5 ጥያቄዎች ለስድስት ኢትዮጵያውያን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለሙያ ሴቶች

ዶ/ር ሶስና ኃይሌ፣ ቤተልሔም ደሴ፣ ዶ/ር ሩት ድሪባ፣ ብርሃን ታዬ፣ ቤተልሔም ላቀው እና ሕሊና ኃይሉ ንጋቱ
የምስሉ መግለጫ, ዶ/ር ሶስና ኃይሌ፣ ቤተልሔም ደሴ፣ ዶ/ር ሩት ድሪባ፣ ብርሃን ታዬ፣ ቤተልሔም ላቀው እና ሕሊና ኃይሉ ንጋቱ

አዲሱን ዓመት 2015 ዓ.ም. ምክንያት አድርገን በተለያየ የሳይንስ ዘርፍ ያሉ ስድስት ኢትዮጵያውያን ሴቶችን አምስት ጥያቄዎች ጠይቀናል።

“የሕዳሴ ግድቡ አሜሪካ የሰው ልጅን ጨረቃ ላይ ከላከችበት የስኬት ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ነው” ዶ/ር ሶስና ኃይሌ

ዶ/ር ሶስና ኃይሌ

የፎቶው ባለመብት, Annette Patko

ዶ/ር ሶስና ኃይሌ- በአሜሪካ፣ ኢሊኖይ ግዛት፣ በኖርዝዌስተርን ዩኒቨርስቲ የማቴሪያልስ ሳይንስ እና ኢንጂነሪንግ ፕሮፌሰር እንዲሁም ኬሚስት

በ2014 ዓ. ም. ባንቺ ሙያ ከተፈጠሩ ወይም ከተሠሩ መካከል ያስደነቀሽ የቱ ነው? ለምን?

ሥራዬ ከኢነርጂ ሳይንስ ጋር ይገናኛል። ዋናው ትኩረቴ ደግሞ ኤሌክትሮኬሚካል ኢነርጂ ትራንስፎርመሮች ናቸው።

በሙያዬ እጅግ ያስገረመኝ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ነው። ይህም አሜሪካ የሰው ልጅን ጨረቃ ላይ ከላከችበት የስኬት ታሪክ ጋር ተመሳሳይ ነው።

የሕዳሴ ግድቡን ጨረቃ ላይ ከመውጣት የሚለየው ዓለምን በሳይንስ ከማሳመን አልፎ የአየር ንብረት ቀውስን ሳያባብስ በአፍሪካ ቀንድ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኃይል ድህነት (Energy Poverty) መንጭቆ ማውጣቱ ነው።

በ2014 ዓ. ም. ካደረግሻቸው መካከል ትልቁ ስኬቴ የምትይው የቱን ነው?

ያለፈው ዓመት ትልቁ ስኬቴ ከአሜሪካ የኢነርጂ ክፍል በተመደበ ገንዘብ የጥናት ቡድን አሰባስቤ ‘ኢነርጂ ፍሮንቲርስ ሪሰርች ሴንተር’ የተባለ የጥናት ማዕከል መቋቋሙ ነው።

ሥራችን፣ ሀይድሮጅን ከጠጣር አካሎች ጋር ስለሚያደርገው ግንኙነት የዓለምን መረዳት የሚያሳድግ ነው። ለአራት ዓመት 10 ሚሊዮን ዶላር አግኝተናል።

ጥናታችን፣ በኤሌክትሪካል ኢነርጂ አማካይነት ውሃን በመክፈል ሃይድሮጅን ለማምረት መሠረት ይጥላል።

ለ2015 ዓ. ም. ምን አቅደሻል?

ኧረ ዕቅዶቼ ብዙ ናቸው! ያለው ጊዜም አጭር ነው! ዕቅዶችሽን ያለ ተጨባጭ ግብ በአደባባይ መናገር ደግሞ ወደ ውድቀት ሊያመራም ይችላል።

እኔና የጥናት ቡድኔ፣ ኤሌክትሪሲቲ በመጠቀም ውሃን ለመክፈል የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን መፍታት ነው ዕቅዳችን።

ልክ እንደ ሕዳሴ ግድቡ፣ የኤሌክትሪክ ኃይልን ከካርበን ነጻ ከሆኑ ምንጮች ማመንጨት ነው ሐሳቡ። ኤሌክትሪኩን ኋላ ላይ ለመጠቀም ሀይድሮጅን ማምረት ቁልፉ ነው።

በ2014 ዓ. ም. አንብበሻቸው ከወደዳቸው መጻሕፍት መካከል ሰዎች ቢያነቧቸው የምትያቸው ሦስት መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? ሦሰት ቢታዩ የምትያቸው ፊልሞችስ?

አይ ምንም የለኝም! የዳንኤል ካህንማን “Thinking, Fast and Slow” ማንበብ ፈልጌ ነበር ግን ገና ጊዜ አግኝቼ አልጀመርኩትም።

ካጠቃላይ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ወይም ግኝቶች የቱ ያስገርምሻል? ለምን?

የዌብ ስፔስ ቴሌስኮፕ ምሥሎች እጹብ ድንቅ ናቸው። አስትሮፊዚሲስቶች 13.7 ቢሊዮን ዓመታት ወደኋላ ተጉዘው ማየት ችለዋል።

እንዴት ወደዚች ምድር እንደመጣን ለማወቅ መመራመራችን ከሌሎች የምድራችን ፍጡራን የተለየን ያደርገናል።

እነዚህ ስለጋላክሲዎች አፈጣጠር የሚነግሩን ምሥሎች አንዳች መንፈሳዊ ኃይል አላቸው። ምድራችንን ጠብቀን ለልጅ ልጆቻችን እንደምናወርስ ተስፋ አደርጋለሁ።

ግራጫ መስመር

“ኢንተርኔትን የመሰለ ፈጠራኮ የለም” ቤተልሔም ደሴ

ቤተልሔም ደሴ- የአይኮግ ኤኒዋን ካን ኮድ ዋና ኃላፊትና ኮምፒውተር ሳይንቲስት

ቤተልሔም ደሴ

የፎቶው ባለመብት, Mikiyas Melese

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በ2014 ዓ. ም. ባንቺ ሙያ ከተፈጠሩ ወይም ከተሠሩ መካከል ያስደነቀሽ የቱ ነው? ለምን?

ቃላት፣ ሐረግና ዓረፍተ ነገር ተሰጥቶት ወደ ምሥል የሚቀይረው አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ሰው ሠራሽ ልኅቀት) አስደናቂ ነው።

ኤአይ የሥዕል ውድድርም አሸንፏል። ይህ እውን ሆኖ ስናይ፣ ሳናስበው ወዴት እየሄድን ነው? የሚል ጥያቄም ያጭራል።

በ2014 ዓ. ም. ካደረግሻቸው መካከል ትልቁ ስኬቴ የምትይው የቱን ነው?

የ2014 ዓ. ም. ከፍታዬ ‘Rebel Girls’ የተባለው መጽሐፍ ላይ መውጣቴ ነው። ከድሮም የልጆች መጽሐፍ ላይ መውጣት አልም ነበር።

እኔ ባለሁበት መጽሐፍ እነ ቢሊ አይሊሽ፣ እነ ቴይለር ስዊፊት አሉበት። ስለዚህ ይገዙታል ማለት ነው። ሲገዙት ደግሞ እነሱ ጋር ደረስኩ ማለት ነው።

መጽሐፉ እስካሁን 5 ሚሊዮን ኮፒ ተሸጧል። ትልቁ የሰው ልጅ ከፍታ ሌሎች ሰዎችን ማነሳሳት ነው።

ለ2015 ዓ. ም. ምን አቅደሻል?

የ2015 ዓ. ም. ዕቅዴ ከ13 ዓመቴ ጀምሮ ያለምኩትን ማሳካት ነው። ይህም ተንቀሳቃሽ የኮምፒውተር ማዕከል ነው። ‘ዲጂ ትራክ ኢትዮጵያ’ ይባላል።

ይህም 40 ጫማ ኮንቴነር ሲሆን በፀሐይ ይሠራል። በየከተማው እየዞረ ኮዲንግ እና ሮቦቲክስ ያስተምራል። በጣም በጣም በጉጉት የምጠብቀው እሱን ነው።

በ2014 ዓ. ም. አንብበሻቸው ከወደዳቸው መጻሕፍት መካከል ሰዎች ቢያነቧቸው የምትያቸው ሦስት መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? ሦሰት ቢታዩ የምትያቸው ፊልሞችስ?

ቢነበቡ የምላቸው መጻሕፍት፡

Shoe Dog [ፊል ናይት]

21 Lessons for the 21st Century [ዮቫል ኖሀ ሀሪሪ]

The Thing Around Your Neck [ቺማማንዳ ንጎዚ አዲቺ]

ቢታዩ የምላቸው ፊልሞች ደግሞ The Gentlemen፣ Rick and Morty እና Love, Death & Robots

ካጠቃላይ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ወይም ግኝቶች የቱ ያስገርምሸል? ለምን?

ኢንተርኔት! ምንም ጥያቄ የለውም።

ኢንተርኔትን የመሰለ ፈጠራኮ የለም። ሕይወት ለውጧል። የዕውቀት ሽግግርን አስችሏል። ተደራሽነቱ በመስፋቱና በመላው ዓለም በመዳረሱ በተለይም በወጣቶች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አለው።

ግራጫ መስመር

“የወባ ክትባት ተስፋ የሰጠኝ ግኝት ነው” ዶ/ር ሩት ድሪባ

ዶ/ር ሩት ድሪባ- የላስት ማይል ኸልዝ ቴክኒካል አማካሪና የሕክምና ባለሙያ

ዶ/ር ሩት ድሪባ

የፎቶው ባለመብት, Ruth Diriba

በ2014 ዓ. ም. ባንቺ ሙያ ከተፈጠሩ ወይም ከተሠሩ መካከል ያስደነቀሽ የቱ ነው? ለምን?

ከመቶ ዓመታት በላይ ለወባ በሽታ ክትባት ለማግኘት ሲሞከር ነበር። ክትባቱ ተገኝቶ በቅርቡ ይፋ ተደርጓል። እስከ 80 በመቶ የወባ በሽታን የመከላከል አቅም ስላለው በበሽታው ሕይወታቸውን የሚያጡ ሕጻናትን ሞት ለመቀነስ ተስፋ ሰጥቷል። በ2014 ዓ. ም. በጣም ያስገረመኝ እና ተስፋ የሰጠኝም ግኝት ነው።

በ2014 ዓ. ም. ካደረግሻቸው መካከል ትልቁ ስኬቴ የምትይው የቱን ነው?

ትልቁ ስኬቴ፣ በዓይነቱ ልዩ ሆኖ ለመጀመሪያ ጊዜ በጤና ጥበቃ እንዲሁም በላስት ማይል ኸልዝ የተተገበረው ለጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች በዲጂታል ቴክኖሎጂ ሥልጠና የሚሰጥበት (Blended Learning) ዲዛይን እና ትግበራ ላይ መሳተፌ ነው።

ለ2015 ዓ. ም. ምን አቅደሻል?

እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ፣ በ2015 ዓ. ም. የሕጻናትን ጤና የሚያሻሽል ሥራ ላይ የመሳተፍ፣ ማኅበረሰቡን እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችን ያማከለ ሥራም የመሥራት እቅድ አለኝ።

በ2014 ዓ. ም. አንብበሻቸው ከወደዳቸው መጻሕፍት መካከል ሰዎች ቢያነቧቸው የምትያቸው ሦስት መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? ሦሰት ቢታዩ የምትያቸው ፊልሞችስ?

ቢነበቡ የምላቸው መጻሕፍት፡

Winning with People [ጆን ማክስዌል]

The Checklist Manifesto [በአቱል ጋውንዴ]

Our Iceberg is Melting [ሆልገር ራታግበር እና ጆን ኮተር]

ቢታዩ የምላቸው ፊልሞች ደግሞ Fractured፣ Unforgivable እና Sweet girl

ካጠቃላይ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ወይም ግኝቶች የቱ ያስገርምሻል? ለምን?

የሚደንቀኝ ፈጠራ ክትባት ነው። በሽታን፣ በበሽታ አምጭ ተሕዋስ ወይም ባለው ንጥረ ነገር ሰውነትን አለማምዶ በሽታን እንዲከላከል ቀድሞ ማዘጋጀት እና ስቃይን ብሎም ሞትን መቀነስ በጣም ትልቅ ፈጠራ ነው።

ግራጫ መስመር

“ኅትመትን የሚበልጥ ፈጠራ ያለ አይመስለኝም” ብርሃን ታዬ

ብርሃን ታዬ- የቴክኖሎጂ ፖሊሲ አጥኚ እና ተንታኝ

ብርሃን ታዬ

የፎቶው ባለመብት, Berhan Taye

በ2014 ዓ. ም. ባንቺ ሙያ ከተፈጠሩ ወይም ከተሠሩ መካከል ያስደነቀሽ የቱ ነው? ለምን?

ያስገረመኝ ዶትፕሎት (DotPlot) መተግበሪያ ነው። ይሄ መተግበሪያ ስልክ ላይ ተጭኖ ሴቶች የጡት ካንሰርን ቀድመው ማወቅ እንዲችሉ ጡታቸው ላይ የሚታይ ለውጥን ይከታተሉበታል።

ገና በሕክምና ፈቃድ ሰጪዎች ይሁንታ እስከሚሰጠው እየጠበቀ ቢሆንም፣ እንዲህ ያለ መተግበሪያ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሴቶች የጡት ካንሰርን እንዲከላከሉ ይረዳል።

በ2014 ዓ. ም. ካደረግሻቸው መካከል ትልቁ ስኬቴ የምትይው የቱን ነው?

ትልቁ የ2014 ዓ. ም. ስኬቴ በቋሚነት የአካል ብቃት እየሠራሁ 10 ኪሎ ሜትር መሮጤ ነው።

ለ2015 ዓ. ም. ምን አቅደሻል?

ዕቅዴ ዋጋ ከምሰጣቸው ሰዎች ጋር ውብ ጊዜ ማሳለፍና በበይነ መረብ ላይ የማሳልፈውን ጊዜ ቀንሼ ከሰዎች ጋር የበለጠ መነጋገር ነው።

በ2014 ዓ. ም. አንብበሻቸው ከወደዳቸው መጻሕፍት መካከል ሰዎች ቢያነቧቸው የምትያቸው ሦስት መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? ሦሰት ቢታዩ የምትያቸው ፊልሞችስ?

ቢነበቡ የምላቸው መጻሕፍት፡

Do Not Disturb: The Story of a Political Murder and an African Regime Gone Bad [ሚሼላ ሮንግ]

Seven and a half Lessons about the Brain [ሊሳ ፌልድማን]

Race after Technology [ሩሀ ቤንጃሚን]

ፊቸር ፊልም እንኳን ብዙ አላይም። ግን ተከታታይ ፊልሞች ልጠቁም። እነዚህም Paper Girls፣ Veep እና The office ናቸው።

ካጠቃላይ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ወይም ግኝቶች የቱ ያስገርምሻል? ለምን?

ኅትመትን የሚበልጥ ፈጠራ ያለ አይመስለኝም። ሕይወት የሰጠን ኅትመት ነው።

“ኢትዮጵያ ውስጥ ስብ መምጠጥ መጀመሩ ደንቆኛል” ቤተልሔም ላቀው

ቤተልሔም ላቀው- የሊሄም ኒውትሪሽን መሥራች፣ የቤኑ ፉድስ አጋር መሥራችና ኃላፊት፣ የአክት ፎር ፉድ አክት ፎር ቼንጅ ንቅናቄ መሪ እንዲሁም ኒውትሪሽኒስት

ቤተልሔም ላቀው

የፎቶው ባለመብት, Zola Studio

በ2014 ዓ. ም. ባንቺ ሙያ ከተፈጠሩ ወይም ከተሠሩ መካከል ያስደነቀሽ የቱ ነው? ለምን?

ኢትዮጵያ ውስጥ ስብ መምጠጥ [Fat Removal] ተጀምሯል። ይሄ ሂደት እኛ አገር እንዲህ በቅርብ ጊዜ ይገባል ብዬ አልገመትኩም ነበር። በጣም ነው ያስደነቀኝ።

በ2014 ዓ. ም. ካደረግሻቸው መካከል ትልቁ ስኬቴ የምትይው የቱን ነው?

የዓለም አቀፉ ‘አክት ፎር ፉድ አክት ፎር ቼንጅ’ ንቅናቄ የኢትዮጵያ ወጣቶች ተወካይ ሆኜ የተለያዩ ሥራዎችን እሠራ ነበር። 2014 ዓ. ም. በጣም ስኬታማ የሆንበት ነው።

ለ2015 ዓ. ም. ምን አቅደሻል?

ሊሄም በትንሽ ደረጃ ነበር የሚሠራው። በ2014 ዓ. ም. ግን አድጎ፣ ቢሮ ተከራይተን መሥራት ጀምረናል። ቢዝነሱ ከተጀመረ እንኳን ቆይቷል። እና በ2015 ዓ. ም. ከአጋሮቻችን ጋር ተጣምረን ወደ ክሊኒክ የማሳደግ ዕቅድ ይዘናል።

በ2014 ዓ. ም. አንብበሻቸው ከወደዳቸው መጻሕፍት መካከል ሰዎች ቢያነቧቸው የምትያቸው ሦስት መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? ሦሰት ቢታዩ የምትያቸው ፊልሞችስ?

ቢነበቡ የምላቸው መጻሕፍት፡

ትንሿ ቤተክርስቲያን [ገብረእግዚአብሔር ኪዳን]

Zero to One [ፒተር ታይል]

ሕክምና በቤታችን [በቀለች ቶላ]

ፊልም እንኳን አላይም። በምትኩ ቢጎበኙ ብዬ የማስባቸውን ሦስት ቦታዎች ልንገርሽ። ላሊበላ፣ አክሱም እና የሩዋንዳው ‘ኪጋሊ ጄኖሳይድ ሜሞሪያል’

ካጠቃላይ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ወይም ግኝቶች የቱ ያስገርምሻል? ለምን?

የኢንዶስኮፒ ምርመራ መደረግ መቻሉ ያስገርመኛል። በእርግጥ ውስብስብ ሳይንስ አይደለም። አሁን ባለው መሣሪያ በቀላሉ የትኛውም ሆስፒታል ውስጥ ሊሠራ ይችላል።

አንድን ግለሰብ ሳናፈርሰው ስላለበት ሂደት እንድናውቅ ያስችላል። የላብራቶሪ ምርመራና የደም ሕዋስ ማየት መቻል አሁን ላለንበት ዘመን ትልቅ ግኝት ነው።

ግራጫ መስመር

“የሰውነት አካላትን በቀዶ ሕክምና መለወጥ ያስደነቀኛል” ሕሊና ኃይሉ ንጋቱ

ሕሊና ኃይሉ ንጋቱ- በአሜሪካ ዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ፣ በርክሌ የኮምፒውተር ሳይንስ የፒኤችዲ ሁለተኛ ዓመት ተማሪ

ሕሊና ኃይሉ ንጋቱ

የፎቶው ባለመብት, Hellina Hailu Nigatu

በ2014 ዓ. ም. ባንቺ ሙያ ከተፈጠሩ ወይም ከተሠሩ መካከል ያስደነቀሽ የቱ ነው? ለምን?

በ2014 ዓ. ም. ካስደመሙኝ ፈጠራዎች አንዱ በኤአይ ሞዴል የሚፈጠሩ ምሥሎች የጥራት ደረጃ ነው። እነዚህ ሞዴሎች በስፋት ጥቅም ላይ ይውላሉ።

በአንድ በኩል እንደ ቤኖ ሳሙኤል ያሉ ባለሙያዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥነ ጥበብ ሲሠሩ ያስገርመኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ተገቢው ቁጥጥር ያልተደረገበት ቴክኖሎጂ ጉዳቱ ያሰጋኛል።

በ2014 ዓ. ም. ካደረግሻቸው መካከል ትልቁ ስኬቴ የምትይው የቱን ነው?

ትልቁ ስኬቴ በአሶሴሽን ፎር ኮምፒውቲንግ ማሽነሪ ተቋም የኮምፒውቴሽናል እና ዳታ ሳይንስ ፌሎሺፕ ማሸነፌ ነው።

ለ2015 ዓ. ም. ምን አቅደሻል?

በ2015 ዓ. ም. በዩሲ በርክሌይ ዩኒቨርስቲ ሁለተኛ ዓመት ፒኤችዲ ትምህርቴን እከታተላለሁ። ዕቅዴም ከአፍሪካውያን አጋሮቼ ጋር ተጣምሬ ማኅበረሰባችንን የሚጠቅም ሥራ ማከናወን ነው።

በ2014 ዓ. ም. አንብበሻቸው ከወደዳቸው መጻሕፍት መካከል ሰዎች ቢያነቧቸው የምትያቸው ሦስት መጻሕፍት የትኞቹ ናቸው? ሦሰት ቢታዩ የምትያቸው ፊልሞችስ?

ቢነበቡ የምላቸው መጻሕፍት፡

All about Love [ቤል ሁክስ]

Race After Technology [ሩሀ ቤንጃሚን]

Shadow King [መዓዛ መንግሥቴ ]

ቢታዩ የምላቸው ፊልሞች Queen of Katwe፣ Us እና እረኛዬ

ካጠቃላይ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች ወይም ግኝቶች የቱ ያስገርምሻል? ለምን?

አንድ ፈጠራ መምረጥ ካለብኝ፣ የተለያዩ የሰውነት አካላትን በቀዶ ሕክምና መለወጥ (Organ Transplant) ይደንቀኛል። ለምን? የሚለው ግልጽ ነው። የሰዎችን ሕይወት ስለሚያተርፍ።