በፈረንሳይ ክብደት ይቀንሳል በተባለ መድሃኒት እስከ 2ሺህ ሰዎች ሞተዋል ተባለ

ሚዲዬተር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በፈረንሳይ 2 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል የተባለው መድሃኒትን የሚመለከተው የአገሪቱ ከፍተኛ የፍርድ ሂደት ተጀመረ።

ውፍረት ለመቀነስ ይረዳል የተባለውና ሚዲዬተር የተሰኘው መድሃኒት አምራች ኩባንያ ግን የመድሃኒቱን የጎንዮሽ ጉዳት ሆን ብሎ በመደበቅ ሁለት ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን እንዲያጡ አድርጓል በሚል በርካታ ክሶች ቀርቦበታል።

በፈረንሳይ የህክምና አገልግሎት ትልቅ ቅሌት ነው በተባለው በዚህ ቀውስ ኩባንያው ሰርቪየር ሆን ብሎ የሰዎች ህይወች ህይወታቸውን እንዲያጡ በማድረግ በርካታ ክሶች ተመስርተውበታል።

ኩባንያው የመድሃኒቱን የጎንዮሽ ጉዳት አልደበቅኩም በማለት የቀረቡበትን ክሶች ያስተባብላል።

የፈረንሳይ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት መድሃኒቱን እአአ በ2009 መንግሥት ከገበያ እስካገደበት ጊዜ ድረስ ከ500 እስከ 2000 የሚሆኑ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።

መድሃኒቱ የተባለውን ጥፋት ሳያደርስ ቀድሞ ማገድ ሲኖርበት እጁን አጣጥፎ ተቀምጦ ነበር የተባለው የአገሪቱ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንም ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቧል።

ሚዲዬተር በተሰኘውን የክብደት መቀነሻ መድሃኒት የፍርድ ሂደት 2600 ከሳሾችና 21 ተከሳሾች ያሉበት ነው።