‘የተሸኙት’ አራቱ ሚኒስትሮች እነ ማን ናቸው? ወደ የትስ ያመሩ ይሆን?

አቶ ተፈሪ ፍቅሬ፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ፣ አቶ ታከለ ኡማ እና አቶ ኡመር ሁሴን

የፎቶው ባለመብት, PM Office

የምስሉ መግለጫ, አቶ ተፈሪ ፍቅሬ፣ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ፣ አቶ ታከለ ኡማ እና አቶ ኡመር ሁሴን

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ከፍተኛ የሚኒስትርነት ኃላፊነት ላይ ሲያገለግሉ የነበሩ አራት አባላቱን በክብር ማሰናበቱን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ላይ አስታወቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የአገሪቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ጥር 06/2015 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን ካደረገ በኋላ ነው አራት ሚኒስትሮች መሸኘታቸውን የገለጸው።

በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ አቶ ታከለ ኡማ፣ አቶ ኡመር ሁሴን እና አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ከምክር ቤቱ አባልነት “በክብር” መሸኘታቸውን አሳውቋል።

ሚኒስትሮቹ የካቢኔ አባል የሆኑት በያዙት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ኃላፊነት ምክንያት በመሆኑ፣ ከምክር ቤቱ ከተሸኙ ሲያገለግሉበት የነበረበት የሚኒስትርነት ሥልጣንም እንዳበቃ አመላካች ነው።

ነገር ግን እነዚህ በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ኃላፊነት ላይ የቆዩት ግለሰቦች ለምን እንደተሸኙ እና በቀጣይ ወደየት እንደሚያቀኑ ወይም እንደሚመደቡ ያለው ነገር የለም።

ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ለአራት ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን፣ ከዚያ ቀደም ብሎም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ እና በሌሎችም የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ አገልግለዋል።

አቶ ታከለ ኡማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ በምክትል ከንቲባነት ተሹመው አዲስ አበባ ከተማን በከንቲባነት ለዓመታት የመሩ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ የማዕድን ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።

አቶ ኡመር ሁሴን በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ ያገለገሉ ሲሆን ባለፉት ዓመታትም የግብርና ሚኒስቴርን በመምራት የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባል ሆነው ቆይተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሌላኛው ብዙም የማይታወቁት የሚኒስትሮች ምክር ቤት መሸኘታቸውን የገለጸው ሚኒስትር አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩ ናቸው።

አቶ ተፈሪ ይህንን ኃላፊነት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ነበር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተሹመው የተረከቡት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ሌሎችም የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በተገኙበት መደረጉ በተገለጸው የአራቱ ሚኒስትሮች ሽኝት ላይ ባልደረቦቻቸው “ቀጣይ ጉዟቸው ስኬታማ እንዲሆንላቸው” እንደተመኙ ከመግለጽ ውጪ ተጨማሪ ዝርዝር አልተሰጠም።

ከሚኒስትሮች ምክር ቤት ከተሸኙት አራት ሚኒስትሮች መካከል የሁለቱ በአምባሳደርነት ተሹመው በውጪ አገራት እንደሚመደቡ ይጠበቃል።

ለዚህም አቶ ኡመር ሁሴን እና አቶ ተፈሪ ፍቅሬ ባለፈው ታኅሣሥ 21/2015 ዓ.ም. በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደርነት ከተሰጣቸው ተሿሚዎች መካከል መካተታቸው ቀጣይ ምደባቸው ወደ ዲፕሎማሲው ሊሆን እንደሚችል አመላካች ነው።

በከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ልምድ ያዳበሩት ወ/ሮ ዳግማዊት እና አቶ ታከለ ኡማ ግን ቀጣይ መድረሻቸው የት ሊሆን እንደሚችል እሳካሁን የተገለጸ ነገር የለም። ቢቢሲ ለማጣራት ያደረገው ሙከራም አልተሳካለትም።

ሽኝቱን ተከትሎ ወ/ሮ ዳግማዊት በትዊተር ገጻቸው ላይ “የምወዳት አገሬ ኢትዮጵያን እና ሕዝቤን በታላቅ ኃላፊነት ለማገልገል በመታደሌ ደስታዬ ወደር የለውም” በማለት በሚኒስትርነት በማገልግላቸው ክብር እንደሚሰማቸው አስፍረዋል።

ኢንጂኒየር ታከለ ኡማም ኢትዮጵያን በማገለግላቸው ጥልቅ ክብር እንደሚሰማቸው ገልጸው “ለዓመታት ያልተቋረጠ ድጋፍ፣ ማበረታታት እና ምክር” ሰጥተውኛል ያሏቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩን አመስግነዋል።