የዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኞችን እያወዛገበ ያለው የኢትዮጵያዊው ስደተኛ ጉዳይ
ባለፈው ዓመት ማብቂያ ገደማ ወሲባዊ ትኮሳ ፈጽሟል በሚል የተያዘው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በስህተት ከእስር ከተለቀቀ በኋላ አሁንም በዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኞች መካከል መወዛገቢያ ጉዳይ ሆኗል።
ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሀዱሽ ገብረ ሥላሴ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽሟል በሚል መያዙን ተከትሎ የፀረ ስደተኞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
በግለሰቡ ላይ የአንድ ዓመት እስር ከተፈረደበት በኋላ ጉዳዩ ረግቦ የቆየ ቢሆንም ባለፈው አርብ በስህተት መለቀቁ ከተሰማ በኋላ ውዝግቡ ተመልሶ ተቀስቅሷል።
የዩናይትድ ኪንግደም ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የገዢው ሌበር ፓርቲን አስተዳደር ደካማነት ለማሳየት የሀዱሽን ከእስር ቤት መውጣት እንደማሳያ እየተጠቀሙበት ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ስታርመርን ጨምሮ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በእስረኛው መለቀቅ ቁጣቸውን በመግለጽ ገለልተኛ ምርመራ ማድረግን ጨምሮ በእስር ቤት የአሠራር ሂደት ላይ ለውጥ እንዲደረግ አዘዋል።
በቀጣዩ ምርጫ የጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር ተፎካካሪ ይሆናሉ የሚባሉት የወግ አጥባቂዊ ፓርቲ መሪዋ ኬሚ ባዴኖች እና የሪፎርም ዩኬ ፓርቲ መሪ የሆኑት ናይጀል ፋራጅ ከሀዱሽ መለቀቅ ጋር አያይዘው መንግሥትን "ደካማ" በማለት ክፉኛ ተችተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ ከእስር ቤት በስህተት የተለቀቀው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ሀዱሽ ገብረ ሥላሴ እጁን እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።
ሀዱሽ ከእስር ቤት ከወጣ ከሁለት ቀናት በኋላ እሁድ ረፋድ ላይ ሰሜን ለንደን ውስጥ በፖሊሶች ተይዟል።
ባለፈው አርብ ከለንደን ሰሜን ምሥራቅ ከምትገኘው ኤሴክስ እስር ቤት የወጣው ኢትዮጵያዊው ስደተኛ በወሲብ ትንኮሳ ተከስሶ መስከረም ላይ የአንድ ዓመት እስር ተፈርዶበት ነበር።
ሀዱሽ በእስር ቤት ጥቂት ሳምንታትን ከቆየ በኋላ እንዴት በስህተት ሊለቀቅ እንደቻለ መነጋገሪያ ሆኗል።
ፖሊስም ስደተኛውን በመፈለግ ቀናት የተቆጠሩ ሲሆን አሁን ደግሞ እጁን እንዲሰጥ ጥሪ አስተላልፏል።
ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ወደ ምሥራቅ ለንደን ማቅናቱን ፖሊስ የገለጸ ቢሆንም የት እንዳለ ግን ማወቅ አልቻለም።
የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ጄምስ ኮንዌይ ቅዳሜ ዕለት እንዳስታወቁት ፖሊስ ስደተኛው እንዴት ሊሰወር እንደቻለ ለማወቅ "ሁሉንም መንገዶች እየመረመረ" ሲሆን፣"ሀዱሽ ባመለጠበት ጊዜ ገንዘብ ማግኘት መቻሉን እና ከነዋሪዎች ድጋፍ ማግኘቱን ደርሰንበታል" ብለዋል።
ሀዱሽ ላይ በተደረገው ክትትል አርብ እኩለ ቀን ላይ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ በተለያዩ የለንደን ባቡር መስመሮች ላይ ተሳፍሮ በርካታ ጉዞ ካደረገ በኋላ ምሥራቅ ለንደን ውስጥ በምትገኘው ስትራትፎርድ ከባቡር መውረዱ ታውቋል።
በሕገወጥ መንገድ በጀልባ ተሳፍሮ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገባ ከሳምንት በኋላ በአንዲት የ14 ዓመት ታዳጊ እና ሌላ ሴት ላይ ወሲባዊ ትኮሳ ፈጽሟል ተብሎ ክስ የቀረበበት ሀዱሽ በአገሪቱ ውስጥ ቁጣን ቀስቅሶ ነበር።
በዚህም ምክንያት ነዋሪዎች ሀዱሽ እና ሌሎች ስደተኞች በመንግሥት እንዲያርፉበት ወደ ተደረገው ሆስቴል በመሄድ ተደጋጋሚ የተቃውሞ ሰልፍ ከማድረጋቸው በተጨማሪ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተው በርካቶች ለእስር ተዳርገው ነበር።
ሀዱሽ ፈጸመ የተባለውን ትንኮሳ መሠረት አድርገው ለስደተኞች አሉታዊ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ያደረጉት ግፊት ጉዳዩ በአገሪቱ ከፍተኛ መሪዎች እና ፖለቲከኞች ዘንድ ትኩረትን አግኝቶ የውዝግብ ምክንያት ሆኖ ሰንብቶ ነበር።
አሁን ደግሞ ስደተኛው ከእስር ቤት ተለቋል መባሉ ውዝግብን አስነስቶ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በገዢው ሌበር ፓርቲ ላይ ትችትን እየሰነዘሩ ነው።
ካለፈው አርብ ከሰዓት በኋላ አንስቶ ሀዱሽ ገብረ ሥላሴን እያፈላለገ ያለው ፖሊስ፣ ግለሰቡ በቀጥታ እጁን እንዲሰጥ ጠይቋል። የፖሊስ ኃላፊው ኮንዌይ ለተፈላጊው ሀዱሽ በቀጥታ ባስተላለፉት መልዕክት ያለበትን ለፖሊስ እንዲያሳውቅ አሳስበዋል።
"ለኢሚግሬሽን ሠራተኞች ወደ ኢትዮጵያ መመለስ እንደምትፈልግ ቀደም ሲል አሳውቀሃል። የተሻለው መንገድ በቀጥታ ከፖሊስ ጋር መገናኘት ወይም ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመሄድ እጅ መስጠት ነው" በማለት ፖሊስ የት እንዳለ ለማወቅ እያፈላለገው መሆኑን ገልጸዋል።
ፖሊስ ቅዳሜ ዕለት ባሠራጨው በደኅንነት ካሜራ የተቀረጸ ቪዲዮ ሀዱሽ ከእስር ቤት የተሰጠውን ልብስ እንደለበሰ በሰሜን ለንደን በሚገኝ ቤተ መጽሐፍት ውስጥ አርብ አመሻሽ ላይ መታየቱን ያሳያል።
ተጨማሪ የፖሊስ መኮንኖች ሀዱሽ ታይቶባቸዋል ወደ ተባሉ አካባቢዎች ተሰማርተው እየፈለጉት መሆናቸውን የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የፍትሕ ሚኒስትር የሆኑት ዴቪድ ላሚይ ሀዱሽ እንዴት ከእስር ቤት ሊለቀቅ እንደቻለ የሚመረምር ገለልተኛ አጣሪን የሚመሩ ዕጩዎች እንዲመረጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
በተጨማሪም ሀዱሽ የተለቀቀበት ዓይነት ስህተትን ለመከላከል እስረኞች ከመለቀቃቸው በፊት ባለው ምሽት ላይ ተጨማሪ ማጣራት እንዲደረግ የሚያዝ አዲስ አሠራር ከሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ ታዟል።
የዩናይትድ ኪንግደም የፍትሕ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ፍርደኛው ከነበረበት እስር ቤት በወጣበት ሁኔታ "በእጅጉ ማዘናቸውን" ገልጸዋል።
ላሚ በኤክስ ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት "ግለሰቡ በአስቸኳይ እንዲያዝ ከፖሊስ ጋር እየሠራን ሲሆን በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ምርመራ እንዲደረግ አዝዣለሁ" ብለዋል።
"ሀዱሽ በእኛ ጎዳናዎች ላይ መቆየት የለበትም፤ለፈጸመው ወንጀል ከአገር መባረር አለበት" ሲሉም ሚኒስትሩ ቁጣቸውን ገልጸዋል።
አካባቢውን ወክለው የፓርላማ አባል የሆኑት ማሪ ጎልድማን እንዴት ግለሰቡ በስህተት ሊለቀቅ እንደቻለ ይፋዊ ፈጣን ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
"ይህ የወከልኩትን ሕዝብ ደኅንነት ለአደጋ የሚዳርግ በመሆኑ ፍጹም ተቀባይነት የሌለው ነው" ያሉት የፓርላማ አባሏ፣ "ከእስር ቤት አገልግሎት መልስ እፈልጋለሁ" ብለዋል።
የወግ አጥባቂዊ ፓርቲ መሪዋ ኬሚ ባዴኖች "በሌበር ፓርቲ ሥር ያለው የአገሪቱ አጠቃላይ ሥርዓት እየፈረሰ ነው" በማለት የእስረኛውን ማምለጥ ተቀናቃኛቸውን ገዢ ፓርቲ ለመውቀስ ተጠቅመውበታል።
የሪፎርም ዩኬ ፓርቲ መሪ የሆኑት ናይጀል ፋራጅ በበኩላቸው "[ሀዱሽ] አሁን በኢሴክስ ከተማ ጎዳናዎች ላይ እየተንቀሳቀሰ ነው። ብሪታኒያ ችግር ላይ ናት" ሲሉ ገዢውን ፓርቲ ወርፈዋል።
በወሲባዊ ትንኮሳ የተከሰሰው የኢትዮጵያዊ ሀዱሽ ጉዳይ ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፎች የቀሰቀሰ ሲሆን አሁን ከእስር ቤት በስህተት መለቀቁ ደግሞ ፖለቲከኞች በቀጣይ ለሚካሄደው ምርጫ ገዢውን ሌበር ፓርቲን ለማጥቃት እየተጠቀሙበት ነው።
ሀዱሽ ገብረሥላሴ ከእስር ቤት በወጣበት ጊዜ የእስር ቤቱን ሙሉ ልብስ ለብሶ በፌስታል እቃዎቹን ይዞ እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።
ሀዱሽ ባለፈው መስከረም ወር አጋማሽ ላይ የአንድ ዓመት እስር በተፈረደበት ጊዜ ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ግለሰቡ በልጆች እና በሴቶች ላይ ወሲባዊ ጥቃት ሊፈጽም ይችላል በማለት ከእስር ከወጣም ቁጥጥር እንዲደረግበት አዝዘው ነበር።
ሀዱሽ የአንድ ዓመት እስር ተፈርዶበት አንድ ወር ከታሰረ በኋላ እንዴት በስህተት ሊለቀቅ እንደቻለ እስካሁን ግልጽ አይደለም።ነገር ግን የእስር ቤቱ ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ሀዱሽ በእስር ቤቱ ሠራተኛ እየተረዳ ከወጣ በኋላ ወደ ባቡር ጣቢያ ተወስዷል።
አንድ የእስር ቤቱ መኮንን ከስደተኛው መለቀቅ ጋር በተያያዘ ከሥራ የታገደ ሲሆን፣ አንድ ከፍተኛ የእስር ቤቱ ኃላፊ ግን ስህተቱ የተፈጠረው "እስር ቤቱ ባሉት ጥቂት መኮንኖች እየሠራ በመሆኑ በሥራ ጫና ምክንያት የተፈጠረ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።
"ለተፈጠረው ስህተት አንድ የእስር ቤቱ መኮንን ብቻ ሊጠየቅ አይገባም፤ ፍትሐዊም አይሆንም" በማለት መኮንኑ ያለውን ችግር አመልክተዋል።
ሀዱሽ ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ "ስህተት" መፈጠሩ ታውቆ የእስር ቤቱ አሰተዳደር ለኤሴከሰ ፖሊሰ ካሳወቀ በኋላ መልሶ ለመያዝ ፍለጋው የተጀመረው አርብ ከእኩለ ቀን በኋላ ሰባት ሰዓት ላይ ነበር።
ስደተኛው ኢትዮጵያዊ ከእስር ቤት ከተለቀቀ በኋላ በባቡር ተሳፈሮ የሄደ ሲሆን፣ የተለያዩ የባቡር መስመሮችን በማቆራረጥ ወደ በርካታ የለንደን አካባቢዎች ተጉዟል።

የፎቶው ባለመብት, Met Police
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የእስረኛው ከእስር ቤት መውጣትን ከሰሙ በኋላ የተፈጠረውን ስህተት "ፍጹም ተቀባይነት የሌለው" በማለት ሀዱሽ "ተይዞ በፈጸመው ወንጀል ምክንያት ከአገሪቱ መባረር አለበት" ሲሉ ተናግረዋል።
የቀድሞው የእስር ቤት ተቆጣጣሪ የሆኑት ጆን ፓድሞር የተፈጠረው ስህተት "ካለው ሰፊ ችግር አንጻር" መታየት እንዳለበት እና "አንድ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝን መኮንን ተጠያቂ የሚያደርግ እንደማይሆን" ተስፋቸውን ገልጸዋል።
ጨምረውም "የእስር ቤቶች አስተዳደር ሥርዓታችን ተበላሽቷል።ይህ የእስር ቤት አስተዳደር ሥርዓት ሲበላሽ የሚከሰት ነገር ነው" በማለት ለቢቢሲ ራዲዮ 4 ተናግረዋል።
አርብ ዕለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚይ ከእስረኛው መለቀቅ ጋር በተያያዘ በእጁጉ መቆጣታቸውን ገልጸዋል።
"ሀዱሽ በታዳጊ እና በአዋቂ ሴት ላይ አስቀያሚ የወሲባ ጥቃት ወንጀል ፈጽሟል። በእነዚህ ምክንያቶች የተነሳ ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ነው" ብለዋል ላሚይ።
የእስር ቤቶች አገልግሎት ቃል አቀባይ እንዳሉት "ፍርደኛው በስህተት ከተለቀቀ በኋላ በአስቸኳይ በቁጥጥር ስር ውሎ ወደ እስር ቤት እንዲመለስ ከፖሊስ ጋር እየሠሩ ነው።"
"ኅብረተሰቡን መጠበቅ ቀዳሚ የምንሰጠው ጉዳይ በመሆኑ እስረኛው እንዴት ለእስር ቤት ሊወጣ እንደቻለ ለማወቅ ምርመራ ጀምረናል።"
ሀዱሽ ፈጽሞታል በተባለው ወሲባዊ ትኮሳ ምክንያት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በቁጥጥር ስር ሲውል በትንሽዬ ጀልባ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገባ በኋላ ካረፈበት 'ዘ ቤል' ሆቴል ውጪ የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል።
ሀዱሽ ሰኔ መጨረሻ ገደማ አንዲት ታዳጊን ለመሳም መሞከሩ እና በርካታ ወሲብ ነክ ንግግሮችን መናገሩ ባለፈው መስከረም ወር ለተሰየመው ፍርድ ቤት ተገልጾ ነበር።
በተከታዩ ቀን ደግሞ ታዳጊዋን በድጋሚ አግኝቶ ወሲባዊ ትንኮሳ ከመፈጸሙ በፊት ሊስማት ሞክሯል። በተጨማሪም የሥራ ማመልከቻ በመጻፍ ሥራ እንዲያገኝ ልትረዳው በነበረች ሴት ላይ ወሲባ ትንኮሳ መፈጸሙን የሚገልጽ ክስ ለፍርድ ቤት ቀርቧል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የስፖርት መምህር እንደነበረ የተናገረው ሀዱሽ ለፍርድ ቤት በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 1986 በመናገሩ ዕድሜው 38 መሆኑ የተገለጸ ቢሆንም፣ የፍርድ ቤት ሰነዶች ግን 41 ዓመቱ መሆኑን ያመለክታሉ።
በቀረቡበት አምስት ክሶች ጥፋተኛ የተባለው ሀዱሽ በመስከረም ወር አጋማሽ ላይ የአንድ ዓመት እስር እና ወሲባዊ ጥቃት እንዳይፈጽም ለመከላከል ለአምስት ዓመታት ማንኛዋንም ሴት እንዳይቀርብ ዕግድ ተጥሎበታል።
በተጨማሪም ለአስር ዓመታት በወሲባዊ ጥቃት ፈጻሚዎች መዝገብ ላይ ሰፍሮ በየጊዜው እንዲፈርም ትዕዛዝ ተላልፎበታል።
የእስር ቤት ምንጮች እንዳሉት ሀዱሽ ከታቀደለት ከዩናይትድ ኪንግደም የመባረር ውሳኔ በፊት ወደ ስደተኞች የማቆያ ማዕከል ሊላክ ነበር።
ፍርድ ቤት በቀረበበት ጊዜ ከዩናይትድ ኪንግደም እንዲባረር "ጽኑ ፍላጎት" እንዳለው ሲናገር ተሰምቶ የነበረ ሲሆን፣ ወደ የትኛው አገር እንደሚባርር ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም።
የኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሀዱሽ ገብረሥላሴ ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ስቦ የፖለቲከኞች መወዛገቢያ ሆነ እንጂ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የእስረኞች በስህተት መለቀቅ አዲስ ነገር አይደለም።
ከአገሪቱ የእስር ቤቶች እና የታሳሪዎች አስተዳደር አገልግሎት የወጣ መረጃ እንደሚያመልክተው ከአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2024 እስከ መጋቢት 2025 ድረስ ባለው ጊዜ 262 እስረኞች ከእንግሊዝ እና ከዌልስ እስር ቤቶች በስህተት ተለቅቀዋል።
ይህ አሃዝ ቀደም ካለው ጊዜ በ115 ከፍ ያለ እንደሆነ ተነግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Met Police
















