ኢትዮጵያ ለኔዘርላንድስ አሳልፋ የሰጠችው ኤርትራዊ ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ክስ ዛሬ መታየት ይጀምራል

የፎቶው ባለመብት, IDN
በዓለም አቀፍ ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር የተከሰሰው እና ከኢትዮጵያ ወደ ኔዘርላንድስ ተላልፎ የተሰጠው ኤርትራዊ ተወልደ ጎይቶም ክስ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 24/2018 ዓ.ም. መታየት ይጀምራል።
ተወልደ ጎይቶም በቅፅል ስሙ ዋሊድ በሊቢያ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በመዝረፍ እና በማሰቃየት ጭካኔ የተሞላበት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ንግድ በመፈጸም ወንጀል በአምስት ክሶች የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ውሳኔ አሳልፎበት ነበር።
በተወልደ ጎይቶም ላይ እና በግብር አበሮቹ ላይ የኔዘርላንድስ ፍርድ ቤት የበርካቶችን ምስክርነት ስለሚሰማ ውሳኔ የሚሰጥበት ጊዜ አንድ ወር ያህል ሊወስድ ይችላል ተብሏል።
ተወልደ ጎይቶም ወይም ዋሊድ ዓለም አቀፍ የሰዎች ዝውውር ቡድንን በመምራት በሊቢያ ውስጥ ኤርትራውያንን በማሰር፣ በማሰቃየት እና ፆታዊ ጥቃቶችን በመፈፀም ተወንጅሏል።
ተወልደ የሚመራው የወንጀል ቡድን በሊቢያ ባኒ ዋሊድ በሚባል አካባቢ የስደተኞች ማቆያ የነበረወ ሲሆን፣ ከግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን ከሱዳን እና ከሌሎች አገራት የመጡ ስደተኞችን በማሰቃየት ከቤተሰቦቻቸው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሲቀበል እንደነበር ተነግሯል።
ወደ አውሮፓ ለመድረስ የሚሞክሩት ስደተኞች በሊቢያ ካምፖች ውስጥ በነበሩበት ወቅት ድብደባ፣ ረሃብ እና መደፈሮችን ጨምሮ አሰቃቂ ጥቃት ለዓመታት ተፈጽሞባቸዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ ስደተኞች መሞታቸው ይነገራል።
ተወልደ ጎይቶም አብዛኞቹ ኤርትራውያን የሆኑ በሺዎች፣ ምናልባትም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በሕገወጥ መንገድ ከቦታ ቦታ ሲያዘዋውር ነበር ተብሏል።
ዋሊድ በቁጥጥሩ ስር በነበሩ ስደተኞቹ ላይ ስልታዊ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ይፈጽም እንደነበር የተለያዩ የጥቃቱ ሰለባዎች ይናገራሉ።
የኔዘርላንድስ ዐቃቤ ሕግ በተወልደ ጎይቶም በኩል ወደ አገሪቱ የገቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በእርሱ እና በተባባሪዎቹ የደረሰባቸውን ከተናገሩ በኋላ ነው ክስ የመሠረተው።
በዚህ ጉዳይ 191 ሰዎች ምስክርነት ተሰምቷል።
ዋሊድ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 2020 በቁጥጥር ስር ሲውል ኪዳነ ዘካሪያስ ኃብተማሪያም (ኪዳኔ) ከሚባል ሌላ አደገኛ የሕገወጥ ሰዎች አዘዋዋሪ ጋር ነበር።
ሁለቱም ግለሰቦች ኤርትራውያን ሲሆኑ አብዛኞቹ ኤርትራውያን የሆኑ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በመያዝ ገንዘብ እስኪከፍሉ ድረስ በቁጥጥራቸው ስር አቆይተዋቸዋል።
ዋሊድ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሕገወጥ ሰዎች ዝውውር ጋር በተያያዘ በቀረቡበት አምስት ክሶች ጥፋተኛ ተብሎ ነበር።
ከዚያ በኋላም ሊቢያ ውስጥ በፈጸማቸው ወንጀሎች ወደሚፈለግበት ኔዘርላንድስ ተላልፎ ተሰጥቷል።
ኪዳኔ በኢትዮጵያ በቁጥጥር ሥር ውሎ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እየታየ በነበረበት ወቅት አምልጦ የነበረ ቢሆንም በኋላ ላይ ሱዳን ውስጥ አንደ አውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 1/2023 በቁጥጥር ስር ውሏል።
በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ በሕገ ወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ በመጠቀም ተከስሶ ችሎት ፊት ቀርቧል።
የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ኪዳኔን ለኔዘርላንድስ አሳልፋ ለመስጠት የተስማማች ሲሆን፣ በዋሊድ ላይ ምስክር ሆኖ ሊቀርብ ይችላል ተብሏል።
በዋሊድ ላይ የቀረቡ ክሶች መታየት የጀመሩት ከአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 2023 ጀምሮ ነው።
ጉዳዩ እየታየ በነበረባቸው የመጀመሪያ ወራት አካባቢ ዋሊድ ምስክሮችን በማስፈራራት እና ሐሰተኛ መታወቂያ ለማግኘት በመሞከር ተከስሷል።
በዋሊድ የተለያየ ስቅይት የደረሰባቸው ኤርትራውያን በከፍተኛ ቁጥር ወደ ችሎት በመምጣት ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሐምሌ 5/2024 ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኤርትራ ማኅበረሰብ አባላት ከፍርድ ቤቱ ፊት ለፊት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ እና የኤርትራ መንግሥት ረዥም እጅ አለበት በሚል የተቃውሞ ሠልፍ አካሄደዋል።
የሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎቹ ሰለባ ለሆኑ እና መውጣት ለፈሩ ሰዎችም የአገሪቱ መንግሥት ከለላ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) በሊቢያ 900 ሺህ ያህል ስደተኞች አሉ ብሎ ይገምታል።
ዋሊድ ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2018 ድረስ በሊቢያ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰንሰለትን ይመራ ነበር ተብሎ ይታመናል።
ይህ ሰንሰለት ኤርትራውያን ስደተኞችን ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ማቆያ ስፍራ ማጓጓዝ፣ ማስፈራራት እና ማሰቃየትን ይጨምራል።
ስቅይቱ በሚፈጸምባቸው ወቅት ለቤተሰቦቻቸው የተጠየቁትን እንዲከፍሉ መደወል ይጠበቅባቸው ነበር።
ለገንዘብ ሲሉ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን ማካሄድ በባርነት እንደ መያዝ ተደርጎ ይቆጠራል።
ስቅይቱ ድብደባን፣ ማቃጠልን፣ ላስቲክ አቅልጦ በሰውነታቸው ላይ ማንጠባጠብን፣ እንዳይንቀሳቀሱ አድርጎ አጥብቆ ማሰርን እንዲሁም በኤሌክትሪክ ሾክ ማድረግን ያካተተ ነው።
በአዘዋዋሪዎቹ ቁጥጥር ሥር ውለው የሚሰቃዩ ስደተኞች የሚታሰሩት ጨለማ በሆነ መጋዘን ውስጥ ሲሆን የሚሰጣቸውም ጥቂት ምግብ ብቻ ነው።
ተመራማሪዎች ከአውሮፓውያኑ 2016 እስከ 2021 ባሉት ዓመታት ውስጥ 100 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች በሊቢያ በኩል አድርገው ወደ አውሮፓ መሻገራቸውን ይገምታሉ።
በዚህ ወቅት የኤርትራውያን ስደተኞች ቤተሰቦች ለሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች የከፈሉት ገንዘብ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚሆን ይገመታል።
በሊቢያ የሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ዋሊድ እና ኪዳኔ ብቻ አለመሆናቸውን በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉ ተቋማት ያስረዳሉ።
በሊቢያ ውስጥ ሌሎች ከፍተኛ ስም ያተረፉ ኤርትራውያን የሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ከሊቢያውያን ጋር በመሆን እንደሚሠሩ እና የተለያዩ የስቅይት ተግባራት እንደሚፈጽሙ ደርሰውበታል።
በሊቢያ አሁንም ገንዘብ ለማግኘት በሚል ሕገ ወጥ ስደተኞችን ማዘዋወር እንደቀጠለ ነው።
ኤርትራውያን ስደተኞች ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ሱዳናውያን እና ሌሎች ስደተኞችም በእነዚህ ቡድኖች የተለያዩ ስቃዮች ይደርስባቸዋል።
ዋሊድን እና ኪዳኔን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ያደረገው ዓለም አቀፍ ምርመራ በሊቢያ የሚገኙ ሌሎች የሕገወጥ ቡድኖች ላይም ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ መሆኑን ይናገራል።
ይህ ኔዘርላንድስ፣ ጣሊያን፣ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እና ኢንተርፖል ያሉበት የምርመራ ቡድን ዋሊድ፣ ኪዳኔ እና አምስት ሌሎች ግብረ አበሮቻቸውን በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አስችሏል።















