በጀልባ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ አውሮፓ ሲጓዙ የነበሩ ሦስት ታዳጊ እህትማማቾች ሰጥመው ሞቱ

የእህትማማቾቹ አስከሬን ወደ ደቡብ ጣልያን ላምፓዱሳ ተወስዷል

የፎቶው ባለመብት, RESQSHIP

የምስሉ መግለጫ, የእህትማማቾቹ አስከሬን ወደ ደቡብ ጣልያን ላምፓዱሳ ተወስዷል

በመካከለኛው ሜዲትራኒያን ባሕር ስደተኞችን አሳፍራ ስትጓዝ የነበረች አነስተኛ ጀልባ 1.5 ሜትር ከፍታ ባለው ማዕበል በተደጋጋሚ ተመትታ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲጓዙ የነበሩ ሦስት ታዳጊ እህትማማቾች መሞታቸውን የጀርመን የነፍስ አድን ሠራተኞች አስታወቁ።

በጀልባዋ ተሳፍረው ከነበሩ ሰዎች መካከል የእህትማማቾቹ እናት እና ወንድም እንዲሁም ሦስት ነፍሰጡሮች እና የሰባት ወር ጨቅላን ጨምሮ 65 ሰዎችን ማትረፍ መቻሉ ተገልጿል።

ሬስክሺፕ (RESQSHIP) የተሰኘው በጎ አድራጎት ድርጅት ስደተኞቹ "በአደገኛ ሁኔታ በተጨናነቀ" የጎማ ጀልባ ከሊቢያ ዙዋራ ከተማ መነሳታቸውን ገልጾ፣ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ "እየጨመረ የመጣው ውሃ ወደጀልባዋ መግባት ጀመረ" ብሏል።

ሊቢያ፤ ወደ ጣሊያኗ ደሴት ላምፔዱሳ ለመድረስ ተስፋ በማድረግ ሜዲትራኒያን ባህርን የሚያቋርጡ ስደተኞች መነሻ ናት።

ሬስክሺፕ ሰምጠው የሞቱት እህትማማቾች የዘጠኝ፣ 11 እና 17 ዓመት ታዳጊዎች መሆናቸውን በመግለጫው ላይ ገልጿል።

የበጎ አድራጎት ድርጅት ኮሙዩኒኬሽን አስተባባሪ ባርባራ ሳርቶሬ ቅዳሜ ዕለት አስከሬናቸው እንዴት እንደተገኘ ስትገልጽ፤ በሕይወት የተረፉት ሰዎች አንድ በአንድ እያወጡ ሳለ "ጩኸት ሰማን እና አንድ ሰው በጀልባው ውስጥ እና ወደ ውቅያኖሱ አመለከተን" ስትል ተናግራለች።

ሳርቶሬ "ከታች አስከሬኖች መኖራቸውን ተረዳን" ብላለች።

"ጀልባዋ በአደገኛ ሁኔታ ተጨናንቃ ነበር፤ ድቅድቅ ጨለማ ነበር፣ ውሃ ወደ ውስጥ እየገባ ነበር፣ ሰዎች ደነገጡ። በዛ ትርምስ ውስጥ፣ በጀልባዋ ውስጥ የተቀመጡት ሦስቱ እህትማማቾች ቀድመው ውሃ ውስጥ መስጠማቸውን ማየት አልተቻለም። የተረፉት ሰዎች ይህንን ሲያውቁ በጣም አስፈሪ ሁኔታ ነበር" ስትል ተናግራለች።

ሩስክሺፕ በሕይወት ከተረፉት መካከል ብዙዎቹ በጀልባው ውስጥ በገባው የውቅያኖሱ ውሃ እና ቤንዚን ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የኬሚካል ቃጠሎ ስለደረሰባቸው ሕክምና ያስፈልጋቸዋል ብሏል።

ቀደም ሲል ወደ ውቅያኖሱ የወደቀ አንድ ሰው አሁንም አለመገኘቱን የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።

የጣሊያን የባህር ጠረፍ ጠባቂዎች ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ 14 ሰዎችን በማውጣት ወደ ላምፔዱሳ የወሰዷቸው ሲሆን፥ የነፍስ አድን መርከቧ ከተረፉት ስደተኞች መካከል የቀሩትን እና የልጃገረዶቹ አስከሬን ይዛ ደርሳለች።

የነፍስ አድን ጀልባ ሠራተኛ የሆነችው ካትጃ ሽኒትዘር "በሦስቱ እህትማማቾች ላይ የደረሰው ነገር ሊታሰብ የማይቻል ነው፤ በስደት ላይ ያሉ ሰዎች ደህንነት በሚፈልጉበት ወቅት የሚገጥማቸው አደጋ ሊታሰብ የሚችል አይደለም።"

የበጎ አድራጎት ድርጅቱ የሟቾቹንም ሆነ የተረፉትን ዜግነት አልገለፀም።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኤጀንሲዎች በዚህ ዓመት ብቻ ከሰሜን አፍሪካ አገራት ሜዲትራኒያንን ለማቋረጥ ሲሞክሩ የነበሩ ከ 700 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ተናግረዋል።

የነፍስ ማዳኑ ስራ መጨመር እንደሚኖርበት ገልጸው፣ የተረፉ ሰዎች ከመርከቧ ሲወርዱ ለደኅንነታቸው ዋስትና መሰጠት አንደሚኖርበት ተናግረዋል።