ዩናይትድ ኪንግደም ስደተኞች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚቀላቀሉበትን መንገድ አገደች

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን ማምጣት የሚችሉበትን መንገድ በጊዜያዊነት ማገዱን አስታወቀ።
የአገር ውስጥ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር ከዚህ ሳምንት ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነውን ይህ ውሳኔ ቤተሰቦቻቸውን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ማምጣት እንደተከለከሉት ፍልሰተኞች ሁሉ ስደተኞችም ተመሳሳይ ክልከላ ተጥሎባቸዋል ብለዋል።
ይህም ማለት አንድ ሰው ቤተሰቦቹን ለማምጣት በዓመት 29 ሺህ ፓውንድ ገቢ ማግኘት እና ምቹ ማረፊያ ሊኖረው የሚገባ ሲሆን የቤተሰብ አባላቱ ደግሞ መሠረታዊ የእንግሊዘኛ ቋንቋ እንደሚችሉ ማሳየት አለባቸው።
የወግ አጥባቂ ፓርቲ ትይዩ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ክሪስ ፍሊፕ የዩናይትድ ኪንግደምን የድንበር ደኅንነት ቀውስን ለመፍታት "የቤተሰብ መቀላቀል ሕጉ ላይ የተወሰነ ማሻሻያ ማድረግ በቂ አይደለም" ብለዋል።
አዲሱ እግድ የአገሪቱ ፓርላማ በአነስተኛ ጀልባዎች ወደ አገሪቱ ለሚገቡ ስደተኞች ሆቴሎችን ለማረፊያነት ጥቅም ላይ ማዋሉ ጠንከር ያለ ትችት ከቀረበበት እና ከክረምት እረፍት ከተመለሰ ከአንድ ቀን በኋላ የመጣ ነው።
ሰኞ ዕለት ይቬት ኩፐር መንግሥት በዩናይትድ ኪንግደም ጥገኝነት የተሰጣቸው ስደተኞች "ያለምንም ቅድመ ሁኔታ" ቤተሰቦቻቸውን ማምጣት ይችሉበት የነበረው መንገድ ለአዲስ አመልካቾች በጊዜያዊነት መታገዱን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ ሕጉ በጦርነቶች እና ግጭቶች የተለያዩ ቤተሰቦችን ለማገናኘት ከረዥም ዓመታት በፊት የወጣ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን በስደተኞች ጉዳይ ከዩናይትድ ኪንግደም ጎረቤቶች ጋር መስራት ባለመቻላቸው እግዱ አስፈልጓል ብለዋል።
አክለውም እንደ ዴንማርክ እና ስዊዘርላንድ ያሉ የአውሮፓ አገራት ስደተኞች ቤተሰቦቻቸውን ለማምጣት ማመልከቻ ከማስገባታቸው በፊት ቤተሰቦቻቸውን እንዲረዱ ለማስቻል ሁለት ዓመት እንዲጠብቁ ያደርጋሉ ብለዋል።
ከዚህ ጋር ሲነፃፀር በዩናይትድ ኪንገደም በአማካኝ ማመልከቻዎች በወራት ውስጥ እንደሚቀርቡ ጠቅሰው፤ በአብዛኛው ስደተኞቹ ለጥገኝነት የተሰጣቸውን ቤት ከመልቀቃቸው በፊት ጥያቄዎችን እንደሚቀርቡ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት በርካታ የስደተኛ ቤተሰቦች ቤት አልባ እንዳይሆኑ ምክር ቤቱን እርዳታ ይጠይቃሉ ሲሉ ጫናውን ገልፀዋል።
ቤተሰቦቻቸውን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለማምጣት የሚያመለክቱ ስደተኞች በርካታ ገደቦች ባለው መደበኛው የኢምግሬሽን ስርዓት ጉዳያቸው ይታያል።
በዚህ ዓመት በቤተሰብ የማገኛኘት መንገዱ ተጨማሪ ማሻሸያዎች ይደረግበታል ተብሎም ይጠበቃል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ባለፉት ወራት በስደተኞች እና ጥገኛ ጠያቂዎች አያያዝ ምክንኣት ከባድ ጫና ውስጥ ወድቋል።
የወግ አጥባቂዎች ፓርቲ አመራር የሆኑት ክሪስ ፍሊፕ የሕግ መሻሻሉን አስመልክተው መንግሥት የድንበር ቀውሱን መፍታት አለመቻሉ በመላው አገሪቱ የተቃውሞ ሰልፎች እንዲካሄዱ አድርጓል ብለዋል።
"ይህ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ ቢሆን እዚህም እዚያም የሚደረጉ ማስተካከያዎች በቂ እንዳልሆኑ ይረዳ ነበር" ብለዋል።
አክለውም ዩናይትድ ኪንግደምን በሕገ ወጥ መንገድ በአነስተኛ ጀልባዎች አቋርጠው የሚገቡ ስደተኞችን ወደ ምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር ሩዋንዳ ለማዘዋወር ተይዞ የነበረው እቅድ እንዲመልስም ጠይቀዋል።















