ታካሚዎች ያለ ልክ እንዲወፍሩ የሚገፋፋው የሰውነት ቅነሳ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ

የፎቶው ባለመብት, COSMEDACARE
ዶ/ር ኦጉን ኤርሰን ይባላል። ቱርካዊ የሰውነት ክብደት ቅነሳ የቀዶ ሕክምና ባለሙያ ነው።
“ክብደት መቀነሻ” መንገዶች የሚላቸውን በመሸጥ ይታወቃል።
ቢቢሲ ስለ ዶክተሩ የበለጠ ለማወቅ ምርመራ አድርጓል። ጋዜጠኛ መሆኗን ሳትጠቅስ ዶክተሩን ያናገረችው የቢቢሲ ጋዜጠኛ፣ ይህ ዶክተር “ክብደት ጨምሪ” እንዳላት ትናገራለች።
የሰውነት ክብደትና ቁመት መመጣጠን በሚለካበት ቢኤምአይ መሠረት 24.4 ናት። ሆኖም ግን “ምግብ በመብላት” ሰውነቷን እንድትጨምር በዶክተሩ ተነግሯታል።
“ተመገቢ፣ ተመገቢ፣ ተመገቢ። የሰውነት ክብደትሽን ከአጠቃላይ ቁመናሽ አንጻር ከፍ አድርጊው” ብሏታል።
የሰውነት ክብደት መቀነሻ የቀዶ ሕክምና አገልግሎቱን ለማግኘት መወፈር እንዳለባት ነበር ለጋዜጠኛዋ የነገራት።
ጋዜጠኛዋ ወደ ዶክተሩ ቢሮ ሄዳ ትክክል ያልሆነ የሰውነት ክብደት መጠን አስመዘበች። ምርመራ ያደረገላት አልነበረም።
ዶ/ር ኦጉን ከሦስት ወር በኋላ ለቀዶ ሕክምና ቀጠራት።
እስከዚያው ክብደት እንድትጨምር ነገራት።
አንድ የጤና ባለሙያ ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ ታካሚዎች ክብደት እንዲጨምሩ ማበረታታት ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጭ ነው።
ቀዶ ሕክምና ካላስፈለገ መከናወን እንደሌለበት እና ከሆነ በኋላ መቀልበስ ለማይቻል ለጉዳቶች እንደሚዳርግ ያስረዳሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ክብደት የመቀነስ ቀዶ ሕክምና እስከ 15 ሺህ ፓውንድ ያስወጣል። በቱርክ ግን በ2,000 ፓውንድ ይሠራል።
ከሙያዊ ሥነ ምግባር ውጭ ሕክምናውን የሚሰጡ ተቋማት እንዳሉ የቢቢሲ ምርመራ ይጠቁማል።
በቱርክ ካሉ ብዙ ሐኪም ቤቶች አንዱ ኢኮል ነው።
ዩኬን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ደንበኞች ለማግኘት ማስታወቂያ ይሠራል።
ከልክ ያለፈ ውፍረት የሚገጥማቸው ሰዎች የሚደረግላቸው ቀዶ ሕክምና (bariatric surgery) ባልተገባ ሁኔታ የሚሰጥ ተቋም እንደሆነ ታይቷል።
ለምሳሌ የሰውነት ክብደታቸው ከቁመተቻው አንጻር (ቢኤምአይ) ሲነጻጸር ለዚህ ቀዶ ሕክምና በቂ ያልሆነ ሰዎችን ለሕክምናው ይመዘግባል።

የሰውነት ክብደት ቅነሳ ቀዶ ሕክምና ምንድን ነው?
ከ40 በታች ቢኤምአይ ያላቸው እና ከልክ ካለፈ የሰውነት ክብደት ጋር በተያያዘ ሕመም የሌለባቸው ሰዎች ይህንን ቀዶ ሕክምና እንዲያደርጉ አይመከርም።
ይህ ቀዶ ሕክምና ከልክ ያለፈ ውፍረት አስጊ የጤና ሁኔታ ውስጥ ላስገባቸው ሕሙማን የሚከናወን የመጨረሻ የሕክምና አማራጭ ነው።
ይህ ማለትም ከ40 አልያም ከ35 የዘለለ አይቢኤም ያላቸው እና ከልክ ካለፈ ውፍረት ጋር በተያያዘ የጤና እክል የገጠማቸው ታካሚዎች እንደ አማራጭ የሚሰጣቸው ቀዶ ሕክምና ነው።
የሰውነት ክብደት ለመቀነስ ሞክረው ያልተሳካላቸው ታካሚዎች መሆንም አለባቸው።
ሁለት ታዋቂ የሰውነት ቅነሳ ቀዶ ሕክምናዎች አሉ። አንደኛው የሆድ ክፍል ወጥቶ ምግብ የሚብላላበትን መንገድ ለመለወጥ የሚደረገው (Sleeve gastrectomy or gastric bypass) ነው።
ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ የሆድን መጠን በመቀነስ ሰዎች የሚመገቡትን መጠን መቀነስ (Gastric band) ነው።
ሁለት የቢቢሲ ጋዜጠኞች ወደ ቱርኩ ሆስፒታል አቅንተው ነበር።
የአንደኛዋ ቢኤምአይ 29 የሌላዋ 33 ነበር። በሕክምና አሠራር መሠረት ሁለቱም ቀዶ ሕክምናው አያስፈልጋቸውም።
አንደኛዋ ጋዜጠኛ የድባቴ ችግር እንደገጠማት ተናግራለች። ይህም ለቀዶ ሕክምናው ዝግጁ እንዳልሆነች ጠቋሚ መሆን ነበረበት።
ሆኖም ግን ሆስፒታሉ ጋዜጠኛው የምትመገበውን መጠን ጨምራ እና ወፍራ ለቀዶ ሕክምና እንድንትሄድ ተነገራት።

የሆስፒታሉ የሽያጭ ባለሙያ “የምበላውን በማስተካከል ለመቀነስ 30 ዓመት ሞክሬያለሁ። ይሄ ባህላዊ መንገድ ይሻላል? ለጥቂት ወራት ከፍተኛ ስብና ካሎሪ መብላት እና መመለስ አይሻልም” ብላታለች።
ሆስፒታሉ ግን ከዓለም አቀፍ መርኅ በተጻራሪው ቀዶ ሕክምናው ለማያስፈልጋቸው እንደማይሰጥ ነው የሚያስተዋውቀው።
ዶ/ር ኦጉን አስተያየቱን ሲጠየቅ ታካሚዎች ከልክ ያለፈ እንዲወፍሩ መንገሩን አስተባብሏል።
የሽያጭ ባለሙያዋ ደግሞ “የጤና ሥርዓቱ መቋቋም ከሚችለው በላይ ከልክ ያለፈ ውፍረት ተፈጥሯል። ሕክምናው የበለጠ ተደራሽ መሆን ነበረበት” ብላለች።
የሰውነት ቅነሳ ቀዶ ሕክምና አማካሪው ኦማር ካሀን እንደሚሉት፣ ታካሚዎች እንዲወፍሩ መገፋፋት ተቀባይነት የለውም።
“በጣም ያሰጋኛል። ታካሚዎቹ ውፍረታቸውን ጨምረው ቀዶ ሕክምና ማድረግ የግድ የሚሆንበት ነጥብ ላይ እንዲደርሱ ነው የሚገፋፋው። ይሄ ከሙያው ሥነ ምግባር ያፈነገጠ ነው” ብለዋል።
የጎንዮሽ ጉዳት የማያስከትል ቀዶ ሕክምና እንደሌለ፣ ነገር ግን እነዚህን ውስን ለማድረግ እንደሚሞከር የሚናገሩት ባለሙያው፣ “ቀጭን ሰው ይህንን ቀዶ ሕክምና ማድረግ የለበትም። ምንም ሳይጠቀሙ ለጎንዮሽ ጉዳት ብቻ ይጋለጣሉ” በማለት ችግሩን ያስረዳሉ።
ለውበት የሚደረግ ቀዶ ሕክምና ተቋም ያላቸው ባለሙያ ጊል ባይርድ፣ ለሰውነት ቅነሳ ቀዶ ሕክምና የሚሄዱ ሰዎችን እንደማይቀበሉ ይናገራሉ።
“አንዳንዶች ከባድ ነገር ኪሳቸው ውስጥ ከተው የሰውነት ክብደታቸው ከፍተኛ ስለሆነ ቀዶ ሕክምና እንደሚፈልጉ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። እኛ የምንመዝነው ግን ፈትሸን ነው” ይላሉ።
“ይህን ሲያደርጉ የሚደርስባቸውን ጉዳት አያስቡትም” ሲሉ ባለሙያዋ ያብራራሉ።
ቀዶ ሕክምናውን ማግኘት ያልቻሉ ሰዎች ወደ ሌሎች አገራት እየሄዱ ሕክምናውን እንደሚወስዱም ባለሙያዋ አክለዋል።
“አንድ ቀዶ ሕክምናውን አናደርግልሽም ያልናት ሴት ሌላ አገር ሄዳ ቀዶ ሕክምናውን አደረገች። በጣም ያሳዝናል። ከሳምንታት በኋላ መሞቷን ሰማን። ይህ ቀዶ ሕክምና ቀላል ነገር አይደለም” ሲሉም ተናግረዋል።












