አሜሪካ የውጭ አገር ወንጀለኞችን ወደ አፍሪካ ማባረሯ ሕጋዊ ነው?

የአሜሪካ አየር ኃይል አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ወታደራዊ አውሮፕላኖች ስደተኞችን ለማባረር ጥቅም ላይ ይውላሉ

የአሜሪካ አስተዳደር ወንጀለኞች ናቸው የሚላቸውን ስደተኞች የሚያባርርበት አዲስ መዳረሻ ለማግኘት ወደ አፍሪካ አህጉር ዓይኑን አዙሯል።

በርካታ ስደተኞች በማዕከላዊ እና ደቡብ አሜሪካ አገራት ሲላኩ፤ የሜክሲኮ፣ ምያንማር እና የመን የመሳሰሉ አገራትን ጨምሮ የ12 አገራት ስደተኞች ባለፈው ወር ወደ ኢስዋቲኒ እና ደቡብ ሱዳን ተልከዋል።

ሌሎች የአፍሪካ አገራት የትውልድ አገራቸው ለመቀበል አሻፈረኝ ያሏቸውን ስደተኞች እንዲቀበሉ በዩናይትድ ስቴት የማግባባት ስራ እየተሰራ መሆኑን የአሜሪካ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስደተኞችን የማባረር እቅድ ባለፈው ዓመት የምርጫ ዘመቻቸውን ሲያካሂዱ ከፍተኛ ድጋፍ አግኝቷል።

ይሁን እንጂ የመንግሥታቱ ድርጅት እና የሰብዓዊ መብት ቡድኖች እንቅስቃሴው እንዳሳሰባቸው እና የስደተኞቹ የትውልድ አገር ወዳልሆነ ወደ ሦስተኛ አገር ማባረሩ ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ ነው ይላሉ።

በዓለም አቀፍ ሕግ ወደ ሦስተኛ አገር ማባረር ሕጋዊ ነው?

ወደ ሦስተኛ አገር ማባረር በተወሰኑ ሁኔታዎች ብቻ ሕጋዊ ሊሆን ይችላል።

በአሜሪካ አልበኒ የሕግ ትምሕርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት ሬይ ብሬሺያ "ወደ ሦስተኛ አገር ማባረር ሰፋ ባለው የጥገኝነት ፅንሰ ሀሳብ አንፃር መታየት አለበት" ይላሉ።

"አንድ ሰው ወደ ትውልድ አገሩ ለመመለስ ደኅንነት ከሌለው መመለስ አይቻልም። ስለዚህ ሦስተኛ አገር አስተማማኝ አማራጭ ሲሰጥ ይችላል የሚል ዓለም አቀፍ መርኅ አለ" ሲሉ ያብራራሉ።

ይህ መርኅ ለስደተኞች የትውልድ አገር ብቻም ሳይሆን ስደተኞች ለሚላኩበት ሦስተኛ አገራትም የሚሰራ ነው።

ሦስተኛው አገር ደኅንነቱ አስተማማኝ ካልሆነ ዓለም አቀፍ ሕግን ይጥሳል ማለት ነው።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ፍርድ ቤት እ.አ.አ በ2023 የብሪታኒያ መንግሥት እቅድ የነበረውን ጥገኛ ጠያቂዎችን ወደ ሩዋንዳ የመላክ እንቅስቃሴን ውድቅ ማድረጉ የዚህ መርኅ አካል ነው።

የስደተኞቹ ጉዳይ በሕግ ሂደት መታየቱም አስፈላጊ ነው።

ስደተኞች የሚላኩበት አገር አደገኛ ከሆነ ውሳኔውን የመንግሥታቱ ድርጅት ሪፖርት እና በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ግኝትን እንደ ማስረጃ ተጠቅመው የመቃወም እና የመከራከር መብት አላቸው።

ፍርድ ቤቶችም ስጋት እና አደጋውን በሚገባ እንዲያዩ ይጠበቃል።

ስቃይ እና ሌሎች ጭካኔ፣ ኢ-ሰብዓዊ ወይም ክብረ ነክ አያየዝ ወይም ቅጣት ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት ልዩ ራፖርተር የሆኑት ዶ/ር አለስ ኤድዋርድስ "ፍርድ ቤቱ ስደተኞቹ ምን አይነት የሕግ ሁኔታ እንደሚኖራቸው፣ ይታሰሩ ከሆነ እና ምን አይነት መጠለያ እንደሚሰጣቸው መመርመር አለበት" ይላሉ።

ይሁን እንጂ በርካታ ስደተኞች በጊዜ የሕግ እርዳታ ለማግኘት ይቸገራሉ።

ፕሮፌሰር ብሬሺያ እንደሚሉት "ከፍተኛ ጥረት እና በአፋጣን እርምጃ የሚወስድ የሕግ ባለሙያ ማግኘት ያስፈልግል"።

"ሕጋዊ መንግዱ ለሁሉም ሰው ላይገኝ ይችላል" ሲሉ ያክላሉ።

ወደ ኢስዋቲኒ እና ደቡብ ሱዳን ስደተኞችን መላክ ዓለም አቀፍ ሕግን ይጥሳል?

በጆርጅታውን ዩኒቨርስቲ የሕግ ማዕከል ፕሮፌሰር ዴቪድ ሱፐር "በእርግጠኝነት በሁለት መልኩ ይጥሳል" ይላሉ።

"አሜሪካ ለስደተኞቹ ጉዳያቸውን ኢንዲከራከሩ የሰጠችው እድል ስለመኖሩ ምንም ማስረጃ የለም። እናም ሰዎችን ችግር ሊገጥማቸው ወደሚችልበት አገር መላክ የተፈቀደላቸው አይደለም።

"እስዋቲኒ እና ደቡብ ሱዳን በሰብዓዊ መብት አያያዛቸው ከባድ ጥያቁ የሚነሳባቸው አገራት ናቸው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ግንቦት ስደተኞችን ወደ ደቡብ ሱዳን ለመላክ በረራው ከተነሳ በኋላ እርምጃውን በመቃወም ለፍርድ አቤቱታ ቀርቧል።

ዳኛው ስደተኞችን ለማባረር መሞከሩ ስደተኞቹ ወደ ሦስተኛ አገራት ሲላኩ የሚገጥማቸውን ችግር የማቅረብ መብት እናዳላቸው የወሰኑትን ውሳኔ የጣሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አምርቶ ስደተኞች ማባረሩ የተፈቀደ ቢሆንም ደቡብ ሱዳን ስደተኞቹን ለመቀበል ደኅንነት ያለባት አገር ስለመሆኗ ግን አልገለፀም።

"እያየን ያለነው ተመሳሳይ ጉዳይ ሰዎች በአብዛኛው የሕግ እርዳታ ሲያስፈልጋቸው እንደተነፈጉ ነው። እናም ሂደቱ ከረፈደ በኋላ ይጀመራል" ይላሉ ዶ/ር ኤርዋርድስ።

"በዚህ ጉዳይ ስደተኞቹ ወደ አሜሪካ የወታደራዊ ካምፕ እየተወሰዱ ነበር። ይህም ትልቅ ችግር ያለበት ነው" ይላሉ።

አክለውም ፍርድ ቤቶች በተለይ ደግሞ የሰዎች መሠረታዊ መብቶች አደጋ ላይ ሲሆኑ ከፖለቲካ ነፃነታቸውን መጠበቅ አለባቸው ብለዋል።

ፕሮፌሰር ብሬሺያ እንደሚሉት የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አደገኛ ሁኔታ አመላካች ሊሆን ይችላል።

"አስተዳደሩ ሰዎች ፍርድ ቤት ከመድረሳቸው በፊት ከዚህ የበለጠ ስደተኞችን በፍጥነት ለማስወጣት ሊያበረታታ ይችላል የሚል ስጋት አለ" ብለዋል።

ኢስዋቲኒ እና ደቡብ ሱዳን ደኅንነታቸው የተጠበቁ አገራት ናቸው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የፍርድ ሂደትን ከመከልከል በተጨማሪ ስደተኞች ደኅንነት ወደሌላቸው አገራት መላካቸው ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ ነው።

በአሁኑ ሰዓት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ወደ ደቡብ ሱዳን ሁሉም ዓይነት ጉዞዎች እንዳይደረጉ ምክር አስቀምጧል። ለዚህም ምክንያት ሲዘረዝር ወንጀል፣ የትጥቅ ግጭት እና እገታን ያነሳል።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ የዓለማችን ደሃ አገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ለመመለስ ጫፍ ላይ ናት ተብላለች።

"በደቡብ ሱዳን ሁከት፣ አለመረጋጋት እና ግጭት በመቀጠሉ ምክንያት ሕግና ስርዓቱ ላይ ከፍተኛ ስጋት አለ" ይላሉ ዶ/ር ኤድዋርድስ።

እንደ ፖለቲከኛው ኤግል ሪክ ማቻር ከሆነ ወደ ደቡብ ሱዳን የተላኩ ስደተኞች በዋና ከተማዋ ጁባ እስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ።

የደቡብ ሱዳን መንግሥት የስደተኞቹን መገኛም ሆነ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚታሰሩ ማረጋገጫ አልሰጠም።

በደቡባዊ አፍሪካ ወደብ አልባ አነስተኛ አገር በሆነችው ኢስዋቲኒ ስደተኞቹ ማረሚያ ቤት እንደሚገኙ እና በዓለም የፍልሰተኞች ድርጅት እርዳታ ወደ አገራቸው እንደሚመለሱ የአገሪቱ ሹማምንት ተናግረዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የኢስዋቲኒ እስር ቤቶች ከአቅማቸው በላይ በመያዝ መጨናነቅ፣ ደካማ የአየር ዝውውር እና የምግብ እና ጤና አገልግሎት ጉድለቶች እንዳሉባቸው ይናገራል።

የኢስዋቲኒ መንግሥት ቃል አቀባይ ታቢል መደሉሊ ለቢቢቢ "ከማኅበረሰቡ ጋር ለመዋኸድ ረጅም ጊዜ ይቆያሉ ብለን አንገምትም" ብለዋል።

ስደተኞቹ በአገሪቱ ውስጥ ለምን ያህል ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉ አሊያም የተፈረደባቸውን የእስር ጊዜ መጀመሪያ ይጨርሳሉ ወይ ለሚለው ምንም ፍንጭ አልሰጡም።

የአሜሪካ መንግሥት ወደ ኢስዋቲኒ የተላኩት ስደተኞች ሕፃናትን መድፈር፣ ግድያ እና ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ "አረመኔያዊ" ወንጀሎችን የፈፀሙ ናቸው ይላል።

በኢስዋቲኒ ውሳኔውን የሚቃረን እንቅስቃሴ እያደገ ነው።

የአገሪቱ ትልቁ ተቃዋሚ ፖርቲ የሆነው የሕዝቦች አንድነት ሲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ፑዲሞ) የሁለቱ አገራት ስምምነት "በማባረር ስም ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ነው" ብሏል።

የዲሞክራሲ ተሟጋች የሆኑት ላኪ ሉኩሌ አገሪቱ "የወንጀለኞች መጣያ ሜዳ" መሆን የለባትም ይላሉ።

ፕሮፌሰር ሱፐር ዓለም አቀፍ ሕግ ቢጣስም እንኳ አሜሪካ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶችን እውቅና ስለማትሰጥ ተጠያቂ የምትሆን አይመስልም ይላሉ።

"ይህ መከልከል ይመስላል፤ አሜሪካ ብትመጡ እንደዚህ አይነት በጣም ከባድ አቀባበል ይገጥማችኋል የሚል መልዕክት የሚልክ ነው" ብለዋል።

ሕጋዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ቢገባም ወደ ሦስተኛ አገር ስደተኞችን ማስወጣት ተጋላጭ ሰዎችን በማያውቁት ከባቢ አነስተኛ ድጋፍ እና የሕግ ከለላ ይጠብቃቸዋል ይላሉ ዶ/ር ኤድዋርድስ።

"በጣም ክፍተት ያለበት ሀሳብ ነው"።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ሁሉንም የማባረር እንቅስቃሴ እንዲታገድ እየሞከሩ ሳይሆን ሰዎች የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወደሚፈፀምባቸው አገራት እንዳይመለሱ ነው ሲሉም ያክላሉ።

ተቀባይ አገራት ምን ያገኛሉ?

ስደተኞችን የማስወጣት ስምምነቶች በጣም ሚስጥራዊነታቸው የተጠበቀ ነው።

የኢስዋቲኒ መንግሥት ቃል አቀባይ አገራቸው ስደተኞችን የምትቀበልበት ምክንያት "ለአሁኑ ሚስጥራዊ መረጃ ነው" ብለዋል።

ይሁን እንጂ የኢስዋቲኒ እና ደቡብ ሱዳን መንግሥታት ከአሜሪካ ጋር ያላቸው ጠንካራ ግንኙነትን እንደ ቁልፍ ተነሳሽነት ጠቅሰዋል።

ፕሮፌሰር ብሬሺያ አንዳንድ አጋርት ባይስማሙ የቪዛ ገደብ ወይም ታሪፍን የመሰሉ የአሜሪካን የአፀፋ እርምጃ ይፈራሉ ይላሉ።

ባለፈው ሚያዚያ ደቡብ ሱዳን ስደተኞችን የማትቀበል ከሆነ ለደቡብ ሱዳናውያንን የተሰጠ ሁሉም ቪዛ እንደሚሻር አሜሪካ አሳውቃ ነበር።

አሁን አገሪቱ ስደተኞችን መቀበሏን ተከትሎ እዚህ ውሳኔ ላይ ማሻሻያ ስለመደረጉ ግልፅ አይደለም።

የፖለቲካ ተሟጋች የሆኑት ማቻር ደቡብ ሱዳን የተስማማችው በምክትል ፕሬዝዳንት ቤንጃሚን ቦል ሜል ላይ አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ እንድታነሳ ነው ይላሉ።

የአሜሪካ መንግሥት በምክትል ፕሬዝዳንቱ ላይ እ.አ.አ በ2021 በሙስና ወንጀል ጠርጥራ ማዕቀብ የጣለች ሲሆን በዚህ ዓመት ማዕቀቡ ታድሷል።

ነገር ግን እንደ ናይጀሪያ ያሉ አገራት አሜሪካን እየተገፉ ነው።

የናይጀሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሴፍ ቱጋር የቬንዙዌላ ስደተኞችን ለመቀበል የቀረበውን ጥያቄ ውድቅ ሲያደርጉ "የራሳችን በቂ ችግሮች አሉን" ብለዋል።

ዶ/ር ኤድዋርድስ እንደዚህ አይነት ስምምነቶች በአመዛኙ ከማበረታቻዎች ጋር ነው የሚቀርቡት።

ከዚህ ቀደም በተደረጉ የሦስተኛ አገር የስደተኞች ቅበላ ዳጎስ ያለ ገንዘብ እንዲሁም የወታደራዊ እና ደኅንነት ትብብሮች የማዕቀፉ አካል ነበሩ።

ባለፈው መጋቢት የፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የቬንዙዌላ ስደተኞችን ኤል ሳቫዶር እንድትቀበል ስድስት ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍል ተናግሯል።