ከኢትዮጵያ ያመለጠው በሕገ ወጥ የሰው ዝውውር የተከሰሰው ኤርትራዊ ለኔዘርላንድስ ተላልፎ ተሰጠ

የፎቶው ባለመብት, INTERPOL
ሰዎችን በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር የተከሰሰው ኤርትራዊ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለኔዘርላንድስ ተላልፎ መሰጠቱ ተገለጸ።
የ41 ዓመቱ ኪዳኔ ዘካርያስ ሃብተማርያም በኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ የአገሪቱ ዐቃቤ ሕግ በድረ ገጹ ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።
በኢትዮጵያ በፍርድ ሒደት ላይ ሳለ ካመለጠ በኋላ ላለፉት አምስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ገብቶ ነበር።
በኔዘርላንድስ ወታደራዊ ፖሊስ ታጅቦ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ወደ አምስተርዳም መወሰዱም ተገልጿል።
ኪዳኔ በወንጀል ቡድን ውስጥ በመሳተፍ፣ ስደተኞችን በሕገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር፣ ሰዎችን በማገት፣ በብዝበዛ፣ አካላዊ ጥቃት በማድረስ እንዲሁም ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም በኔዘርላንድስ ሲፈለግ ነበር።
የኪዳኔ ጉዳይ ከሌላው ኤርትራዊ ተወልደ ጎይቶም ጋር የሚተሳሰር ሲሆን፤ ጎይቶም ባለፈው ወር በኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት ቀርቧል።
ዐቃቤ ሕግ ጎይቶም በ20 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ጠይቋል።
የጎይቶም ጠበቆች ኪዳኔን እንደ ምስክር ማቅረብ ይፈልጋሉ። ዐቃቤ ሕግ ባወጣው መረጃ መሠረት በሕገ ወጥ የሰው ዝውውር ትልቅ ከሚባሉ የፍርድ ሒደቶች አንዱ ነው።
እአአ በ2022 ከኢትዮጵያ ለኔዘርላንድስ ተላልፎ የተሰጠው ጎይቶም ለፍርድ ቤት በሰጠው ቃል በቁጥጥር ሥር የዋለው በተሳሳተ ማንነት እንደሆነ ገልጿል።
ጎይቶም በኢትዮጵያም በሕገ ወጥ የሰው ዝውውር ተከስሶ እንደነበር ይታወሳል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የተመራ ዓለም አቀፍ አሰሳ ተካሂዶ ኪዳኔ በ2023 በሱዳን ተይዞ ነበር።
የፊታችን ቅዳሜ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብም የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ አስታውቋል።
"ሁለቱ ኤርትራውያን አብረው በመሥራት ከፍተኛ ገንዘብ አግኝተዋል። በዋናነት ኤርትራውያን ስደተኞችን ያንገላቱ እና ገንዘባቸውን ይበዘብዙ ነበር። ጥቃት ያደርሱ የነበረው በሊቢያ ነው። ኔዘርላንድስ ካሉ ቤተሰቦቻቸው ገንዘብ በመጠየቅ ብዝበዛውን ፈጽመዋል" ሲል ዐቃቤ ሕግ መግለጫ አውጥቷል።
በሊቢያ ኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የሚያደርሱት ስቅይት "ይቆም የነበረው ቤተሰቦቻቸው ከከፈሉ ብቻ ነው" ሲል ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።
የስደተኞቹ ቤተሰቦች ገንዘብ ከከፈሉ በኋላ ስደተኞቹ የሚደርስባቸው ስቃይ ተገትቶ ወደ አውሮፓ ጉዟቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚፈቀድላቸውም ተገልጿል።
ኪዳኔ ከኢትዮጵያ ካመለጠ በኋላ በሌለበት የዕድሜ ልክ እስራት ተፍርዶበት ነበር።
የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ ኪዳኔ ላይ የሚያቀርበው ክስ ከሊቢያ ወደ አውሮፓ የሚጓዙ ስደተኞች ላይ ከተፈጸመ ጥቃት እና ብዝበዛ ጋር ይገናኛል።
ጥር 1/2023 በሱዳን በቁጥጥር ሥር የዋለው ኪዳኔ በኔዘርላንድስ የሚፈለጉ ተጠርጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ነበር።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ መስመር ውስጥ በማስገባት ላይ ምርመራ ስታደርግ ኪዳኔ እንደተያዘ የዐቃቤ ሕግ መግለጫ ይጠቁማል።
በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በቀረበበት ክስ ታስሮ ከቆየ በኋላ ለኔዘርላንድስ ተላልፎ ተሰጥቷል።
ከሁለቱ ኤርትራውያን በተጨማሪ ሌሎች አምስት ተጠርጣሪዎች ለወንጀል ቡድን ገንዘብ በመሰብሰብ እና በማስተላለፍ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተገልጿል።
የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ምርመራ እየተካሄደ ያለው እአአ ከ2014 እስከ 2020 ድረስ በተፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶች ነው።
በዚህም ጣልያን፣ ዩሮፖል፣ ኢንተርፖል እና ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንደሚሳተፉ ተገልጿል።















