ደራርቱ ቱሉ፡ ከ30 ዓመት በፊት ለአፍሪካ ሴቶች የተተከለ የድል ችቦ

ደራርቱ ቱሉ

ደራርቱ ቱሉ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ነግሳ ከቆየች ድፍን 30 ዓመታት ተቆጠሩ። ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ገብታ መኖር የጀመረችው የባርሴሎና ኦሊምፒክን ተከትሎ ነው።

በባርሴሎና ደግሞ ለእርሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንም ፈር የቀደደ ድል ነበር ያስመዘገበችው። ሳቂታዋ ደራርቱ በሩጫው ሜዳ ብቻ ሳይሆን በስፖርት አስተዳደርም ስሟ በበጎ ይነሳል።

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን በፕሬዝዳንትነት፣ የምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ በምክት ፕሬዝዳንትነት እና በአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንግረስ ደግሞ ኢትዮጵያን ወክላ የምክር ቤቱ አባል የሆነችው ደራርቱ ከቢቢሲ ጋር በነበራት ቃለ ምልልስ ባርሴሎናን አስታውሳለች።

ሩጫ እንዴት ጀመርሽ?

ሩጫ የጀመርኩት በቆጂ ትምህርት ቤት እያለሁ ነው። ሩጫ እወድ ነበር። እረኛም ስለሆንኩኝ ከብትም ለመመለስ ስሄድ፣ ውሃም ስቀዳ፣ ጎረቤትም ስላክ ገበያም ስላክ ሁሌ በሩጫ ነው። ውሃ ስቀዳ ትንሿን ገንቦዬን ተሸክሜ እሮጥ ነበር። ከሩጫ ጎን ለጎን ደግሞ ፈረስ መጋለብ እወድ ነበር።

ትምህርት ቤት ውስጥ ሩጫ የጀመርኩት በ15 ዓመቴ ነበር። ሩጫ እና ፈረስ ግልቢያ የኔ መዝናኛዎች ናቸው። በሩጫ እታወቃለሁ ብዬ ሳይሆን እንዲሁ ስለምወድ ነበር የምሮጠው። እግዚአብሔር ፈቅዶ ደግሞ እንጀራዬ አደረገው።

በሩጫ ለመጀመርያ ግዜ መወዳደር የጀመርሽው የት ነው? ለምን?

ሩጫን የጀመርኩት አርሲ ውስጥ በትንሿ በቆጂ ከተማ በትምህርት ቤቴ ነው። በትምህርት ቤት ውስጥ ለስፖርት ክፍለ ጊዜ፣ ለማርክ ሲባል የተለያዩ ስፖርቶችን እንሰራ እና እንጫወት ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚያውም በውድድሮች ላይ መሳተፍ ጀመርኩኝ። ለትምህርት ቤት፣ ለወረዳ፣ ለአውራጃ ከዚያ ለክፍለ አገር ለመወዳደር በቃሁ።

እኤአ በ1992 ኦሊምፒክ ላይ ስትሳተፊ ምን ተሰማሽ?

እስካሁንም ድረስ ለባርሴሎና ኦሊምፒክ ያለኝ ስሜት ትልቅ ነው። ምክንያቱም እስካሁንም ከአገሬ ሕዝብ እንዲሁም ከዓለም ማኅበረሰብ ጋር ያስተዋወቀኝ ውድድር ነው።

ከእኔ መታወቅ፣ ከእኔ ደስታ በላይ ደግሞ በባርሴሎና ኦሊምፒክ ላይ የእኔ ማሸነፍ ለኢትዮጵያ ሴቶች በር ከፋች በመሆኑ በጣም ደስ ይለኛል። ሁልጊዜም የምደሰትበት ነው።

ለካ ሴቶችም ከሰሩ፣ ወደ ስፖርቱ መድረክ ከመጡ በእንደዚህ ዓይነት የአደባባይ ውድድሮች ላይ ማሸነፍ ይችላሉ ብለው የኢትዯጵያ ሴት አትሌቶች ተነሱ። በዚያ ነው እስካሁን ድረስ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ሴቶች የበረከቱት። ስለዚህ የባርሴሎና ድል ለእኔ ሁለት ስሜት፣ ሁለት ደስታ አለው።

ባርሴሎና ላይ በወቅቱ ስትሳተፊ አሸንፋለሁ የሚል የራስ መተማመን ነበረሽ? እንዲህ ዓይነት ዝግጁነት ነበረሽ?

ከዚያ በፊት በተወሰኑ ውድድሮች ላይ ተሳትፌአለሁ። ኦሊምፒክ ግን የመጀመሪያዬ ነበር። ባርሴሎናን እንደ ማንኛውም ውድድር ነበር ያየሁት። ምክንያቱም በዚያን ወቅት ኦሊምፒክ ከሌሎች ውድድሮች ምን ያህል እንደሚለይ ለይቼ ስለማላውቅ እንደማንኛውም ውድድር ነበር ያየሁት።

ነገር ግን የውድድሩን ትልቅነት የሚያውቁት፣ ዓለም አቀፍ ልምድ ያላቸው አሰልጣኜ አስፈላጊውን ልምምድ አድርገን በከፍተኛ ሁኔታ ነበር ያዘጋጁን።

በወቅቱ ምንም ዓይነት የፍርሃት ስሜት አልነበረኝም፤ ምክንያቱም በእድሜ ልጅ ነበርኩ። የመጀመሪያዬ የኦሊሎምፒክ ውድድርም ስለሆነ መሸነፍና ማሸነፉ ብዙም አላስጨነቀኝም። ግን ጥሩ አቋም ላይ ነበርኩኝ።

ከዚያ ውድድር በፊት ጃፓን ቶኪዮ ላይ ተወዳድሬ ነበር ስምንተኛ ነበር የወጣሁት። ስለዚህ ባርሴሎና ላይ እንደ ቶኪዮው መጨረሻ ላይ ሄደሽ እንዳትቆሚ ከፊት ከሚሄዱት ጋር እግር በእግር እየተከተልሽ ሂጂ ተብዬ ነበር።

ደራርቱ ቱሉ እና ኤላና ሜየር በጋራ ድላቸውን ሲያከብሩ

በወቅቱ 10 ሺህ ማጣሪያ ነበረው። እዚያ ላይ ፉክክሩን ስታዬ ምን ነበር ስሜትሽ?

ጥሩ አቋም ላይ ስለነበርኩኝ፣ ጥሩ ስለተዘጋጀሁኝ ማጣሪያውም ፍጻሜውም አልከበደኝም። አሰልጣኜ በቂ ልምምድ እና ዝግጅት እንድሰራ በማድጋቸው ብዙ አልተቸገርኩም። ሌላው ደግሞ አብረውን የሚወዳደሩትን ብዙዎቹን አላውቃቸውም ነበር። እኔ የማውቀው ሁለት አትሌቶችን ብቻ ነበር። ሌሎቹን አላውቃቸውም። እናም ብዙ አልከበደኝም።

በወቅቱ በተካሄዱት የማጣሪያ እና የፍጻሜ ውድድር መካከል ምን ታደርጊ በር?

(ሳቅ) አሰልጣኜ ዓለም አቀፍ አሰልጣኝ ናቸው። እርሳቸው ከውድድር በፊት ምን እንደምንሰራ፣ በውድድር መካከል ደግሞ ምን እንደምናደርግ ያውቃሉ።

የረዥም ጊዜ ውድድር ፕሮግራም ምን እነደሆነ፣ በዚያ መካከል ደግሞ በማጣሪያ እና በፍጻሜ መካከል ደግሞ ያለውን ስለሚያውቁ እርሳቸው የሚሰጡንን ልምምድ ነበር የምንሰራው።

እንግዲህ አሁን ብዙ አላስታውስም ግን እርሳቸው የሚሰጡንን ስሰራ ደስተኛ ሆኜ ነበር የምሰራው። ግን ከማጣሪያው በኋላ ለፍጻሜውም አልተጨናነኩም ነበር።

ከውድድር በፊት የምታደርጊው የተለየ ነገር አለ?

ሌላ ጊዜ አንደማደርገው ልምምዴን ከቁርስ በፊት ወይንም ደግሞ በኋላ ልሰራ እችላለሁ። ከሰራሁም በኋላ ደግሞ እተኛለሁ። ስለዚህ እበላለሁ፣ እጠጣለሁ፣ ከዚያ ደግሞ አርፋለሁ። ከዚያ ውጪ የተለመደው ምግብ፣ የተለመደው እረፍት፣ የተለመደውን ልምምድ ነው ያደረግኩት።

ማታ ራሱ ማሟሟቂያ ሰዓቴ እስኪደረስ ድረስ ስታዲየም ውስጥ መተኛቴ ትዝ እለኛል። ማማሟቂያ ሜዳ ላይ በጣም ጥሩ እንቅልፍ መተኛቴ ትዝ ይለኛል። ትዝ ይለኛል አሰልጣኜ ነበረ የቀሰቀሱኝ። ብዙ ነገር ስለባርሴሎና ይረሳኛል ይህ ግን አይረሳኝም።

ደራርቱ ቱሉ እና ኤላና ሜየር በጋራ ሲፎካከሩ

ስለ ፍጻሜው ውድድር ትዝ የሚልሽ ነገር ምንድን ነው?

ሳስብ የነበረው አሰልጣኜ ልክ የቶኪዮው ዓይነት ነገር እንዳይገጥመኝ የመከሩኝን ነበር። እሱም ተጠንቅቀሽ ሩጪ፣ ከከበደሽ በራስሸ ጊዜ ሩጪ፣ እንዳትደነዝዢ ነበር ያሉኝ።

እርሳቸውም እነዳሉኝ፣ ቀስ እያልኩ ነበር ዙሩን የሄድኩት። ምክንያቱም እርሳቸው ልጆቹ ፈጥነው የሚሄዱብሽ ከሆነ ራስሽን ጠብቀሽ ሂጂ ብለውኝ ነበር።

ደቡብ አፍሪካዊቷ ኤለና ሜየር አስር ዙር ሲቀር ነበር የሄደችው እና እኔ ቀረት ብዬ ቀስ ብዬ ነበር የደረስኩባት። ምክንያቱም እኔ አሰልጣኜን በጣም አከብራለሁ። በጣም እወዳቸዋለሁ። የሚሉኝንም ስለምሰማ እና ቃላቸውን ስለማከብር እርሳቸው የመከሩኝን ነበር እያሰብኩ ስሮጥ የነበረው።

ከሦስት፣ ከአራት ዙር በኋላ ነበር የደረስኩባቸው። ልክ አሰልጣኜ የመከሩኝን ነበረ የማደርገው።

ስታሸንፊ ምን ተሰማሽ?

በወቅቱ የስፔኗ ባርሴሎና በጣም ሞቃት ነበረች፣ በዚያ ሙቀት ቲሸርት ደርቤ ነበር ስሮጥ የነበረው። ነገር ግን አቋሜ ጥሩ ነበረ።

ልክ 400 ሜትር ሲቀር እንደምወጣ እና በአጨራረስ እንደማሸንፋቸው ነበር የማስበው እና ጥሩ ስሜት ነበር የተሰማኝ። ደስታውም ወደር አልነበረውም።

ውድድሩን በአሸናፊነት ካጠናቀቅሽ በኋላ ከኤላና ሜየር ጋር ደስታችሁን በጋራ ነበር የገለጻችሁት፤ ለምን?

ይሄማ ሁል ጊዜ የሚደረግ ነገር ነው። ምክንያቱም አሸንፈን ሁለታችንም አንደኛ እና ሁለተኛ ነው የወጣነው። አንደኛው ሁለታችንም ከአፍሪካ ነበርን። ሁለተኛው ደግሞ አፓርታይድ ያበቃበት ወቅት ነበር።

ደቡበን አፍሪካውያን በዚያን ጊዜ ከአፓርታይድ ሥርዓት ማብቃት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉበት ኦሊምፒክ ስለነበር በጋራ ደስታችንን ገለጽን።

ከኤሌና ጋር ባንተዋወቅም እንግዲህ ስፖርት ለእህትማማችንት፣ ለሰላም፣ ለፍቅር የሚለው እዚያ ሜዳ ላይ ታየ ማለት ነው። በዚህ ምክንያት ነበር ደስታችንን ነው የገለጽነው ማለት ነው።

ከድል በኋላ በአገር ቤት የነበረው አቀባበል ምን ይመስል ነበር?

(ሳቅ) በጣም የተለየ ነበር። በጣም በጣም የተለየ እና እስከዛሬም ድረስ ልዩ ስሜት የሚፈጥርብኝ አቀባበል ነበር።

ቤተሰቤ፣ ፌዴሬሽናችን፣ አገራችን፣ መሥሪያ ቤቴ (ማረሚያ ቤቶች)፣ ጓደኞቼ ሁሉም በአጠቃላይ እንደ አገር ጀግና ነበር የተቀበሉኝ። እና ሁሌም በጣም በጣም ሁሌም የማይረሳ አቀባበል ነው ያደረጉልኝ። በጣም ነበር ደስ ያለኝ።

በተጨማሪም እኔ ወታደር ስለሆንኩ ከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ ያገኘሁበትም ነው። በወቅቱ ከፍተኛ ገንዘብ የተሸለምኩበት፣ እንደገና ደግሞ በአገሬ ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ያወቀኝ፣ እና ብቻ ለእኔ ልዩ ነበር ያ ጊዜ።

አሸናፊነትሽ ጥሎ ያለፈው ነገር ምንድን ነው? እንዴት እታወሳለሁ ብለሽ ታስቢያለሽ?

(ሳቅ) እንግዲህ ጥሎ ያለፈው እንደገለጽኩት ከሕዝበ ጋር ያስተዋወቀኝ ይህ የባርሴሎና ድል ነው። ሁለተኛ ደግሞ የኢትዮጵያውያን አትሌቶች ምሳሌ መሆኔ የእኔ ውርስ [ሌጋሲ] ነው ብዬ አስባለሁ።

የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት ሴት የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ በመሆንሽ እና ለአገርሽ እና ለአፍሪካ ፈር ቀዳጅ የሆነውን ውጤት ማስመዝገብሽ ምን ስሜት ፈጥሮብሽ ነበር?

(ሳቅ) እንግዲህ ባርሴሎና የመጀመሪያዬ ይሁን አንጂ ብዙ ውድድሮችን አድርጌያለሁ። ከአገር አቋራጭ ጀመሮ የተለያዩ ውድድሮችን አሸንፌያለሁ። ብዙ የተለየ ነገር አይሰማኝም።

እንዲያውም ምንድን ነው አሁን ከአትሌትነት ወጥቼ ወደ ስፖርት አመራርነት ስመጣ እና በቅርቡ ደግሞ ከአሜሪካ ኦሪገን በድል ስንመለስ ልክ የባርሴሎናው እና የሲድኒው ጊዜ ድል ነው ትዝ ያለኝ።

በሩጫ ዘመኔ እንደዚህ ዓይነት አቀባበል ሲደረግ ማየቴ በጣም ነው ያስደሰተኝ። ምከንያቱም አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ነው እንደዚህ ዓይነት ዕድል የሚሰጠው።

እኔ ያሳለፍኩባቸው ጊዜያት ወርቃማ ናቸው። ምክንያቱም ያለውንም ጊዜ በደንብ ነበር የተጠቀምኩበት። በጣም ነው ደስ የሚለኝ። በጣም በጣም ወርቃማ ጊዜያት ነበሩ። ለእኔም ለቤተሰቤም ልዩ ጊዜ ነበር። የዛሬ 30 ዓመትን ዛሬ ላይ ቆሜ ሳስታውሰው በጣም ደስ ይለኛል።

ደራርቱ ቱሉ ከዘመኑ ኮከብ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ጋር
የምስሉ መግለጫ, ደራርቱ ቱሉ ከዘመኑ ኮከብ አትሌት ለተሰንበት ግደይ ጋር

ሦስት የቤተሰቦችሽ አባልም በሩጫው ዘርፍ ውጤታማ አትሌቶች ናቸው። ቤተሰቦችሽ በሩጫው ውጤታማ የመሆናቸው ሚስጥሩ ምንድን ነው?

(ረዥም ሳቅ) ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ምንም የተለየ ምስጢር የለውም። አንዱ ደግሞ ወደዚህ እስከመጣሁ ድረስ እኔ በጣም ሥራዬን አክባሪ ነኝ። ታታሪ ነኝ። የሚጠበቅብኝን በሚገባ እሰራለሁ። ልምምዴን በደንብ እሰራለሁ።

አንድ ሰው ሥራው በእግዚአብሔር እንዲባረክልት በተቻለ መጠን መልፋት፣ መጣር አለበት። ከዚያ ደግሞ ባለው ዕምነት እግዚአብሔር ጥረቱን እንዲባርክለት ፀሎት ማድረግ አለበት። ዋናው ጠንክሮ መስራት፣ መታገስ፣ ለሥራ ያለን ፍቅር ማሳየት ነው። ይኸው ነው ሌላ የተለየ ነገር የለውም።

የስፖርት ቡድንን ለመቀላቀል ብለሽ ለእናትሽ ሳትናገሪ መሄድሽ እውነት ነው?

ከዛሬ 35 ዓመት በፊት እኔ ሩጫ ስጀምር አገር ቤት የነበረው አመለካከት፣ ሴት ልጅ ረዥም ቀሚስ ለብሳ፣ በሥነ ሥርዓት ትምህርቷን ተምራ፣ ትዳርም የምትይዝ ከሆነ በሥርዓቱ ተድራ ቤተሰብ ትመሠርታለች እንጂ በቁምጣ መታየት ነውር ነው።

ስለዚህ እናቴም እንደ አንድ እናት ጥሩ ልጅ ሆኜ፣ ጨዋ ልጅ ሆኜ እንዳድግ ትፈልጋለች። ስለዚህ በዚያ ጊዜ ከወንድ ጋር መሮጥ፣ በቁምጣ መሮጥ፣ እንደ ባለጌ ልጅ፣ ሥነ ምግባር እንደ ሌላት ልጅ ያስቆጥራል። ስለዚህ ለእናቴ ፍላጎቴን ብነግራት ስለማትፈቅድልኝ ለአባቴ እና ለእህቶቼ፣ ለአክስቶቼ ነግሬ ነበር የመጣሁት።

በዚያው ወቅት ባርሴሎና ከሩጫ ሜዳው ውጪ ምን ተሰማሽ? ከተማውን ጎበኘሽ?

(ሳቅ) በዚያ ወቅት ምንም አላየሁም። ምክንያቱም ሁልጊዜ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች፣ አሁንም ድረስ የምናደርገው የግል ውድድር ካልሆነ በስተቀር፣ አገር ወክለን ስንሄድ ውድድራችን እና ልምምዳችን ላይ ነው የምናተኩረው።

ውድድር የጨረሰ ውድድር ያልጨረሰውን መደገፍ ማበረታታት እንጂ እንደዚህ ከተማ የመዞር፣ ገበያ የመሄድ ብዙም ልምድ የለንም። እስከዛሬ ድረስም የኢትዮጵያን አትሌቶች፣ አንዱ የማመሰግንበት ነገር ይሄ ነው።

ስለዚህም የዚያን ጊዜ ባርሴሎናን ተዘዋውሬ አላየኋትም። ነገር ግን የማስታውሰው ልምምድ በምሰራበት ወቅት፣ የልምምድ ስታዲየም መኖሩ፣ ምግብ ቤቶቹ 24 ሰዓት ክፍት መሆናቸው እርሱ እርሱ ለእኔ ይገርመኝ ነበር።

የሚስተናገደው ሰው ብዛት ይገርመኝ ነበር። በቁርስ ሰዓት፣ በምሳ ሰዓት በእራት ሰዓት ሰዉ አይቀንስም እና ወጪ ወራጁ መብዛቱ ይገርመኝ ነበር። በወቅቱ ከተማዋን ተዘዋውሬ ባላያትም የባርሴሎና ኦሊምፒክ ለእኔ አሁንም ድረስ የተለየ ነው።

ከባርሴሎና በኋላ ከኤለና ሜየር ጋር ግንኙነታችሁ ቀጥሏል?

እርሷ ናት ከእኔ ቀድማ ሩጫ ያቆመችው። ሩጫ እስክታቆም ድረስ እንገናኝ ነበር። ከዚያ በኋላ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ በአጋጣሚ እንገናኝ ነበር። የደቡብ አፍሪካው ዩኒቨርስቲ የክብር ዶክተሬት ሲሰጠኝ የክብር እንግዳ ሆና መጥታ ተገናኝተናል። ለመጨረሻ ጊዜ የተገናኘነው ያኔ ነው።

ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና