በለንደን ስደተኞችን በመቃወም አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች ፖሊስ ላይ ጥቃት ፈጸሙ

የፎቶው ባለመብት, EPA/Shutterstock
ቅዳሜ ዕለት በለንደን ስደተኞችን በመቃወም አደባባበይ የወጡ ቀኝ ዘመሞች 26 የፖሊስ ባልደረቦች ላይ ጥቃት መፈፀማቸው ተገለፀ።
በብሪታኒያ ዋና ከተማ ለንደን 150,000 ሰዎች ስደተኞችን በመቃወም አደባባይ መውጣታቸው ተከትሎ ለጥበቃ የተሰማሩ የፖሊስ ባልደረቦች "በተወርዋሪ ነገሮች ተመትተዋል" እንዲሁም "ጥቃት ተፈጽሞባቸዋል" ተብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም በተካሄደው የተቃውሞ ሠልፍ ላይ የውሃ ፕላስቲኮች እና ሌሎች ቁሶችን ወደ ፖሊስ መወርመወር ሲጀምሩ ውጥረት መፈጠሩን እና አራት የፀጥታ አባላት በጽኑ መጎዳታቸውን የሜትሮፖሊታን ፖሊስ አስታውቋል።
ቢሊኒየሩ ኤለን መስክ በቪዲዮ ንግግር ያደረገ ሲሆን 5000 ያህል ሰዎች ደግሞ በሌላ አካባቢ ሠልፉን ተቃውመው አደባባይ ወጥተዋል።
ትናንት በዩኬ ፀረ ስደተኛ አቋምን በሚያራምደው አክቲቪስት ቶሚ ሮቢንሰን "ዩናይት ዘ ኪንግደም" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው እና በመቶ ሺህ የተቃውሞ ሠልፈኞች የተገኙበት ሠልፍ ተካሄዷል።
በተመሳሳይ አካባቢ ደግሞ "ስታንድ አፕ ቱ ሬሲዝም" በሚል መሪቃል 5000 ያህል ሰዎች ይህንን በመቃወም ሠልፍ አካሄደዋል።
የሜትሮፖሊታን ፖሊስ እንዳስታወቀው 25 ሰዎች "ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው" ያለውን የተለያዩ ጥሰቶችን ሲፈጽሙ በመገኘታቸው በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በማዕከላዊ ለንደን 1000 የፀጥታ ኃይሎችን በማሰማራት እንዲሁም ከሌሎች የዩኬ ከተሞች 500 ተጨማሪ ፖሊሶችን በማምጣት ጥበቃ ተካሄዷል።
ረዳት ኮሚሽነር ማት ትዊስት ፖሊሶች የተጣለባቸው ግዴታ ፈታኝ መሆኑን እያወቁ "ያለ ፍርሃት እና አድልኦ" ሥራቸውን አከናውነዋል ብለዋል።
"አብዛኞቹ ሕግ የሰጣቸውን የመቃወም መብት ለመጠቀም መምጣታቸው የማይታበል ሀቅ ነው፤ ነገር ግን ሌሎች ደግሞ ለዐመጽ ይሁነኝ ብለው መጥተዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
ረዳት ኮሚሽነር ትዊስት የፖሊስ ባልደረቦች የጥርስ መሰበር፣ የጭንቅላት መፈንከት፣ የዲስክ መንሸራተት፣ የጭንቅላት ግጭት እና የአፍንጫ መሰበር አጋጥሟቸዋል ብለዋል።
"አሁን በቁጥጥር ስር ያዋልናቸው 25 ሰዎች ገና የመጀመርያችን ናቸው" ሲሉ በሰላም ማደፍረሱ ላይ የተሳተፉ ተጨማሪ ሰዎችን የከተማዋ ፖሊስ እንደሚለይ ተናግረዋል።
የአገር ውስጥ ሚኒስትር ሻባና ማሃሙድ ጥቃቱን አውግዘው "የፖሊስ አባላት ላይ ጥቃት የፈጸሙ እና ጉዳት ያደረሱትን" አውግዘዋል።
አክለውም "ማንኛውም በወንጀል ተግባር ላይ ተሳትፎ የተገኘ የሕግን ሙሉ አቅምን ይጋፈጣል" ብለዋል።
በከተማዋ የተካሄዱት ሠልፎች በአብዛኛው ሠላማዊ የነበሩ ቢሆንም የፖሊስ አባላት ሁለት የተለያየ ዓላማ ይዘው የወጡ ሠልፈኞችን ለመለያየት በሚሞክርበት ወቅት ወደ አመጽ ተሸጋግሯል።
'ዩናይት ዘ ኪንግደም' በሚል የተቃውሞ ሠልፍ ያደራጁ አካላት" ከግምታቸው በላይ የሆነ ሠልፈኛ" አደባባይ መውጣቱን ፖሊስ ተናግሯል።
ይህም ማለት ሠልፉ በተካሄደባቸው በዋይት ሆል እና በፓርላማው አደባባይ አካባቢ በቂ ስፍራ አልነበረም።
በርካታ ሠልፈኞች ፖሊስ የሚሰጠውን መመርያ ቸል በማለት 'ስታንድ አፕ ቱ ሬሲዝም' በሚል ርዕስ አደባባይ በወጡ ሠልፈኞች ወደ ተያዘው ስፍራ አምርተዋል።
"የፖሊስ አባላት ወደዚያ እንዳይሄዱ ለመከልከል በሞከሩበት ወቅት በእርግጫ እና በቦክስ ማጥቃት ጀምረዋል ሲል የከተማዋ ፖሊስ አስታውቋል።
እነዚህን ሁለት ተቃዋሚ ሠልፈኞች ለመጠበቅ ፖሊስ በፈረስ እና በውሻ ታግዟል።
በዋይት ሆል አካባቢ ተቀምጠው የነበሩ የሽቦ አጥር እንዲሁም መከላከያን ጥሰው በማለፍ "ራሳቸውን እና ሌሎችን ለአደጋ ጥለዋል" ሲል ፖሊስ አክሎ ገልጿል።
በቪዲዮ ሊንክ በድንገት የተከሰተው መስክ "ቁጥጥር ያልተደረገበት የስደተኞች ወጀብ" በማለት ንግግር ያደረገ ሲሆን በዩናይትድ ኪንግደም "የመንግሥት ለውጥ" እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል።
የሰልፉ አዘጋጅ የሆነው ሮቢንሰን ሲጠይቀውም መስክ "የሆነ ነገር መደረግ አለበት" ብሏል።
"ፓርላማው ተበትኖ አዲስ ምርጫ መካሄድ አለበት"።
ዘረኝነትን እንቃወም (Stand Up To Racism) በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሠልፍ ላይ ንግግር ያደረጉት የሕዝብ እንደራሴ ዲያን አቦት ለሠልፈኞቹ ዘረኝነት እና አመጽ እንዲሁም ፋሺስትነት አዲስ አይደሉም። ግን ምን አንደሆነ ታውቃላችሁ? ሁሌም ዘረኝነትን እና አመጽን እንዳሸነፍን ነው" ብለዋል።















