በሊቢያ ስደተኞችን አሳግተው "2.1 ቢሊዮን ብር ሰብስበዋል" የተባሉ 28 ሰዎች ክስ ተመሠረተባቸው

የፎቶው ባለመብት, The Federal High Court of Ethiopia
የፌደራል ዐቃቤ ሕግ፤ ስደተኞችን "በሕገ ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ድንበር" ካስወጡ በኋላ ሊቢያ ውስጥ ታግተው ገንዘብ እንዲጠየቅባቸው እና "እጅግ አሰቃቂ" በሆነ መንገድ እንዲሰቃዩ አድርገዋል ባላቸው 28 ሰዎች ላይ ክስ መመሥረቱን አስታወቀ።
በተከሳሾቹ አማካኝነት ከተዘዋወሩት ስደተኞች ውስጥ የሁለቱ ሕይወት እንዳለፈ እና 15 ሰዎች "የደረሱበት እንዳልታወቀም" ተገልጿል። ክስ ከተመሠረተባቸው ተጠርጣሪዎች ውስጥ በስምንቱ ብቻ የተሰበሰበው ገንዘብ "2.1 ቢሊዮን ብር" እንደሆነም ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ፍትሕ ሚኒስቴር ዛሬ ማክሰኞ ጥር 19/2018 ዓ.ም. ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ይህ ክስ የተመሠረተው "በሊቢያ መስመር በሰው ልጅ የሚነግዱ ዋና ዋና አዘዋዋሪዎች ላይ ትኩረት አድርጎ" የተካሄደን ምርመራ መነሻ በማድረግ ነው።
በዚህ ምርመራ ላይ ተሳትፈዋል ከተባሉ የፌደራል ተቋማት መካከል ፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት እንዲሁም የፋይናንስ መረጃ ደኅንነት ይገኙበታል።
ዐቃቤ ሕግ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመሠረተው ክስ፤ ግለሰቦቹ "የተደራጀ የወንጀል ቡድን አደራጅተው" እንዲሁም "በስራቸው ሌሎች አነስተኛ ሥራ የሚሠሩ ደላሎችን በመመልመል" ስደተኞችን ሲያዘዋውሩ እንደቆዩ እንደሚያስረዳ ተገልጿል።
ፍትሕ ሚኒስቴር ያወጣው መረጃ "ተከሳሾቹ በባሕር ዳር እና ጎንደር አካባቢ ሰዎችን ወደ ሱዳን ድንበር የሚያጓጉዙ ተቀጣሪዎችን በማዘጋጀት ኢ-መደበኛ በሆነ መንገድ ከሀገር ሲያስወጡ ቆይተዋል" ይላል።
ስደተኞቹን "በሕገ-ወጥ መንገድ ከኢትዮጵያ ድንበር ካስወጡ" በኋላ "ሊቢያ ወስደው በመጋዘኖች ሲያጉሩ" እንደነበርም መረጃው ያትታል።
ስደተኞች የሚቆዩባቸው መጋዘኖች "ተከሳሾች እና ግብረ አበሮቻቸው" የሚያስተዳድሯቸው እንደሆነ የሚጠቅሰው መረጃው፤ "በሕይወት ለመቆየት ብቻ የሚበቃቸውን ምግብ እንዲያገኙ አድርገው" እንደያዟቸውም ይገልጻል።
የስደተኞቹ ቤተሰቦች "ከፍተኛ ገንዘብ" እንዲከፍሉ ሲጠይቁ እንደነበር እና ገንዘቡ እስኪከፈል ድረስም ሰዎቹን "በዕዳ መያዣነት ሲይዙ ቆይተዋል" በሚል ተከስሰዋል።
"በፍጥነት ገንዘብ" ያልተከፈለላቸው ስደተኞችን "እጅግ አሰቃቂ በሆነ ሁኔታ እየደበደቡ እና እያሰቃዩ በተንቀሳቃሽ ምሥል በመቅረፅ ወደ ቤተሰቦቻቸው በመላክ ገንዘብ እንዲከፈል ጫና ሲያደርጉ ቆይተዋል" ሲሉም ወንጅሏል።
ክስ የተመሠረተባቸው ሰዎች በአጠቃላይ 1,800 ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ እንዳዘዋወሩ የገለጸው ፍትሕ ሚኒስቴር፤ ከእነዚህ ውስጥ የ85 ስደተኞች ማንነት እንደተለየ ገልጿል።
ማንነታቸው ከታወቁት ሰዎች መካከልም ሁለት ሕይወታቸው ማለፉ እና ሁለት ሰዎች ደግሞ "በድብደባ ምክንያት ለበሽታ" መዳረጋቸው ተረጋግጧል ብሏል። አስራ አምስት ሰዎች ደግሞ "የደረሱበት ያልታወቀ" እንደሆነ መረጋገጡን አስታውቋል።
ዐቃቤ ሕግ የመሠረተው ክስ እንደሚያስረዳው፤ ታጋቾችን ለማስፈታት የሚከፈለው ገንዘብ ሲሰበሰብ የነበረው "ስምንት ተከሳሾች እና ሌሎች ግብረ አበሮቻቸውን የባንክ ሂሳብ በመጠቀም" ነው። "ስምንት ገንዘብ ሰብሳቢዎች አማካኝነት ብቻ ብር 2,160,863,361 ብር መሰብሰባቸውን የዐቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ያሳያል" ሲል ፍትሕ ሚኒስቴር ገልጿል።
የተሰበሰበውን ገንዘብ "በፍጠነት" ሲጠቀሙበት እና "ለግብረአበሮቻቸው ክፍያ" ሲፈጽሙበት ነበር ያለው መረጃው፤ ከ"ዝውውር ወጪ የተረፈው" ቀሪው ገንዘብን በውጪ አገር እና አገር ውስጥ ሀብት ተፈርቶበት እንደተገኘም ገልጿል።
ዐቃቤ ሕግ በቁጥጥር ስር በዋሉ 28 ተጠርጣሪዎች ላይ ሦስት ክሶችን እንደመሠረተ ተገልጿል። የመጀመሪያው ክስ "የከባድ በሰው ልጅ መነገድ ወንጀል" ሲሆን "በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ" ድርጊትም ከክሶቹ መካከል ነው።
ሦስተኛው ክስ "ሕገ ወጥ ሐዋላ በመሥራት ሀብት የማሸሽ ወንጀል" እንደሆነ ተገልጿል። ተከሳሾቹ ያፈሯቸው ቤቶች፣ ተሽከርካሪዎች እና ከ71 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ገንዘብ "ለማካካሻነት" እንደታገደም ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውቋል።















