የዩኬ መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎችን የሚያስተናግድበትን ስርዓት ለማሻሻል ማቀዱን አስታወቀ

ስደተኞች በፖሊስ መኮንኖች ተጅበው

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ውሳኔ የሚጠባበቁ እና ሆቴል የሚቆዩ ስደተኞችን ቁጥር ለመቀነስ እየተመለከተ ባለበት ወቅት የጥገኝነት ጠያቂዎችን ስርዓት ለማሻሻል ማቀዱን አስታወቀ።

መዝገቦችን በፍጥነት ለመመርመር ዓላማ ያደረገ አዲስ እና ገለልተኛ አካል ጉዳዮችን የሚመለከቱ ገለልተኛ ዳኞችን በመመደብ እንደሚሰራ ተናግሯል።

የአገር ውስጥ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር ተቀባይነት የሌላቸውን መስተጓጉሎች ለማስቀረት ተጨባጭ እርምጃዎች እየወሰዱ መሆኑን ገልፀዋል።

የአገሪቱ መንግሥት ጥገኝነት ጠያቂዎች ሆቴሎች ላይ የሚቆዩበትን ጊዜ እንዲቀንስ የሚደርስበት ግፊት ጨምሯል።

ሚኒስትሮች ሆቴሎችን ለማቆያነት መጠቀምን ለመቋጨት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃል የገቡ ቢሆንም፤ አሁን ላይ 32 ሺህ የሚሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች በሆቴሎች ይኖራሉ።

የአገር ውስጥ ሚኒስትር ኩፐር የጥገኛ ጠያቂዎችን ማመልከቻዎች ውሳኔ ለመስጠት በፍጥነት ቢሰራም፤ ይግባኝ በሚያቀርቡ ጥገኝነት ጠያቂዎች ላይ "ተቀባይነት የሌለው መዘግየት" ታይቷል ብለዋል።

አሁን ላይ ይግባኝ ያቀረቡ ስደተኞች ጉዳያቸው ዳግም እንዲታይ በአማካኝ ከአንድ ዓመት በላይ የሚፈጅባቸው ሲሆን፤51 ሺህ መዝገቦች ውሳኔያቸውን እየተጠባበቁ ነው።

ጥገኝነት ጠያቂዎች ማመልከቻቸው ውድቅ ከተደረገ በኋላ በታክስ ከፋዮች ገንዘብ መጠለያን ጨምሮ እንዲስተናገዱ ያደርጋሉ።

በመሆኑም የገለልተኛ ዳኞች ጉባዔ የይግባኝ መዝገቦችን እንዲመለከት የሚደረግ ሲሆን፤ ይህም ከፍርድ ቤቶች በበለጠ በፍጥነት እንደሚሰራ በሚኒስትሮች ታምኖበታል።

የዩኬ መንግሥት መዝገቦችን እንዴት ለማፋጠን እንዳሰበ በቀጣይ ዝርዝር መረጃ ለማቅረብ ቃል ገብቷል።

ወግ አጥባቂዎች ስርዓቱ ቀውስ ውስጥ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን፤ ሪፎርም ዩኬ የተባለው ፓርቲ ደግሞ ሕገ ወጥ ስደተኞች በገፍ እንዲባረሩ እየወተወተ ነው።

ባለፉት ሳምንታት ጥገኝነት ጠያቂዎች እንዲኖሩ በሚደረግበት ቦታ ቁጣ የተነሳ ሲሆን፤ ቅዳሜ ዕለት በመላው ዩኬ የሆቴሎችን ጥቅም ላይ መዋል በመቃዎም ሰልፎች ተካሂደዋል።

ካለፈው ሐምሌ ጀምሮ 'ኢፒንግ' የተባለው አካባቢ የተቃውሞ ሠልፎች ዋነኛ ስፍራ የሆነ ሲሆን፤ አንድ ጥገኝነት ጠያቂ የ14 ዓመት ታዳጊ ላይ ወሲባዊ ጥቃት በማድረስ መከሰሱን ተከትሎ የጥገኛ ጠያቂዎች መኖሪያ በሆነው ቤል ሆቴል በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገዋል።

ባለፈው ማክሰኞ የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከተፈቀደለት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሷል በሚል ለጥገኛ ጠያቂዎች በቤል ሆቴል የሚሰጠው መኖሪያ በጊዜያዊነት እንዲታገድ ውሳኔ አሳልፏል።

በሆቴሉ የሚኖሩ ጥገኛ ጠያቂዎች እስከ መስከረም 2 ድረስ መውጣት አለባቸው።

የዩኬ መንግሥት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለመቀልበስ ይግባኝ እንደሚል ጠቁሟል።

ይቬት ኩፐር መንግሥታቸው ሁሉም የጥገኝነት ጠያቂ ሆቴሎች ለመዝጋት ቁርጠኛ ነው ያሉ ሲሆን፤ ነገር ግን ተገቢ በሆነ መንገድ መመራት አለበት ብለዋል።