ለ12ኛ ጊዜ ከእስር ቤት ያመለጠው ሴኔጋላዊ ታራሚ ተያዘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በተደጋጋሚ በመታሰርና ከእስር ቤት በማምለጥ የሚታወቀው ባየ ሞዱ ፎል የተባለ ሴኔጋላዊ ታራሚ ለአስራ ሁለተኛ ጊዜ አምልጦ መያዙ ተዘግቧል።
ግለሰቡ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ከመዲናዋ ዳካር ከሚገኝ እስር ቤት ነበር ያመለጠው።
ከእስር ቤት ካመለጠ በኋላ ጎረቤት አገር ማሊ ድንበር አካባቢ በምትገኘው ሙሳላ በምትባል ግዛት በቁጥጥር ስር መዋሉን የሴኔጋል ጦር ቃለ አቀባይ ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
የ32 አመቱ ታራሚ በተደጋጋሚ ከእስር ቤት በተደጋጋሚ በማምለጡም " አምላጩ ጀግና" የሚል ቅጥያ ስም ተሰጥቶታል።
ታራሚው ለአገሪቱ ሚዲያ በያዝነው ሳምንት ሰኞ እንደተናገረው ያመለጠው የዋስ መብቱ በመከልከልከሉና የፍትህ ሂደቱ በመራዘሙ ተሰላችቶ መሆኑን ነው።
ታራሚው ከእስር ቤት እንዴት እንዳመለጠም በዝርዝር አስረድቷል። እሱ እንዳለው ከክፍሉ በአየር ማናፈሻው በኩል ተንጠላጥሎ እንደገባና በጣራው ላይ እየተረማመመደ ሄዶ በመጨረሻም በገመድ የእስር ቤቱን ግንብ ወርዶ ማምለጥ እንደቻለ ነው።
ግለሰቡ በተደጋጋሚ እንዲህ የማምለጡ ሁኔታ ጥያቄን አጭሯል። የአካባቢው ባለስልጣናት ይህ ግለሰብ ከእስር ቤቱ ውስጥ አጋዥ ሳይኖረው አይቀርም በሚልም ምርመራ መክፈታቸውን አስታውቀዋል።








