የአፍሪማ የሙዚቃ ሽልማት ለካሥማሠ እና ለጉቱ የፈጠረላቸው ስሜት እና ተስፋ

ካሥማሠ እና ጉቱ

የፎቶው ባለመብት, SM

የምስሉ መግለጫ, ካሥማሠ እና ጉቱ

ዳካር ሴኔጋል ውስጥ በተካሄደው በስምንተኛው የመላው አፍሪካ የሙዚቃ ሽልማት (አፍሪማ) ውድድር ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ባለሙያዎች በዕጩነት ቀርበው የተወሰኑት ሽልማቱን አግኝተዋል።

ከእነዚህም መካከል ወጣቶቹ የሙዚቃ ባለሙያዎች ካሥማሠ እና ጉቱ አበራ ይጠቀሳሉ።

ሁለቱም ወጣት ሙዚቀኞች በአፍሪማ ሽልማት ላይ በተወዳደሩበት ዘርፍ አሸናፊ በመሆናቸው በጣም ደስታ እንደተሰማቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሙዚቃ ሥራው ሽልማት ሲያገኝ የመጀመርያው መሆኑን የተናገረው ካሥማሠ የአፍሪማ ሽልማት ትልቅ ደስታ እንደፈጠረለት ጠቅሶ “በባህሪዬ አብዝቼ መደሰት የምወድ ሰው አይደለሁም፤ በአንድ ቀን ተደስቼ አንዳያልቅብኝ ያዝ አድርጌ፣ እየቆጠብኩ ለሌላ ሥራ እንዲሆነኝ እደሰታለሁ” ብሏል።

ጨምሮም ካሥማሠ ሽልማቱ የተካሄደበት ሴኔጋል አለመገኘቱን ገልጾ፤ ዋናው ሁሌም የሚሰራው አድማጮቹን እና አድናቂዎቹን ለማስደሰት በመሆኑ እነርሱ ሲደሰቱ በመመልከቱ የተሰማውን ደስታ ገልጿል።

ነዋሪነቱ አውሮፓ የሆነው ጉቱ አበራ ባለፉት ዓመታት በኦሮምኛ ባቀረባቸው ሙዚቃዎቹ እና የሙዚቃ ቪዲዮዎቹ በአገር ውስጥ አድናቆትን ያገኘው ሌላኛው ወጣት የሙዚቃ ባለሙያ ነው።

በአፍሪካ የሙዚቃ ሽልማት ላይ ‘ዴሚ’ በሚለው ሙዚቃ በማሸነፉ ትልቅ ደስታ እንደተሰማው ለቢቢሲ ገልጿል። “ለሥራዬ እና ለጥረቴ እንደዚህ በአፍሪካ ደረጃ ያለ ተቋም እውቅና ሲሰጠኝ ታላቅ ደስታ ነው የተሰማኝ” ብሏል።

ካሥማሠ በበኩሉ ስለውድድሩ ሲናገር ከዚህ በፊት ሲያደምጣቸው እና ሲያደንቃቸው ከነበሩ ደምጻውያን ጋር በአንድ ዘርፍ መመደቡን በማስታወስ፣ ከእነሱ ጋር ተወዳድሮ ማሸነፍ በመቻሉ የተለየ ስሜት ፈጥሮበታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የካሥማሠ ሥራ በውድድሩ ላይ በምርጥ የምሥራቅ አፍሪካ አርቲስት፣ በምርጥ የአፍሪካ አነቃቂ ሙዚቃ እንዲሁም በምርጥ የአፍሪካ ሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍ የሙዚቃው ዳይሬክተር ማራናታ ታጭቶ ነበር።

ድምጻዊ ካስማሠ ዕጩ በሆነባቸው ሦስት ዘርፎች ሁሉ ታጭቶ የነበረው ‘ሰዋሰው’ በተሰኘው የሙዚቃ ሥራው ሲሆን አሸንፋለሁ ብሎ ጠብቆ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጿል።

ጉቱ አበራ በምርጥ የአፍሪካ የጃዝ ሙዚቃ ሥራ ለሽልማት ስላበቃው ‘ዴሚ’ የተሰኘው ሙዚቃው ሲናገር “የከሚሴ እና የወሎን ምት (ሪትም) በማቀላቀል” የተሰራ መሆኑን እና የሙዚቃ ቪዲዮው መቼት ደግሞ ከረዩ አካባቢ መሰራቱን ጠቅሷል።

“ዜማው ደግሞ በአብዛኛው ጃዝ በሚባለው የሙዚቃ ስልት የተሰራ ነው። የጃዝ የሙዚቃ ስልት ውስብስብ ከመሆኑ አንጻር የሙዚቃ ሥራችን በዚህ ስልት ውስጥ ተካቶ በማሸነፉ ትልቅ ደስታ ነው የተሰማኝ።

“በአፋን ኦሮሞ የሙዚቃ ታሪክም፣ የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ ለዚህ ሽልማት ሲታጭም ሆነ ሲያሸንፍም ይህ የመጀሪያው” መሆኑ የተለየ ደስታን ፈጥሮለታል።

ካሥማሠን ለሽልማት ያበቃው ‘ሰዋሰው’ የተሰኘው የሙዚቃ ሥራው እስካሁን ድረስ በተለያየ የሙዚቃ ሥራዎቹ ውስጥ ያነሳቸውን ሃሳቦች ጠቅለል አድርጎ ያቀረበበት መሆኑን በማንሳት “ዓለም አንድ እንደሆነች። ሁላችንም ወንድም እና እህት እንደሆንን የሚያሳይ ስለሆነ ፍቅርን ለመግለጽ ያለው ጉልበት ታይቶ ለአሸናፊነት የበቃ ይመስለኛል” ብሏል።

ይህ የሙዚቃ ሥራው የደቡብ ኦሞ የዳሰነች ማኅበረሰብ የሚኖርበትን አካባቢ በጎበኘበት ጊዜ የሙዚቃው እና የሙዚቃው ቪዲዮ ሃሳብ መወለዱን ካሥማሠ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የዳሰነች ማኅበረሰብ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሱ የሚኖሩ መሆናቸውን በመጥቀስ፣ የእርሱም ሙዚቃ ድንበር ሳይገድበው በሁሉም አድማጭ ዘንድ በአንድ ልብ አንዲሰማ ፍላጎት ኖሮት እንደሰራው ገልጿል።

በሙዚቃ ሥራዎቹ አድናቆትን እያገኘ የመጣው ወጣቱ ድምጻዊ ጉቱ፣ የአፍሪማ ሽልማት የበለጠ በሥራው እንዲተጋ እንደሚያደርገው በመግለጽ፣ ሌላ እያዘጋጀው ያለ ሥራም እንዳለ አመልክቷል።

“ሙዚቃ ሁሌም የምሰራው ነገር ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ለየት ያለ አዲስ ነጠላ ዜማ ይዤ እመጣለሁ” የሚለው ጉቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥም ሙሉ አልበም ለአድማጮቹ ለማቅረብ ተስፋ እንደሚያደርግ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የአፍሪማ ሽልማት አሸናፊ መሆኑ ሌላ ሰፊ የሙዚቃ ሥራ ዕድል እንደሚፈጥርለት የሚናገረው ካሥማሠ፣ በሙዚቃ ሥራው ከኢትዮጵያ ባሻገር ወዳለው የሙዚቃ አድማጭ ለመድረስ ፍላጎት እንዳለው ይናገራል።

“ሽልማቱ ወደ ሰፊው የአፍሪካ ሙዚቃ አድማጭ ብሎም ወደ ቀሪው ዓለም ለመድረስ ከሌሎች የአፍሪካ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር አብሮ የመስራት ዕድል ይዞ ይመጣል” ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግም ካሥማሠ ለቢቢሲ ተናግሯል።