አሜሪካ የዩፎዎች መኖር ጥያቄ ላይ ነው እያለች ነው

ፔንታጎን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ መንግስት የዩፎዎችን (unidentified flying objects ) ማለትም ምንነታቸው ያልታወቁ በራሪ አካላት መታየታቸውን አስመልክቶ ባሰራጨው ዘገባ ኤሊየን የተባሉ ፍጡራን ስለ መኖራቸው ምንም ዓይነት ማስረጃ ባያገኝም የሉም ብሎ መደምደም እንደማይፈልግ ባለስልጣናት ለአሜሪካ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

የ 120 ክስተቶችን ግምገማ ተከትሎ የአሜሪካ ቴክኖሎጂዎች በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸው የለበትም ብሎ ይደመድማል የሚል ግምት ይጠበቃል፡፡

ከዚያ ውጭ ግን ሪፖርቱ በነዚህ በራሪዎች ምንነት ላይ ትክክለኛ ግምገማ አልሰጠም ተብሏል፡፡

ይፋ ያልሆነው የሪፖርቱ አንድ ክፍል በሰኔ ወር ለህግ አውጭዎች ይቀርባል፡፡

ሪፖርቱ ባለፈው ዓመት በአሜሪካ የአየር ክልል ለአስር ዓመታት ያልተገለፁ የአየር ላይ እንቅስቃሴዎችን ለመመርመር የተቋቋመው ወታደራዊ ግብረ ኃይል ውጤት ነው ተብሏል፡፡

የመከላከያ ሚንስቴሩ በዩፎዎች ያሉትን "ግንዛቤያቸውን ለማሻሻል" እና ለአገር ደህንነት ስጋት ስለመሆናቸው ለማወቅም እፈልጋለሁ ብሏል፡፡

የሪፖርቱ ይፋ መሆን ስለ ዩፎ መታየት እና ተያያዥ ስለሆነው የኤሊየን ፍጡራን ሴራ ጽንሰ ሃሳብ ጋር በተያያዘ የአሜሪካውያንን ቀልብ ስቧል፡፡

ሰኔ 25 ቀን ለኮንግረሱ ሊቀርብ የታቀደውን የሪፖርቱን ይዘት አስመልክቶ ግምቶች በዩፎ ደጋፊዎች እየቀረቡ ነው፡፡

ስለ ሪፖርቱ ምን እናውቃለን?

የጥናቱን ዝርዝር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘገበው በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ሲሆን በመቀጠልም ሲ ኤን ኤን እና ዋሽንግተን ፖስት ተቀባበሉት፡፡

መገናኛ ብዙኃኑ ስለ ግኝቱ ከበርካታ የመንግስት ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከተመዘገቡት የ 120 እና ከዚያ በላይ ክስተቶች መካከል አብዛኛዎቹ በአሜሪካ የባህር ኃይል ሠራተኞች ሪፖርት የተደረጉ ናቸው። የተወሰኑት ደግሞ የውጭ ሃገር ወታደሮችን መረጃ ያካተቱ ናቸው ፡፡

በቅርብ ዓመታት የባህር ኃይል አውሮፕላን አብራሪዎች የተመለከቱት የአየር ላይ ክስተቶች እንግዳ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ምንም ማስረጃ የለም ሲል ታይምስ ዘግቧል፡፡

ጋዜጣው የስለላ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ የተወሰኑት ክስተቶች እንደ ቻይና ወይም ሩሲያ ያሉ ተቀናቃኝ ሃገራት የሙከራ ቴክኖሎጂ ተደርጎ ሊወስድ ይችላል ብሏል፡፡

ጋዜጣው እና ሲኤንኤን የስለላ ባለሥልጣናት ጠቅሰው የብሔራዊ ደህንነት ድምዳሜው አንድምታ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል፡፡

ዩፎዎች ተከስተዋል?

ባለፈው ወር የሲቢኤስ ኒውስ ዘገባን ተከለትሎ በዩፎዎች ዙሪያ ውይይቱ ጦፎ ነበር።

እንደ መገናኛ ብዙሃኑ ከሆነ ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው የአሜሪካ የባህር ኃይል አብራሪዎች በፍጥነት የማይበሩ ቁሶችን ማየታቸውንና ከዚህ በፊት ካዩዋቸው የሚለዩ ናቸው ብለዋል፡፡

ያን ግሬቭስ የተባሉ ጡረተኛ ፓይለት በበኩላቸው ተዋጊ አውሮፕላኖቻቸው እአአ በ 2014 ከቨርጂኒያ ዳርቻ በሚገኘውና በተከለከለው የአየር ክልል ላይ ሲያንዣብቡ ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡

ቁሶቹ የማይታይ የጭስ ማውጫ የየሌትም እና የታወቁ የቴክኖሎጂ ገደቦችን የሚጥስ በሚመስል ፍጥነት ይጓዛሉ ብለዋል፡፡

በአትላንቲክ ዳርቻ ላይ ሥልጠና የሚሰጡ አብራሪዎች "በየቀኑ ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያህል" ተመሳሳይ ነገር ማየታቸውን ግሬቭስ ተናግረዋል፡፡

የቀድሞው የአሜሪካ የፀረ-ደህንነት ወኪል ሉዊስ ኤሊዞንዶ ባለፈው ወር ለኢቢሲ ኒውስ እንደገለፁት የሚታዩት አንዳንድ ቁሶች "በእኛ እጅ ከሚገኙት ነገሮች ይበልጣሉ" ብለዋል፡፡

"ጥያቄው ምንድን ናቸው የሚለው ነው? ዋናው ነገር እኛ አናውቅም ማለት ነው" ብለዋል፡፡

የሃገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት ሚያዝያ "ያልተገለፁ የአየር ላይ ቁሶችን" የሚያሳዩ ሦስት ምስጢራዊ ቪዲዮዎችን ይፋ አደረገ፡፡

ሚንስትሩ ቀደም ሲል በ 2007 እና በ 2017 የተለቀቀው "ቪዲዮው እውነት ስለመሆኑ በሕዝብ ዘንድ የሚስተዋሉ ማንኛውንም የተሳሳቱ አመለካከቶችን ለማጣራት እፈልጋለሁ" ብሏል፡፡