ፌስቡክ በቻይና ቢሮውን ሊከፍት ነው

የፌስቡክ መስራች የሆነው ማርክዙከንበርግ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፌስቡክ ድረገፁ እንዳይታይ በታገደበት ቻይና ቢሮ መክፈት የሚያስችለውን ፈቃድ አገኘ። ድርጅቱ እንዳለው ቢሮው ቻይናዊያን የዴቬሎፐሮችንና የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማገዝ እንዲሁም መነሻ የሚሆናቸውን ነገር ለማመቻቸት ያገለግላል።

የቢሮው መከፈት እውን ከሆነ ፌስቡክ በቻይና እግሩን ሲያስገባ የመጀመሪያው ይሆናል።

ነገር ግን ከቻይና መንግሥት ድረገፅ ላይ የምዝገባ ፍቃዱ ዝርዝር ስለተነሳ ትንሽ ወሰብሰብ ያለ ነገር እንደሚኖር ኒው ዮርክ ታይምስ ጠርጥሯል።

ቻይና በአለማችን ትልቋ የማህበራዊ ሚዲያ ገበያ ብትሆንም እንደ ትዊተር፣ ፌስቡክ እና ዩቲዩብ ያሉ ድረገፆች በሀገሪቱ ስለተዘጉ መጠቀም አይቻልም።

ከዛ ይልቅ ለቻይናውያን ብቻ ተብለው በሀገሬው የተሰሩ እና በቻይና መንግስት ቁጥጥር የሚደረግባቸው እንደ ዌይቦ፣ ሬይነርን እና ዩኩት የሀገሬውን የማህበራዊ ድረገፅ ፍላጎት ለማገልገል ጥቅም ላይ ውለዋል።

የፌስቡክ መስራች የሆነው ማርክዙከንበርግ በተደጋጋሚ የቻይና ባለስልጣናትን ለማማለል ማንድሪን እስከመማር ድረስ ደርሷል።

የፌስቡክ አቻ በደቡባዊ ቻይናዋ ከተማ ሀንግዡዋ የተመዘገበ ሲሆን የ30 ሚሊየን ፓውንድ ካፒታል አለው።