በዩናይትድ ኪንግደም ቁጣ እና ተቃውሞ የቀሰቀሰው የኢትዮጵያዊው ስደተኛ ክስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ከገባ በኋላ በቀናት ውስጥ በታዳጊ ሴቶች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ፈጽሟል በሚል ባለፈው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ላይ የተከሰሰው ኢትዮጵያዊ ጉዳይ በአገሬው ዜጎች ዘንድ ቁጣ እና ተቃውሞን ቀስቅሷል።
ሀዱሽ ገብረሥላሴ ቅባቱ የተባለው ግለሰብ ኤሲክስ በተባለችው ከተማ ውስጥ ከሚኖርበት የስደተኞች መጠለያ ሆቴል አቅራቢያ በሁለት ቀናት ውስጥ ፈጸመው ተብሎ የተጠረጠረበት የወሲባዊ ጥቃት ክስ በፍርድ ቤት እየታየ ነው።
ነገር ግን ይህ ክስተት በነዋሪዎች ዘንድ ስጋትን ፈጥሮ ላለፉት ሁለት ወራት ጥገኝነት ጠያቂዎች ያረፉበት ሆቴል እንዲዘጋ እና ስደተኞቹ ከከተማዋ እንዲወጡ የሚጠይቁ የተቃውሞ ሰልፎች አካሂደዋል።
ተመሳሳይ ስጋትም በሌሎች አካባቢዎች እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
ትናንት ማክሰኞ በድጋሚ ፍርድ ቤት የቀረበው ሀዱሽ ድርጊቱን አለመፈጸሙን ገልጾ ቢከራከርም፣ ሁለት የ14 ዓመት ልጆችን በከተማዋ ማዕከላዊ ክፍል ውስጥ ባገኘበት ጊዜ "ከእነሱ ልጅ መውለድ እንደሚፈልግ" እና ሊስማቸው ሞክሯል የሚል ክስ ለፍርድ ቤቱ ቀርቧል።
ይህን ክስተት ተከትሎም ተከታታይ ፀረ ስደተኛ የተቃውሞ እና ስደተኞችን የሚደግፉ ሰልፎች ሀዱሽ እና ሌሎች ጥገኝነት ጠያቂዎች ባረፉበት 'ዘ ቤል ሆቴል' አቅራቢያ ሲካሄዱ ሰንበተዋል።

በተጨማሪም የቀረበው ክስ የአካባቢው አስተዳደር ምክር ቤት መሪ በከተማዋ የሚገኘው የጥገኝነት ጠያቂዎች ማረፊያ የሆነው ሆቴል እንዲዘጋ እስከመጠየቅ ደርሰዋል።
በጀልባ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መግባቱ የተነገረው ሀዱሽ ዕድሜው 41 ዓመት እንደሆነ የተዘገበ ቢሆንም ለፍርድ ቤት በሰጠው ቃል ላይ የተጠቀሰው የተወለደበት ዘመን ዕድሜውን 38 ያደርገዋል።
የአገሪቱ ኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያዊ መሆኑ የተገለጸው ግለሰብ ሰኔ 22/2017 ዓ.ም. ወደ ዩናይትድ ኪግንደም በጥገኝነት ጠያቂነት የገባ ሲሆን፣ የተከሰሰበትን ድርጊት ፈጽሟል የተባለው ከስምንት ቀናት በኋላ ነው።
የሀዱሽ ጠበቃ ራፋኤል ፒጎት "እዚህ የገባው መደበኛ ባልሆነ መንገድ በጀልባ አማካኝነት እንደ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ ነው" በማለት ኢትዮጵያዊ መሆኑን እንዳረጋገጠላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ትንኮሳው ተፈጽሞባታል የተባለችው ታዳጊ በነጋታው ክስተቱን ለፖሊስ ሪፖርት ካደረገች በኋላ የኤሲክስ ፖሊስ ሁኔታውን እንዳወቀ ተገልጿል።
ክስተቱ በከተማዋ ከተሰማ በኋላ የነዋሪው መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን፣ የተቃውሞ አና የሰልፎች መነሻም ለመሆን በቅቷል።

ኤሲክስ የምትገኝበት አካባቢ የምክር ቤት አባል የሆኑት የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ መሪ ክሪስ ዋይትብሬድ "ክስተቱ በጣሙን የሚረብሽ እና እጅግ አሳሳቢ" በማለት የአካባቢው ባለሥልጣናት ሆቴሉ ለጥገኝነት ጠያቂዎች መጠለያነት መዋሉን መቃወማቸውን ገልጸዋል።
ይህንን ክስተት ተከትሎ ባለፈው ወር ፖሊስ እንዳለው እስከ ሁለት ሺህ የሚደርሱ ሰዎች የተሳተፉባቸው ተከታታይ ሰልፎች ከሆቴሉ ውጪ ተካሂደዋል።
እነዚህ ሰልፎች ስደተኞችን የሚቃወሙ ብቻ ሳይሆን የሚደግፉም ነበሩ። ሰልፎቹ በመጪዎቹ ቀናትም እንደሚካሄዱ ታውቋል።
ተቃዋሚዎቹ "ማኅበረሰባችንን ጠብቁ"፤ "ከውጭ ዜጎች ይልቅ የሴቶች እና የልጆች ደኅንነት ይቅደም" የሚሉ መፈክሮችን የያዙ ሲሆን፣ የቀኝ አክራሪ እንቅስቃሴ አራማጆችም ተሳትፈውበታል።
ኃይል የተቀላቀለባቸው ሰልፎች በተደረጉበት ወቅት ደግሞ በንብረት እና በፖሊስ ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሞከሩ የተወሰኑ ሰልፈኞች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
'ስታንድ አፕ ቱ ሬሲዝም' የተሰኘው የፀረ ዘረኝነት እንቅስቃሴ ቡድኖች ተቃውሞው የቀኝ አክራሪ ቡድኖች ተግባር መሆኑን በማመልከት "የዘረኝነት ጥቃትን በማበረታታት" ችግሩ እንዲባባስ እያደረጉ ነው ሲል ከስሷል።
ሀዱሽ እና ሌሎች ጥገኝነት ጠያቂዎች ጉዳያቸው እልባት እስኪያገኝ ድረስ በዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት አማካኝነት እንዲያርፉበት የተደረገው ሆቴል ከቀረበው ክስ ጋር ተያይዞ እንዲዘጋ ለፍርድ ቤት የቀረበው ጥያቄ በጊዜያዊነት ተቀባይነት አግኝቷል።















