ማኅበራዊ ሚዲያን ከጥላቻ መልዕክቶች የማጽዳት ዘመቻ

ፌስቡክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከሳምንታት በፊት የተፈጸመውን የድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በአዲስ አበባና በአንዳንድ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶችና ባጋጠሙ ግጭቶች ሳቢያ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከፍተኛ መጠን የለው ንብረት በመውደሙ በርካቶች ቤት ንበረታቸውን አጥተው ለችግር ተጋልጠዋል።

ታዲያ ለእዚህና ለሌሎች መሰል ጥቃቶች በማኅበራዊ ሚዲያና በሌሎች መደበኛ መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚሰራጩ ጥላቻንና ጥቃትን የሚያበረታቱ መልዕክቶች አስተዋጽኦ አላቸው ያሉ በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን እነዚህን ድርጊቶች ለማስቆም አንድ ኔትወርክ አቋቁመዋል።

ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆነውና የዚህ እንቅስቃሴ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ነአምን ዘለቀ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኔትወርኩ በተለያዩ ዘርፎች የተዋቀሩ ኮሚቴዎችን የያዘ ነው። ኮሚቴዎቹ የሕግ፣ የሚዲያና ዲፕሎማሲ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያ ዘርፍ የተዋቀሩ ናቸው።

ይህ ኔትወርክ በአሜሪካ፣ በካናዳና በአውሮፓ አገራት ውስጥ ያሉ በርካታ የፖለቲካ ሰዎች፣ ምሁራን፣ አክቲቪስቶች፣ ሲቪክ ማኅበረቦች የተሰባሰቡበት እንደሆነም አቶ ነአምን ጨምረው አስረድተዋል።

ኔትወርኩ በአገር ውስጥ መረጋጋት እንዲመጣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፤ ወንጀለኞችና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ ለሕግ እንዲቀርቡ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን አስተባባሪው ገልፀውልናል።

የማኅበራዊ ሚዲያው ኮሚቴ 'ተጋምደናል' (Interunited) የሚል ዘመቻ የጀመረ ሲሆን የጥላቻ ንግግሮችን በመሰብሰብና ሪፖርት በማድረግ እንዲሁም ባሉት ገፆች አማካይነትም መልዕክቶችን የማስተላለፍ ሥራ ይሰራል።

የሕግ ኮሚቴውም እንዲህ ዓይነት መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ መገናኛ ብዙሃንና ግለሰቦች ባሉበት አገር ውስጥ ተጠያቂ እንዲሆኑና ለሕግ እንዲቀርቡ የሚሰራ ሲሆን መረጃዎችን በመሰብሰብ በማደራጀት የሚሰራው በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ቡድኑ ይደገፋል ብለዋል።

እስካሁንም በኔትወርኩ በተከፈተው የኢሜል አድራሻ በርካታ ማስረጃዎች እንደደረሷቸው አክለዋል።

በሌላ በኩል "ከዚህ ቀደም በተለያዩ የዓለም አቀፍ ሚዲያዎች በተዛባ መልኩ ዘገባዎች ተሰርተዋል" የሚሉት አቶ ነአምን፤ የሚዲያና ዲፕሎማሲ ኮሚቴው ማስረጃዎችን በማሰባሰብ የማስተካከያ እርምጃዎች እንዲደረጉ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

አቶ ነአምን "ከአገር ውጭ ሆነው በሕዝቡ ውስጥ መረጋጋትና ሰላም እንዳይኖር፤ ከባድ የጥላቻና ሕዝብን ከሕዝብ የሚያጋጩ መልዕክቶችን የሚያሰራጩ ናቸው" ያሏቸው አካላት በአንድ ወገን ያሉ ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ ብሔሮችን እንወክላለን የሚሉ መሆናቸውንም ይናገራሉ።

በተለያየ ጊዜ በአገሪቱ ተመሳሳይ ክስተቶች መፈጠራቸውን በማስተዋስ፤ አሁን ወደዚህ እንቅስቃሴ እንዲገቡ የገፋቸውን ምክንያት "የመጣው አደጋ በመግዘፉና ሕዝብን ለአመፅና ለሁከት የሚያነሳሱ መልዕክቶች በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በተደራጀ መልኩ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በማየታችን ነው" ሲሉ አመልክተዋል።

ኔትወርኩ ወገን ሳይለይ በሁሉም ብሔር ፅንፈኞች የሚደረጉ ጥላቻና፣ ግጭትና ጥቃትን የሚቀሰቅሱ እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ እንዲገነዘብ ማድረግ እና የጥላቻ ንግግሮችን የሚያራምዱ ሚዲያዎችና ግለሰቦችን በሕግ መጠየቅ የኔትወርኩ የአጭር ጊዜ እቅድ መሆኑን የገለፁት አቶ ነአምን፤ ወደ ፊትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

አቶ ነአምን ዘለቀ እና አቶ ዮሐንስ ሞላ
የምስሉ መግለጫ, አቶ ነአምን ዘለቀ እና አቶ ዮሐንስ ሞላ

"እኔም ሳፀዳ፤ ሌላውም ሲያፀዳ፤ አብረን እንፀዳለን"

በሌላ በኩል በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የጥላቻ ንግግሮችና ጥቃት ቀስቃሽ መልዕክቶችን ለፌስቡክ ሪፖርት የሚያደርግ እንቅስቃሴ እየተካሄደ ነው።

ይህንን እንቅስቃሴ የጀመረው ገጣሚና የማኅበራዊ ለውጥ አራማጁ ዮሐንስ ሞላ ነው። ከ10 ዓመታት በላይ የፌስቡክ ተጠቃሚ እንደሆነ የሚናገረው ዮሐንስ፤ ከዚህ ቀደምም እንዲህ በዘመቻ አይጀምረው እንጂ ከፌስቡክ ሕግ ጋር የሚጣረሱ መልዕክቶችን ሲመለከት ሪፖርት እንደሚያደርግ ይናገራል።

ዮሐንስ እንደሚለው ብሔር ተኮር ብቻ ሳይሆን ጾታዊ ትንኮሳ፣ ዛቻን፣ የህፃናት ጥቃትን እንዲሁም ሌሎች መልዕክቶችን የሚያስተላልፉ ፅሁፎችን፣ ፎቶዎችንና ቪዲዎችን ሲመለከት ለፌስቡክ የማሳወቅ ልምድ አለው።

"የፌስቡክ አካውንት መክፈታቸውን እንጂ ማህበራዊ መድረኩን ሲቀላቀሉ፤ ሕጉ ምን እንደሆነ የማያውቁት ጥቂት አይደሉም" የሚለው ዮሐንስ፤ በዚህም የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮችን ባልተገባ መልኩ ጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሆነ ያስረዳል ይላል።

ከሰሞኑ ያጋጠመውን አለመረጋጋት ተከትሎም ይህንን በግሉ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ወደ ዘመቻ በመለወጥ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ በማሰብ እንቅስቃሴ መጀመሩን ይገልጻል።

"ፌስቡክ የፌስቡክ አካውንቶችን የሚዘጋው አሊያም የተላለፉ ይዘቶችን ከገፁ ላይ የሚያወርደው፤ የራሱን ሕግ ተከትሎ እንጂ ሪፖርት ባደረገ ሰው ብዛት አይደለም" የሚለው ዮሐንስ፤ ዘመቻውን መክፈቱ ሰዎችን ለማስተማርና እነርሱም ይህንን ማድረግ እንዲችሉ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው ብሏል።

ለእንደዚህ አይነት ሁከቶች የጥላቻ ንግግሮችና የጥቃት ቅስቀሳዎች ከፍተኛ የሆነ ድርሻ አላቸው በማለትም "ቀደም ብለን ብንጀምር፤ ምን አልባት ይሄ ቀን አይመጣም ነበር፤ ባለማድረጌም ቆጭቶኛል" ይላል።

ዮሐንስ አሁን ላይ 'መንጥር' (Network Against Hate Speech) የሚል ኔትወርክ ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ አመልክቶ፤ ኔትወርኩ የቋንቋ፣ የብሔር፣ የፖለቲካ አቋም እንዲሁም የሙያ ስብጥር ያላቸው ሰዎች የተሳተፉበት እንደሆነም ያስረዳል።

"ዘመቻው በአንድ ወገን ላይ ብቻ ያተኮረ ነው" የሚሉ ክሶች እንደሚቀርቡ ያነሳንለት ዮሐንስ፤ "በእኔ ፍላጎት ሳይሆን ፌስቡክ ይዘቱን ተመልክቶ በራሱ ሕግ ነው እርምጃ የሚወስደው" በማለት፤ ከየትኛውም በኩል የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮችንና የጥቃት መልዕክቶችን ሪፖርት ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይል ያስረዳል።

ዮሐንስ አክሎም ይህን የሚሉ ወገኖችም በእነርሱ ገፅ የሚያዩት መሰል መልዕክቶች ካሉ ሪፖርት ያድርጉ በማለት ዋናው ሕግ መከበሩ በመሆኑ "እኔም ያገኘሁትን ሳፀዳ፤ ሌላውም ሲያፀዳ፤ አብረን እንፀዳለን" ብሏል።

እስካሁን ባደረጉት እንቅስቃሴዎችም ውጤት ማየታቸውንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ዮሐንስ ይናገራል።

ይህ የበጎ ፈቃደኞች ስብስብ በፌስቡክ ላይ የሚተላለፉ የጥላቻ ንግግሮችን ብቻ ሳይሆን እንደ ዩቲዩብና ትዊተር ባሉ ሌሎች የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች ላይ የሚተላለፉትንም መሰል መልዕክቶችን ሪፖርት ያደርጋል።