የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንቶች በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀው አዲሶች ተሾሙ

አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ
የምስሉ መግለጫ, አቶ ቴዎድሮስ ምህረት እና ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው በፈቃዳቸው ሥራ ለመልቀቅ ያረቡትን ጥያቄ ተቀብሎ በምትካቸው አዲስ ፕሬዝዳንቶችን ሾመ። ላለፉት አራት ዓመታት ያህል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ በፈቃዳቸው ሥራቸውን ለመልቀቅ ለምክር ቤቱ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው አዲስ ፕሬዝዳንት በምትካቸው የተሾመው።

በዚህም መሠረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ትምህርት ረዳት ፕሮፌሰር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ቦታ ተተክተው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው እንዲሰሩ ተሹመዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ ጥር 09/2015 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ባደረገው መደበኛ ስብሰባው፤ የወ/ሮ መአዛን መልቀቂያ ተቀብሎ የአቶ ቴዎድሮስን ሹመት ያፀደቀው በሦስት ድምጸ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምጽ ነው።

አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በአገሪቱ ዋነኛ ዩኒቨርስቲ ውስጥ በረዳት ፕሮፌሰርነት ደረጃ መምህር ሆነው ከመስራታቸው በተጨማሪ፣ በተለያዩ ተቋማት ውስጥ የሕግ ባለሙያ እና አማካሪ ሆነው መሥራታቸው ተገልጿል።

በተመሳሳይ የወይዘሮ መአዛ አሸናፊ ምክትል ሆነው በአንድ ላይ ተሹመው ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ ሰሎሞን አረዳም የሥራ መልቀቂያቸውን በማቅረባቸው፣ ምክር ቤቱ ወይዘሮ አበባ እምቢአለን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ሾሟል።

የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ አበባ እምቢአለ፣ እስከ ተሾሙበት ጊዘ ድረስ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ነበሩ።

ከዚያ ቀደም ብሎ ደግሞ በተለያዩ የክልል እና የፌደራል መንግሥቱ ተቋማት ውስጥ በዳኝነት እና በዐቃቤ ሕግነት የዓመታት ልምድ እንዳላቸው ተገልጿል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት አዲሶቹ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ቃለ መሐላ ፈጽመው ኃላፊነቱን ተረክበዋል።

ላለፉት አራት ዓመታት የፌደራሉን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፕሬዝዳንትነት እና በምክትል ፕሬዝዳንትነት የመሩት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ እና አቶ ሰሎሞን አረዳ በአንድ ላይ ሥራቸውን በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ምክንያታቸው ምን እንደሆነ አልተገለጸም።

ሁለቱ ባለሥልጣናት የሥራ መልቀቂያቸውን ማቅረባቸውን በተመለከተ ቢቢሲ ከአንድ ወር በፊት መረጃውን ቢያገኝም ከሁለቱም በኩል ማስተባበያም ሆነ ማረጋገጫ ሳያገኝ ቆይቶ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ቁልፍ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ በርካታ ሴቶችን በሾሙበት ጊዜ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊ ታዋቂ የሕግ ባለሙያ ናቸው።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን በመምራት የሚታወቁት ወይዘሮ መአዛ ከማኅበሩ ጋር በመሆን የሕግ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ ዘመቻ ከማካሄድ በተጨማሪ አቅመ ደካማ ለሆኑ ሴቶች ነፃ የሕግ ድጋፍ እና ጥበቃ በመስጠት አገልግለዋል።

በተጨማሪም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን በሴቶች እና በህፃናት መብቶች በሕግ በአማካሪነት ከስድስት ዓመታት በላይ ሰርተዋል።