የፌስቡክ ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፌስቡክ የተጠቃሚዎችን ግላዊ መረጃ አሳልፎ በመስጠት ከተከሰሰ በኋላ ይፋ የሆነ ሪፖርት እንዳመለከተው የሩብ ዓመት ገቢው በ50 በመቶ ከፍ ብሏል።
ኩባንያው እንደገለፀው በአውሮፓውያኑ ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ገቢው 11.9 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አመልክቷል። ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ያገኘው ገቢ 8 ቢሊዮን ዶላር ነበር።
የፌስቡክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ማርክ ዙከርበርግ ስለተገኘው ገቢ ሲናገር "ምንም እንኳን ከባድ ተግዳሮት የገጠመን ቢሆንም፤ ለዓመቱ ሥራችን መልካም ጅማሬ ነው።"
ጨምሮም ተቋሙ ያለበትን ሃላፊነት በስፋት እየመረመረ መሆኑን አሳውቋል።
ይህ ፌስቡክ በሦስት ወራት ውስጥ ያስመዘገበው ከፍተኛ ገቢ የባለፈው ዓመት ገቢውን እንዲያድግ አድርጎታል።
ፌስቡክ በመጋቢት ወር ላይ የፖለቲካ አማካሪ ተቋም ከሆነው ኬምብሪጅ አናሊቲካ ከተባለው ድርጅት ጋር በተያያዘ የተጠቃሚዎችን መረጃ አሳልፎ ሰጥቷል በሚል ከፍ ያለ ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ነበር ።
በዚህም ፌስቡክ 87 ሚሊዮን የሚደርሱ ተጠቃሚዎቹን ግላዊ መረጃ ተገቢ ባልሆነ መንገድ አሳልፎ መስጠቱን አምኗል።
የፌስቡክ መስራችና ባለቤት ማርክ ዙከርበርግ እንዳለውም "ያለብንን ሃላፊነት ሰፋ አድርገን እየተመለከትነው ሲሆን የምናቀርበው አገልግሎትም ለመልካም ነገር መዋሉን ለማረጋገጥ የሚያስፈልገውን እያደረግን ነው።
"በተጨማሪም ሰዎችን ለማገናኘት፣ ማሕበረሰባችንን ለማጠናከርና ዓለምን ለማቀራረብ አዳዲስ ዘዴዎችን ማፈላላጋችንን እንቀጥላለን" ብሏል።
ፌስቡክ እንደሚለው በመጋቢት ወር ላይ የየእለቱ አማካይ መደበኛ የተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ 1.5 ቢሊዮን ደርሷል። ይህም ከባለፈው ዓመት በ13 በመቶ ጨምሯል።
የመጋቢት ወር አማካይ ወርሃዊ መደበኛ ተጠቃሚዎች ቁጥር 2.2 ቢሊዮን ደርሶ በ13 በመቶ ከፍ ብሏል። የፌስቡክ ሰራተኞች ቁጥርም በ48 በመቶ አድጎ 27742 ደርሷል።












