ናይጄሪያ 'የራሷ በቂ ችግር' ስላላት ከአሜሪካ የሚባረሩ ስደተኞችን እንደማትቀበል አስታወቀች

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ቱጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ቱጋር

ናይጄሪያ የቬንዙዌላ ስደተኞችን ወይም የሌላ አገር ስደተኞችን ከአሜሪካ እንድትቀበል ከትራምፕ አስተዳደር ለሚደርስባት ጫና እንደማትበገር የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዩሱፍ ቱጋር ተናገሩ።

ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው የ1990ዎቹ አሜሪካዊ ራፐር ቡድን ፐብሊክ ኢነሚን (Public Enemy) ጠቅሰዋል።

"በዝነኞቹ የአሜሪካ ራፕ ቡድን ፐብሊክ ኢነሚ ቃል. . . የቡድኑ አባል የሆነው ፍላቫ ፍላቭ ያለውን ታስታውሳላችሁ 'ፍላቫ ፍላቭ የራሱ ችግሮች አሉበት።ወዳጄ፣ ላንተ ምንም ማድረግ አልችልም" ሲሉ ለአንድ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ተናግረዋል።

"ከ230 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አለን" ብለዋል ሚኒስትሩ።

የሚኒስትሩ አስተያየት የተሰማው ዋሽንግተን ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገሯ ለማባረር የምትከተለውን ፖሊሲውን በማይቀበሉ አገራት ላይ ቪዛ ለመገደብ እና ታሪፍ ለመጨመር ማስፈራራቷን ተከትሎ ነው።

"ናይጄሪያ 300 የቬንዙዌላ ስደተኞችን እንድትቀበል ማድረግ ኢፍትሃዊ ነው" ሲሉ በቅርቡ አሜሪካ በናይጄሪያውያን ተጓዦች ላይ ያደረገችው የቪዛ ገደብ "አጸፋዊ" ሳይሆን ጫና የማድረግ ስልት መሆኑን ጠቁመዋል።

አክለውም "የቬንዙዌላ እስረኞችን ለመቀበል ከተስማማን እኛን ከሚተቹን መካከል ትሆናለህ" ብለዋል።

ከሰኞ ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም. ጀምሮ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለናይጄሪያ፣ካሜሮን እና ኢትዮጵያ ዜጎች የሚሰጠው ስደተኛ ያልሆኑ እና የዲፕሎማቲክ ቪዛዎች ለአንድ ጊዜ መግቢያ ብቻ የሚያገለግሉ እና የሦስት ወራት ቆይታ ብቻ እንደሚኖራቸው አስታውቋል።

ሚኒስቴሩ ይህ ውሳኔ ከዚህ በፊት ከነበረው አሰጣጥ ፍፁም የተለየ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከአገራት ጋር በሚኖር ግንኙነት መሠረት የተደረገ ዓለም አቀፋዊ ማስተካከያ አካል ነው ብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ጥቅም የሚፃረሩ የብሪክስ ኅብረት ፖሊሲዎችን የሚደግፉ አገራት ላይ በ10 በመቶ ተጨማሪ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተዋል።

ብሪክስ የምዕራባውያንን ፖለቲካዊ እና የምጣኔ ሃብት አቅም ለመገዳደር የተነደፈ የ11 ታዳጊ አገራት ጥምረት ነው።

ባለፈው ዓመት የብሪክስ አባላት ዝርዝር ከመጀመሪያዎቹ ብራዚል፣ሩሲያ፣ሕንድ፣ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ በተጨማሪ፤ ግብፅ፣ኢትዮጵያ፣ኢንዶኔዥያ፣ኢራን፣ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ይገኙበታል።

ናይጄሪያ የብሪክስ ሙሉ አባል ባትሆንም በጥር ወር ዘጠነኛ አጋር አገር ሆናለች።

ሚስተር ቱጋር የታሪፍ ጭማሪ ማስፈራርያ "በብሪክስ ከመሳተፋችን ጋር የተያያዘ አይደለም" ብለዋል።

አክለውም "በተጨማሪም አሜሪካ የአፍሪካ አገራት ከአሜሪካ የሚባረሩ ቬንዙዌላውያንን፣ የተወሰኑት በቀጥታ ከእስር ቤት እንደወጡ እንዲቀበሉ ከፍተኛ ጫና እያደረገች መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል" ብለዋል።

"እንደ ናይጄሪያ ያለ አገር የቬንዙዌላውያን እስረኞችን ለመቀበል ይቸገራል። እኛ የራሳችን በቂ ችግሮች አሉብን። ተቆጥተው ስለተናገሩ የቬንዙዌላ ስደተኞችን መቀበል አንችልም።"

በአሜሪካ የትራምፕ የሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ ያላቸውን አቋም የተቃወሙ ሰዎች አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, Los Angeles Times via Getty Image

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ የትራምፕ አስተዳደር የሰነድ አልባ ስደተኞች ላይ ያለውን አቋም የተቃወሙ ሰዎች አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን ገልፀዋል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይልቁንም ናይጄሪያ በአሜሪካ የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሚፈለጉ ጋዝ፣ ወሳኝ ማዕድናት እና ብርቅዬ ማዕድናት ስላሏት "ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ለማድረግ" ትፈልጋል ብለዋል።

ሚኒስትሩ ናይጄሪያ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ለመፈለግ ምን እየሠራች እንደሆነ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ አገሪቱ ከአሜሪካ ጋር ልዩነቶችን ለመፍታት እየተወያየች ነው ብለዋል።

የሚኒስትር ቱጋር አስተያየት የመጣው የትራምፕ አስተዳደር የላይቤሪያ፣ የሴኔጋል፣ የሞሪታኒያ፣ የጋቦን እና የጊኒ ቢሳው መሪዎች የትውልድ አገራቸው የማይቀበሉዋቸውን ወይም ለመውሰድ የዘገዩ ስደተኞችን እንዲቀበሉ እየገፉ መሆኑን 'ዎል ስትሪት ጆርናል' የውስጥ ሰነዶችን እና ምንጮችን ጠቅሶ ከዘገበ በኋላ ነው።

ጋዜጣው እንዳለው አምስቱ የአፍሪካ መሪዎች ረቡዕ ዕለት በዋይት ሐውስ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት አገራቱ ከአሜሪካ የሚባረሩ ሰነድ አልባ ስደተኞችን እንዲቀበሉ አስቀድሞ ተጠይዋል።

ጋዜጣው ይህንን የትራምፕ አስተዳደር ስትራቴጂ ሕገወጥ ስደተኞችን ከአገር የማባረር ዘመቻ እና በውጭ ፖሊሲያቸው መካከል ያለ "አደገኛ" መደራረብ ብሎ ገልጾታል።

ከአምስቱ የምዕራብ አፍሪካ አገራት ጥያቄውን የተቀበለ ይሁን አይኑር ግልፅ አይደለም።

የላይቤሪያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሳራ ቢሶሎው ኒያንቲ በዚህ ጉዳይ ከዋሽንግተን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንዳልነበራቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ወደ ላይቤሪያ ስለሚመጡ ስደተኞችም ሆነ ወንጀለኞች ውይይት አላደረግንም።"

ቢሆንም፣ ትራምፕ ከአምስቱ መሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ሃሳቡን ማንሳታቸው ታውቋል።

በመክፈቻ ንግግራቸው ወቅት "ከቪዛ በላይ የሚቆዩ ሰዎችን ቁጥር ዝቅ ለማድረግ እና ደኅንነቱ በተጠበቀ የሦስተኛ አገር ስምምነቶች ላይ መቀራረብ እንደምንችል ተስፋ አደርጋለሁ" ብለዋል ።

በያዝነው ወር መጀመሪያ አሜሪካ ስምንት ሰነድ አልባ ሰዎችን ወደ ደቡብ ሱዳን አባርራለች።

ሌሎች ቢያንስ አራት የአፍሪካ አገራት ስደተኞችን ለመውሰድ በአሜሪካ ፍርድ ቤት ቀርበዋል ተብሏል። እነሱም ቤኒን፣ ኢስዋቲኒ፣ ሊቢያ እና ሩዋንዳ ናቸው።