ለኢንሹራንስ ካሳ ሲል እግሩን ቆርጧል የተባለው የቀዶ ጥገና ሐኪም እስር ተፈረደበት

የቀዶ ጥገና ሐኪም

በዩናይትድ ኪንግደም የኢንሹራንስ ካሳ ለማጭበርበር በሚል የራሱን እግሮች ቆርጧል የተባለው የቀዶ ጥገና ሃኪም የሁለት ዓመት ከስምንት ወር እስር ተፈረደበት።

ኔይል ሃርፐር የተባለው የዩኬ ብሔራዊ ጤና አገልግሎት የደም ቧንቧ የቀዶ ጥገና ሐኪም ኢንሹራንስ በማጭበርበር እንዲሁም ወጣ ያሉ የወሲብ ፊልሞችን በመያዝ ነው የእስር ቅጣቱ የተፈረደበት።

የ49 ዓመቱ ዶክተር በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች እግራቸውን በቀዶ ጥገና ያስወገደ ሲሆን የራሱንም እግር የቆረጠው በአውሮፓውያኑ 2019 ነው።

ግለሰቡ ሰውነት የራሱን በሸታ የመከላከል አቅም (ኢሚዩኒቲ) በሚያጠቃው ሴፕሲስ ኢንፌክሺን ተጠቅቻለሁ የሚል ውሸት ለኢንሹራንስ ሰራተኞች በመንገር የራሱን እግር በቀዶ ህክምና ማስወገዱ ተነግሯል።

የትሩሮ ከተማ ፍርድ ቤት ዶክተሩ እግሮቹን የቆረጠው እንደሚለው በበሽታ ምክንያት ሳይሆን ለኢንሹራንስ መሆኑን ሰምቷል።

ግለሰቡ "ሚስጥራዊ ህመም" ካደረበት በኋላ ከጉልበት በታች ጉልበቱን እንደቆረጠ ፍርድ ቤቱ ሰምቷል።

ሆኖም ዶክተሩ እግሮቹን በበረዶ በማቀዝቀዝ መቆረጥ የሚገባቸው ደረጃ ላይ ማድረሱን አቃቤ ህግ ኒኮላስ ሊ ተናግረዋል።

ግለሰቡ የቀረቡበትን ሁለት የማጭበርበር ወንጀሎችን እንዲሁም "በአካል መቁረጥ ላይ ወሲባዊ ዝንባሌ ማሳደር"ን ጨምሮ ወጣ ያሉ ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ፊልሞችን በመያዝ ሶስት ክሶችን አምኗል።

ዳኛ ጄምስ አድኪን በቅጣት ውሳኔው ላይ ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪከርዶች የሌሉት ዶክተር ጸጸት ተሰምቶታል ብለዋል።

ሆኖም ከሰውነት መቆራረጥ ጋር ወሲባዊ ዝንባሌዎች ማሳደሩ ጋር በተያያዘ በቀረቡት ሶሰስት ቪዲዮዎች ላይ የሚታየው "የጉዳት ደረጃ" በጣም ከፍተኛ ነው ሲሉ ዳኛው ተናግረዋል።

ዶክተሩ እግሮቹ ላይ ከፍተኛ ህመም በመሰማቱ በቀዶ ህክምና እንዲወገዱ ተደርገዋል።

ግለሰቡ የቀዶ ህክምና ሲደረግለት ተጠርጥሮ የነበረው ህመም ሴፕሲስ ነበር።

ነገር ግን የጉዳቱ ትክክለኛ መንስዔ እግሮቹን በበረዶ በማቀዝቀዝ ራሱን ጉዳት ላይ እንደጣሉ ለሃኪሞቹ አለመናገሩ በፍርድ ቤት ተገልጿል።

ዶክተሩ በተጭበረበረ መልኩ ከሁለት ኢንሹራንስ ድርጅቶች ከ466 ሺህ ፓውንድ በላይ ማግኘቱ ተሰምቷል።

ዶክተሩ "በስግብግነት" ተፈትኗል ሲሉ ዳኛው ተናግረዋል።

ዶክተሩ "ይህንን አጋጣሚ ልጠቀምበት" ሲል ለጓደኛው መልዕክት መላኩ በፍርድ ቤት ቀርቧል።

በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ የሚዲያ ቀልብ መሳቡ ለዶክተሩ ደስታ ፈጥሮለታል ብለዋል።

ዶክተሩ "የራሱን አካል ለማስወገድ የነበረው አባዜ ከወሲባዊ ፍላጎት ጋር ተደማምሮ ይህንን ድርጊት ፈጽሟል" ብለዋል።

እግሩን መቁረጥ "የረጅም ጊዜ ፍላጎቱ ነበር" ሲሉም ዳኛው አክለዋል።

ግለሰቡ እግሮቹ ከተቆረጠ ስድስት ወር ሳይሞላው በሰው ሰራሽ እግሮች ወደ ስራ ገበታው ተመልሷል።

ከዚያም በአውሮፓውያኑ 2023 በቁጥጥር ስር ውሎ ከአገልግሎቱ እንዲታገድ ተደርጓል።

የዶክተሩ ድርጊት በርካታ የጤና ባለሙያዎችን ያስደነገጠ ሆኗል።