉት ግብርና ኮሌጅ ነበር።
የጠቅላላ ተማሪዎች ቁጥር ደግሞ 11 ብቻ ነበር።
ይህ በ1950ዎቹ መባቻ መሆኑ ነው።
ያን ጊዜ መምህሩም አስተዳደሩም ከአሜሪካው ኦክላሆማ ዩኒቨርስቲ ነበር የሚመጣው።
በዚያ ዘመን በአገሩ የኔታ እንጂ ፕሮፌሰር የለማ።
ጃንሆይ በትውልድ አገራቸው ለከፈቱት ዓለማያ ኮሌጅ ስስ ልብ ነበራቸው ይባላል።
ያን ዘመን ወተት በቧንቧ ለተማሪዎች ይቀርብ ነበር እየተባለም ይታማል።
ይሄ አፈ-ታሪክ (myth) ዛሬም ድረስ ይወራል። ጃንሆይ አያደርጉትም አይባልም።
እና በዚያ ዘመን ተማሪ መሆን በራሱ ብርቅ ነው። ኮሌጅ መግባት ተዓምር ነው።
ለዚህ ጽሑፍ መሳለጥ ስንል ‘የብላቴ ባች’ ብለን የምንጠራቸው እነ ዶክተር ተፈራ ደርበው ራሱ ዩኒቨርስቲ ሲገቡ ቁጥራቸው 500 ነበር።
በዚህ ቁጥር የተረሳ ዜሮ የለም።
አሁን በሐረማያ ዩኒቨርስቲ 30ሺህ ተማሪ ይርመሰመሳል፤ በሩቅም በቅርብም።
በእነ ተፈራ ደርበው ጊዜ የትምህርት ክፍል (Department) 5 ብቻ ነበር። አሁን 230 አልደረሰም ብላችሁ ነው?
ደግሞ ያኔ እነ አምባሳደር ተፈራ 500 ሆነው ገቡ እንጂ 500 ሆነው አልወጡም።
ያን ጊዜ መመረቅ መቼ የዋዛ ሆነና።
በዚያ ዘመን በኮሌጅ በር ማለፍ ራሱ ‘ግመል በመርፌ ቀዳዳ’ አለፈች የሚባልበት ጊዜ ነበር።
እና በዚያ ዘመን ከ500ዎቹ፣ 250ዎቹ ብቻ ተመረቁ።
ክፋቱ፣ ልክ ሊመረቁ ሲሉ ጓድ መንግሥቱ አሰናከሏቸው።
“...ንቀውናል፤ ደፍረውናል፤ ብታምኑም ባታምኑም በቁም ሞተናል። ...ትዘምታላችሁ ወይንስ…”ብለው ብላቴ ላኳቸው።
ጓድ መንግሥቱ ይህን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተናግረው፣ እርሳቸው በኬንያ ሹልክ ብለው ዚምባብዌ ገቡ።
ብላቴዎች አንዳንዶቹ ዲግሪውን ሳይቀበሉ በሞያሌ ኬንያ ገቡ። ምረቃው ተስተጓጎለ።
ከሞትና ከኬንያ የተሩፉት እንደ ምንም በነሐሴ 1984 ተመረቁ።
ለዚያም ነው፣ እኒህ ተማሪዎች ዘመነ-ትውልዳቸውን የ’ብላቴ ባች’ ብለው የሚጠሩት።
ማንቼ-አርሴ ባልነበረበት ዘመን ትምህርት
ዶ/ር አስናቀ ፍቅሬ አሁን የእጽዋት ሳይንስ ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው።
ወግና ጨዋታ እንደ እግር ኳስ አሰላለፍ ቢኖረው ‘የብላቴ ባች’ የፊት መስመር አጥቂ መሆን የሚችሉ ናቸው።
የዘመን ማለፍ አላኮሳተራቸውም። ተጫዋችነታቸው ዛሬም አለ።
‘ድሮ ያለ ፕሪምየር ሊግ ኮሌጅ እንዴት ተገፋላችሁ? ትምህርቱስ እንዴት ዘለቃችሁ?’ አልናቸው።
‘የኛ ብቸኛ መዝናኛ ቅዳሜ ማታ 4፡00 ሰዓት ነበር። ኅብረ-ትርዒት።‘ አሉን።
ሌላስ?
“ሌላ በቃ የሕንድ ፊልም በሳምንት ዐርብ እናያለን። ከእራት በኋላ ልክ 11፡30 ላይ ይጀምራል። ‘ማዘር ኢንዲያ' የሚባል ፊልም ደጋግመን እናይ ነበር።“
‘ወተት በቧንቧ ይቀርብላችሁ ነበር የሚባለው እውነት ነው?’
“እሱ ነገር በኛ ጊዜም ይወራ ነበር። ምናልባት ከኛ በፊት የነበሩት ቀርቦላቸው ይሆናል፟።
‘ለእናንተስ?’
“ለእኛ በቧንቧ ባይሆንም በኩባያ የፈላ ወተት ይሰጠን ነበር። በሳምንት ሦስት ቀን”

የፎቶው ባለመብት, የምሥራቅ ሐረርጌ አካባቢ ጥበቃ
‘እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለማያ ሐይቅም ተመልጧል’
እናላችሁ እነዚህ የድሮ ተማሪዎች ከ30 ዓመት በኋላ ተገናኙ አልናችሁ።
ድሮ ደቃቅ ነበሩ፤ አሁን ገዝፈዋል። ድሮ አፍሮዎች ነበሩ። አሁን ተመልጠዋል።
እነርሱ ብቻ አልነበረም የተመለጡት።
የሚወዱት ሐይቅም ተመልጦ ነበር የጠበቃቸው።
ከ’በግ ተራ’ ቆንጃጅት አፈስ አድርገው የሚዝናኑበት ሐይቅ ዛሬ የለም። የለም ባይባልም እንኳ አለ አይባልም።
እንደ አንዳንዶቹ ተማሪዎች ጨርሶውኑ ባይመለጥም ከአናቱ ‘ገባ ብሏል’።
ሄድ መጣ ይላል።
“አሁን እንዲያውም ጥሩ ነው ያለው። ከ18 ሚሊዮን ሜትሪክ ኪዩቢክ ውሃ 40 ከመቶው ተመልሷል” ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ።
ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ ደግሞ ማን ናቸው?
እሳቸውም፣ ‘የብላቴ ባች’ ናቸው። ሲመረቁ ግን እዚያው ቀሩ።
የ30 ዓመት ርዝማኔን በእርሳቸው መለካት ይቻል ከሆነ እንሞክረው።
የተማሩበት ዓለማያ ራሱ ስሙን በዘመን ርዝማኔ ሐረማያ ብሎታል።
በሦስት ዐሥርታት ከጀማሪ ረዳት ምሩቅነት ወደ ተባባሪ ፕሮፌሰርነት ደርሰዋል።
በተማሩበት ኮሌጅ ዛሬ የዩኒቨርስቲው የምርምር ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት ሆነዋል።
ወልደው ከብደዋል።
እንኳንስ እርሳቸው፣ ሴት ልጃቸውም የዩኒቨርስቲ መምህርት ሆናለች። አሁን ለከፍተኛ ትምህርት ኔዘርላንድስ ሄዳለች።
ከዚህ በላይ የ30 ዓመት ርዝማኔ እንዴት ይገለጻል?
ሐይቁ ብቻ ሳይሆን ሰውም ጠፍቷል
ሐይቁስ መለስ ቀለስ ይላል። ሰው ነው ከሄደ የማይመለስ።
ዓለማያ ሐይቅ ደርቆ ሜዳ ሆኖ ነበር።
የሚገርመው ግን እንዲያ እንደሚሆን ገና ድሮ መተንበዩ ነው።
ትንቢት ስንላችሁ ሳይንሳዊ።
‘…በ15 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሐይቁ ሊጠፋ እንደሚችል ተተንብዮ እንደነበር አስታውሳለሁ’ ይላሉ ሌላኛው የዚሁ ባች አባል ዶ/ር አስናቀ።
በዚያ ዘመን ተማሪዎች በተለይ በግብርና ሳይንስ ዘርፍ ጥይት ነበሩ።
ስለዚህ ይህ እንደሚመጣ መተንበያቸው የሚደንቅ አይሆንም።
በነገራችሁ ላይ ይህ ሐይቅ ለብዙ ተማሪዎች ልዩ ትዝታ ያለው ነው።
እንኳን ለተማሪዎቹ ይቅርና የኮሌጁ መሥራች አባት ጃንሆይም የማይረሳ ትዝታ አላቸው።
በአንድ ወቅት በዚህ ሐይቅ እየዋኙ ሰምጠው ከመሞት ያመለጡበት አጋጣሚ አይዘነጋም።
ከዚያ መጥፎ አጋጣሚ በኋላ ንጉሡ ረግመውት ይሆን እንዴ የደረቀው (ትንሽ ፈገግታ)?
ይህ በአንዲህ ሳለ፣ ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ሐይቁን ለመመለስ የሚደነቅ ሥራ ሠርቷል።
ሐይቁም ቀስ በቀስ እየተመለሰ ይመስላል።
እውነት ነው፤ ሐይቅ ይመለሳል፤ ጸጉርም ይተከላል። ከሄደ የማይመለሰውስ ሰው ነው።
ለምሳሌ ብላቴዎች 500 ሆነው ዓለማያ ገቡ፣ 250 ሆነው ተመረቁ፤ መቶ ምናምን ሆነው ከ30 ዓመት በኋላ ተገናኙ።
በዚህ ጊዜ ታዲያ 17 ሞተዋል።
“ስንገናኝ፣ በሕይወት ስለቆየን ፈጣሪን አመስግነናል፤ በሞት ለተለዩንም የ1 ደቂቃ የሕሊና ጸሎት አድርገናል።‘’ ይላሉ ዶ/ር አስናቀ።

የፎቶው ባለመብት, HU FM
‘ያን ጊዜ ሴት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ብርቅ ነች’
እነዚህ የድሮ ተማሪዎች ሲገናኙ ሌላ ምን አደረጉ?
ለግቢው ማኅበረሰብ ግብር አበሉ፤ እነሱም የበግ ሥጋ በሉ።
በግ ስንል ምን ትዝ አለን? ‘በግ ተራ’
ድሮም ለካ የተማሪ የፍቅር ጉሊት ነበር፤ ስሙም ‘በግ ተራ’።
ለያኔው ዓለማያ ተማሪዎች ‘ባቴና ገንደቦይ’ የሚባሉ የድንበር ሰፈሮች ነበሯቸው።
አሁን መልካቸው ተቀይሯል።
እንደዛሬ ሕንጻ እንደ ሳር መብቀል ከመጀመሩ በፊት ዩኒቨርስቲው በፈረስ ተኩል ሰዓት ያስኬድ ነበር።
የተማሪ ማደርያዎች ሦስት ነበሩ። ለዚያውም ድንክ ምድር ቤቶች።
በወዲያኛው ማዶ ደግሞ የሴቶች አንድ ማደርያ አለ።
“እንደ ዛሬው አይምሰልህ ታዲያ፤ ያን ጊዜ ሴት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ብርቅ ነበረች’ ይላሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ።
ስለዚህ በግ ተራ ብድግ ተብሎ አይኬድም። ወግና ሥርዓት አለው።
‘በግ ተራ የምንቆመው በወረፋ ነው። የማስጠራት ወረፋው የሚደርሰን ታዲያ በስንት ጊዜ አንዴ ነው።'
ለዚያ ይሆን ብዙዎቹ ተማሪዎች የትዳር አጋር ከዚያ ኮሌጁ ያላገኙት?
ሁሉም ግን ባዶ እጃቸውን አልሄዱም።
በተገናኙ ዕለት ለምሳሌ አንድ ሁለቱ ዶክተሮች እንዲህ ሲሉ ተሰምተዋል።
‘ዓለማያ ዕውቀት ብቻም ሳይሆን ሚስትም ሰጥቶናል።'

የፎቶው ባለመብት, Haramaya University
የሴቶች ዶርምን 'በቁጥጥር ሥር' የዋሉት ሰውዬ
እነ ዶ/ር አስናቀና የብላቴ ጓዶቻቸው ከ30 ዓመት በኋላ ሲገናኙ የደንቡን አድርሰዋል።
ለምሳሌ ፎቶ ተነስተዋል። ችግኝ ተክለዋል።
የጥንት የጠዋቱን ታሪክ እያነሱ ተሳስቀዋል። ለምሳሌ ስለ ብላቴ ዘመቻ አውግተዋል።
ከሳቁባቸው ታሪኮች መሀል አንዱን እነሆ።
ያኔ ፌስቡክ አልነበረም።
ፍቅር ምን ይመስል ነበር ከተባለ ‘ሰመመን’ መጽሐፍን ነበር የሚመስለው።
ያፈቀረ የመልካሙ ተበጀን ዜማ ያንጎራጉራል።
የጠናበት ወደ ሴቶች ዶርም ደብዳቤ ይልካል።
በቀለ የሚባል ቀልጣፋና ተግባቢ ጓደኛ ነበራቸው።
ለአንድ ፍቅር ለጠናበት ወዳጁ የፍቅር ደብዳቤ ይዞ በታላቅ ጀብዱ ሴቶች ዶርም ገባ።
ተቆጣጣሪዎች ደረሱበት።
አንድ ወንድ ተማሪ ሴቶች ዶርም ተገኘ ማለት ፍርዱ የማያዳግም ነው። በቃ ይባረራል። ምሕረት ብሎ ነገር የለም።
በቀለ ላይ ታላቅ አደጋ ተጋረጠ።
በወቅቱ የነበሩት ሴት ተማሪዎች መልካምም፣ መልከ-መልካም ነበሩ።
በቀለ ተማሪ ሳይሆን ‘ጀብሎ’ ነው ብለው ድርቅ አሉለት።
ጀብሎ በዚያ ዘመን ለሴቶች አንዳንድ ዕቃዎችን የሚላላክ ልጅ ማለት ነው።
ሴቶች ዋሽተውላቸው ተረፉ።
እነሆ የያኔው ወጣት በቀለ ከመባረር ተርፈው ከ30 ዓመት በኋላ ትልቅ ሰው ሆነው ዳግም ቦታው ተገኝተው ዳግም ለመሳቅ በቁ።
‘ከ30 ዓመት በፊት ወጥ የጨለፉልን ‘ማዘር’
እነዚህ የብላቴ ባቾች ከብዙ ትዝታ ጋር ሁለት ቀን በግቢው ተመላለሱ።
Love street (የፍቅር ጎዳና) በሚሉት ጎዳና ተንሸራሸሩ።ይህ የፍቅር ጎዳና ከድሮው ቤተ መጻሕፍት ፊት ለፊት ይገኛል።
ከ30 ዓመት በፊት ያንቀላፉባቸውን ማደርያዎቻቸውን ደባበሱ።
በአካባቢው ትዝታ ከተናጡ በኋላ ወደፊት ላለመለያየት ቃል ገቡ።
ከመለያየታቸው በፊት ግን የሽኝት እራት አሰናዱ።
በዚህ መሀል አንድ የተቀደሰ ሐሳብ ብላጭ አለላቸው።
ድሮ ‘ዜር ፎር’ ይጨልፉላቸው የነበሩትን ማዘርን ፍለጋ ወጡ።
ማዘር አርጅተው ጡረታ ወጥተው በአካባቢው አገኟቸው። እማማ ቀለሟ ይባላሉ።
የክብር እንግዳ ተደረጉ።
ድሮ ወጥ ጨልፈው ያስተናገዷቸውን ‘ማዘርን’ አሁን ደግሞ እነ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ፣ እነ ዶ/ር አስናቀ በተራቸው ወጥ ጨልፈው አስተናገዷቸው።
እማማ ስሜታቸው ተነካ። ‘ይህ ለኔ ዳግም የመፈጠር ያህል ነው አሉ።‘
ዶ/ር አስናቀ ወጥ የሚጨልፉት ማዘርንም ሲያስታውሱ በበጎ ነው።
‘ሲጨልፉ ቀና ብለው እንኳ አያዩንም ነበር። ትኩረታቸው ድስቱና ጭልፋው ላይ ነበር። የሳህኑን ባላንስ ነው የሚያዩት። ቀና ብለው ካዩን እንዳያዳሉ ብለው እኮ ነው።
ሌላም ምስክርነት ተሰጠ፤ ‘በተለይ ‘ዜርፎር’ ሲጨልፉ ፍትሐዊ ነበሩ። ‘’አሉ፤ ሌላ ዶክተር።
’ዜር-ፎር’ የሦስት ሙዳ ሥጋዎች 'ሜታፊዚክሳዊ' አቀማመጥን ተከትሎ የወጣ ስያሜ መሆኑን ልብ ይሏል።

የፎቶው ባለመብት, HU FM
የጉሮሮ ትራፊክ
ይህ ብቻም አይደለም።
ድሮም ‘ቲከር’ የሚባል የጉሮሮ ትራፊክ ነበር።
‘ቲከር’ ማለት መዝገብ ይዞ ምግብ አዳራሽ የሚቆም ተቆጣጣሪ ነው።
በተማሪዎች የምግብ ካርድ ላይ ምልክት ያኖራል።
ተማሪው ገብቶ ሲበላ ካርዱ ላይ ‘ቲክ’ ያደርጋል።
በአጭሩ የጉርሻ ፖሊስ ልትሉት ትችላላችሁ።
አንድ ተማሪ አጭበርብሮ ምግብ ለመድገም ሲመጣ ማንቁርቱን ይዞ ያስወጣዋል።
እነ ዶ/ር አስናቀ በዚያ ዘመን በዚህም በዚያም ብለው ደግመው ካፌ ለመብላት ይሞክሩ እንደነበር ከ30 ዓመት በኋላም ቢሆን አምነዋል።
“በምላጭ ምልክቷን እየፋቅኩ ‘ድጌ’ በመብላት የተሳካ ሙከራ ማድረጌን አልክድም” ይላሉ ዶ/ር አስናቀ በረዥም ሳቅ ታጅበው።
ይሄ ‘ቲከር’ የተባለ ትራፊክ ግን በቀላሉ የሚታለል አልነበረም።
ስሙ አማረ ጌታቸው ይባላል። የብላቴ ባቾች ፈልገው አገኙት።
‘ቲከር አማረ’-‘ጋሽ አማረ’ ሆነዋል። ከእማማ ቀለሟ ጋር የክብር እንግዳ ተደረጉ።
ያን ዕለት እራት ሲበሉ ታዲያ ያን ውብ ትዝታ ለማስታወስ ጋሽ አማረ በድጋሚ ‘ቲክ’ እያደረጉ አስገቧቸው።
ከ30 ዓመት በኋላ ሌላ ሳቅ ተፈጠረ።
ከ30 ዓመት በኋላም ጋሽ አማረን አታለው ገብተው የበሉ ዶክተር/ፕሮፌሰሮች የሉም ለማለት ይቸግራል። ብላቴ ባች ብዙም የሚታመን አይደለም።
ብቻ አባባ አማረ ስጦታ ተሰጣቸው። ፍጹም ስሜታቸው ተነካ።
‘ልጆቼ ከ30 ዓመት በኋላ ስላስታወሳችሁኝ አመሰግናለሁ’ አሉ።

የፎቶው ባለመብት, Haramaya University
በመጨረሻ ምን ተባባሉ?
በነገራችሁ ላይ የቀድሞው ዓለማያ የአሁኑ ሐረማያ በዕድሜ ሽማግሌው ዩኒቨርስቲ ነው።
የቀዳማዋ ኃይለሥላሴ ኮሌጅ ብቻ ነው የሚቀድመው።
ከዚህ አንጻር ‘የብላቴ ባች’፣ የጥንት የሚባል 'ባች' አይደለም።
አቶ ፍሬዘር የአልሙናይ ቢሮ ኃላፊ ናቸው።
ዩኒቨርስቲው በድምሩ 117ሺህ ተመራቂዎችን አስመርቋል ይላሉ።
‘የቻይና ባችና የወይራ ባች የሚባሉ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ተጠራርተው መገናኘታቸውንም ያስታውሳሉ።
ምናልባት የብላቴ ባችን ልዩ የሚያደርገው በዲፓርትመንት ሳይሆን በሙሉ አንድ ባች መገናኘቱ ነው።
እናም እነ ዶ/ር አስናቀን፣ እነ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬን 30 ዓመት ረዥም ነው አጭር ብለን ጠየቅን። ደግሞስ ምን ተባባላችሁ ስትለያዩ አልናቸው።
ለካንስ ዘመንን ገምግመው ነው የተለያዩት።ለካንስ ዘመንን ገርምመው ነው የተለያዩት። የኃሊት።
ዘመኑ ተለወጠ እንጂ ብዙ ነገር ባለበት ነው።
ለምሳሌ ያን ዘመን ሲመረቁ ጦርነት ነበር።
የአሁኑ ተባባሪ ፕሮፌሰር ተስፋዬ እንዲያውም ያኔ ወጣት ላይብረሪ እያጠኑ ነበር። የተኩስ እሩምታ ተከፍቶ መስታወቱ ዱቄት ሲሆን ያስታውሳሉ።
ያኔም ጦርነት ነበር፤ አሁንም ጦርነት አለ።
ሌላስ?
'ተማሪ ሳለን ረሀብ ነበር፤ አሁንም ረሀብ አለ። ግን ለምን?' ብለው ተወያዩ።
ዶ/ር አስናቀ በተለይ እንዲህ አሉ፤
‘በ20 ዓመት ኮሪያዎች በግብርና ከተረጂነት ወደ ረጂነት ተሸጋግረዋል። እኛ ይህ ለምን አቃተን ብለን ቆዘምን'
አእናም ከ30 ዓመት በኋላ የትዝታ ሻንጣቸውን ሸክፈው ተለያዩ።
'ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ይዘን ነው የተለያየነው'
አነ ዶ/ር በድጋሚ ሊገናኙ ተማምለዋል።ምናልባት ከ30 ዓመት በኋላ፣ ምናልባትም ቀደም ብለው።
የዛሬ 30 ዓመት መልሰው ሲገናኙ ረሀቡና ጦርነቱ 'የድሮ ታሪክ' ይኾን ይሆን?












