በፆታዊ ትንኮሳ ተፈርዶበት ከዩኬ ወደ ኢትዮጵያ የተባረረውን ግለሰብ መልቀቁን ፌደራል ፖሊስ ገለጸ

ሐዱሽ ገብረ ሥላሴ ቅባቱ በዩናይትድ ኪንግደም በሁለት የጾታዊ ትንኮሳ ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ 12 ወራት እስር ተፈርዶበታል

የፎቶው ባለመብት, Essex Police

የምስሉ መግለጫ, ሐዱሽ ገብረ ሥላሴ ቅባቱ በዩናይትድ ኪንግደም በሁለት የጾታዊ ትንኮሳ ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ 12 ወራት እስር ተፈርዶበታል

በዩናይትድ ኪንግደም በፈፀመው ፆታዊ ትንኮሳ ተፈርዶበት ወደ ኢትዮጵያ የተባረረው ሀዱሽ ገብረ ሥላሴ ዛሬ ማለዳ ኢትዮጵያ ከደረሰ በኋላ መለቀቁን የፌደራል ፖሊስ ለቢቢሲ ገለፀ።

የፌደራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄይላን አብዲ እንደተናገሩት ግለሰቡ ከዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ተባርሮ ወደ ኢትዮጵያ ሲላክ አብሮ የመጣ ምንም ዓይነት የወንጀል ክስ አለመኖሩን ገልፀዋል።

በዚህም ምክንያት ግለሰቡ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ወደ ፌደራል ፖሊስ ቢሮ ከተወሰደ በኋላ መለቀቁን ለቢበሲ አረጋግጠዋል።

"ለእኛ አብሮ በግለሰቡ ላይ ተያይዞ የመጣ ክስ ስለሌለበት ለቀነዋል፤ ምንም አብሮ የመጣ የወንጀል ክስ የለም. . . እኛ ጋር መጥቶ አጣራን ምንም ዓይነት አብሮ የመጣ ክስ ከሌለ ፖሊስ ይለቀቃል፤ ለቀነዋል።"

የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለቢቢሲ አንዳረጋገጡት በዩኬ ውስጥ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቶ የነበረው ሀዱሽ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ መለቀቁን በተመለከተ "በአሁኑ ሰዓት እኛ ስር አይደለም ለቅቀነዋል" ብለዋል።

ሀዱሽ ገብረ ሥላሴ ቅባቱ በጀልባ ከፈረንሳይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገባ በኋላ በአንዲት ታዳጊ እና አዋቂ ሴት ላይ ጾታዊ ትንኮሳ በመፈጸሙ የ12 ወራት እስር ተፈርዶበት ነበር።

ሀዱሽ ባለፈው ሳምንት አርብ ከእስር ቤት በስህተት ከተለቀቀ በኋላ በተደረገ ፍለጋ ከሁለት ቀናት በኋላ በሰሜን ለንደን አንድ መናፈሻ ውስት ተገኝቷል።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በፈጸመው ፆታዊ ትንኮሳ የተፈረደበት እና በስህተት ተለቅቆ የነበረው ሀዱሽ ገብረሥላሴ ቅባቱ ወደ ኢትዮጵያ መባረሩን የአገሪቱ መንግሥት ያስታወቀው ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 19 2018 ዓ.ም. ማለዳ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሀዱሽ ከፈረንሳይ በባሕር ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገባ በኋላ ይኖርበት በነበረበት ኤሲክስ የ14 ዓመት ታዳጊ እና ሌላ ሴት ላይ ፆታዊ ትንኮሳ በመፈጸሙ ተከስሶ የአንድ ዓመት እስር ተፈርዶበት ነበር።

ባለፈው ሳምንት አርብ ዕለት በስህተት ከእስር ቤት ከተለቀቀ በኋላ ለሁለት ቀናት ሲፈለግ ቆይቶ በሰሜን ለንደን አንድ መናፈሻ ውስጥ ተይዞ ወደ ማረሚያ ቤት ተመልሶ ነበር።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ በአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና በተቃዋሚዎች መካከል ውዝግብ የፈጠረው ይህ ግለሰብ አሁን ወደ ኢትዮጵያ መላኩ ተገልጿል።

ማክሰኞ ዕለት ማታ ወደ ኢትዮጵያ በሚጓዝ አውሮፕላን መሳፈሩን እና ረቡዕ ዕለት ማለዳ ኢትዮጵያ መድረሱን የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አስታውቋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስት የሆኑት ሻባና ሞሐሙድ "ባለፈው ሳምንት የተከሰተው በድጋሚ መሆን የለበትም። የተቀሰቀሰውን የሕዝብ ቁጣም እኔም እጋራለሁ" ብለዋል።

"ሀዱሽን ወደ አገሩ ለመመለስ እና ከብሪታኒያ ምድር ለማስወጣት ያለውን አማራጭ ሁሉ ተጠቅሜያለሁ። ይህ ጨካኝ ሕጻናት ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ የሚፈጽም ወንጀለኛ ግለሰብ ወደ አገሩ እንዲመለስ መደረጉን ሳረጋግጥላችሁ በደስታ ነው። በዚህም የተነሳ ጎዳናዎቻችን ደኅንነታቸው የተጠበቀ ሆኗል" ሲሉ አክለዋል።

ሀዱሽ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ዳግመኛ እንዳይመለስ በሚል መባረሩን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ሀዱሽ ታስሮበት ከነበረው ማረሚያ ቤት ቼልምስፎርድ ወደ ስደተኞች ማቆያ ማዕከል ከተወሰደ በኋላ የውጭ ዜጋ ጥፋተኞችን ከአገር በፍጥነት ለማስወጣት በተዘጋጀው አሠራር መሠረት እንዲወጣ ተደርጓል።

ባለፈው ሳምንት ሀዱሽ ከእስር ቤት በስህተት መለቀቁን ተከትሎ የፍትህ ሚኒስትሩ ዴቪድ ላሚ "ሰዋዊ በሆነ ስህተት" መሠረት መለቀቁን ተናግረዋል።

የኤሲክስ ፖሊስ ሀዱሽ በስህተት መለቀቁን ባወቀበት ወቅት፣ እርሱ በከተማዋ ውስጥ ያገኛቸውን ሰዎች ድጋፍ በመጠየቅ ወደ ለንደን የሚጓዝ ባቡር ተሳፍሮ ነበር።

እሁድ ዕለት በፊንስበሪ የመናፈሻ ስፍራ በሚገኝ የመኪና መቆሚያ አካባቢ ከታየ በኋላ ለፖሊስ ጥቆማ በመድረሱ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ ማረሚያ ቤት ተልኳል።

ሀዱሽ ከአገር ከተባረረ በኋላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን የሆኑት አሌክስ ኖሪስ ለቢቢሲ "ጉዳዩ ማብቃት ባለበት መልኩ አብቅቷል" ሲሉ ተናግረዋል።

"ይህ ስህተት መሆኑን እንቀበላለን፤ በሁኔታው እኛም ሕዝቡም በጣም ተናድደናል።"

በማረሚያ ቤቶች ተመሳሳይ ነገር እንዳይደገም ጥፋተኞችን ወደ አገራቸው ለመላክ ከእስር ቤት ሲወጡ ጠንካራ "ማጣራቶችን" ጨምሮ "አፋጣኝ የቁጥጥር እርምጃ" መወሰዱን እንዲሁም ገለልተኛ መርማሪ ቡድን ከድርጊቱ የተወሰደው ትምህርትን መለየቱን ተናግረዋል።

ገለልተኛ ወገን ያደረገው ምርመራ ሀዱሽ እንዴት ከእስር ቤት ሊለቀቅ እንደቻለ እና የእስር ቤቱ ሠራተኞች በቂ ልምድ፣ ሥልጠና እና ቴክኖሎጂ ነበራቸው ወይ የሚለውን ይፈትሻል።

የመርማሪ ቡድኑን በሊቀመንበርነት የሚመሩት የሜትሮፖሊታን ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዳሜ ላይን ኦውንስ የሀዱሽ ፆታዊ ጥቃት ሰለባዎችን ተመሳሳይ ስህተት እንዳይፈጸም ምን መደረግ አለበት የሚለውን ምክረ ሃሳብ ይጠየቃሉ ተብሏል።

አንድ ታራሚ ከእስር ቤት ሲለቀቅ መደረግ ስላለበት ጥንቃቄ አፋጣኝ ዳሰሳ ተደርጓል።

ሀዱሽ ገብረሥላሴ ቅባቱ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የገባው ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበረ።

ሀዱሽ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከፈረንሳይ በጀልባ ከመግባቱ በፊት በሱዳን፣ በሊቢያ እና በጣሊያን አድርጎ ተጉዟል።

ሐምሌ ወር ላይ ፆታዊ ጥቃት በመፈጸም ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ሲውል እርሱ እና ሌሎች ጥገኝነት ጠያቂዎች በሚኖሩበት ሆቴል አካባቢ ከፍተኛ የተቃውሞ ሠልፍ ተካሂዶ ነበር።

ቼልምስፎርድ ፍርድ ቤት ጉዳዩን በተመለከተበት ወቅት ሀዱሽ ታዳጊ ልጅን በከተማዋ ማዕከል አካባቢ ለመሳም መሞከሩን እንዲሁም ግልጽ የሆኑ ወሲባዊ አስተያየቶችን መሰንዘሩን ገልጿል።

በሚቀጥለው ቀንም ይህችን ልጅ ያገኛት ሲሆን እርሷ እና ሌላ ሴት ላይ ፆታዊ ትንኮሳ ከማድረሱ በፊት ሊስማት ሞክሮ ነበር።

ሐዱሽ የቀረቡበትን ክሶች የካደ ሲሆን፣ ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የ12 ወራት እስር ተፈርዶበታል።

በዩናይትድ ኪንግደም ሕግ መሠረት አንድ ወንጀል የሠራ ስደተኛ ከአገር ለመባረር ቢያንስ 12 ወራት እስር ሊፈረድበት ይገባል።