ከአሜሪካ የተባረሩ ስምንት ስደተኞችን ያሳፈረ አውሮፕላን ደቡብ ሱዳን ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በትራምፕ አስተዳደር ከአሜሪካ ተባርረው በጂቡቲ በሚገኝ የአሜሪካ የጦር ሠፈር ለአንድ ወር ያህል ተቀምጠው የነበሩ ስምንት ስደተኞችን ያሳፈረው አውሮፕላን ደቡብ ሱዳን ደረሰ።
ፍልሰተኞቹ ከአገር እንዳይባረሩ ለማድረግ የተለያዩ የሕግ ጥረቶችን ቢያደርጉም ተቀባይነት ባለማግኘታቸው ወደ ደቡብ ሱዳን ተልከዋል።
ስደተኞቹ የሕግ ክርክር ውስጥ ስለነበሩ በጅቡቲ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሠፈር ውስጥ እንዲቆዩ ተደርገው ነበር።
ሰዎቹ የተባረሩት አርብ በአሜሪካ የነፃነት በዓል ቀን ነው ሲሉ የአገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤቱ ረዳት ፀኃፊ ትሪሻ ማክላውሊን በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
"ይህ ለሕግ የበላይነት፣ ለአሜሪካ ሕዝብ ደህንነት እና ጥበቃ ድል ነበር" ሲል ማክላፍሊን ተናግረዋል።
በጁባ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሰሩ ሁለት ባለስልጣናት ከአሜሪካ የመጡ ስደተኞችን የያዘ አውሮፕላን ቅዳሜ ደቡብ ሱዳን መግባቱን ለሮይተርስ የዜና ወኪል አረጋግጧል።
እንደ ጠበቆቻቸው መረጃ ከሆነ ስምንቱ ስደተኞቹ ከኩባ፣ ላኦስ፣ ሜክሲኮ፣ ምያንማር፣ሱዳን እና ቬትናም የመጡ ናቸው።
ወደ ደቡብ ሱዳን መባረራቸው ጭካኔ እና ያልተለመደ ቅጣት የሚከለክለውን የአሜሪካን ሕገ መንግሥት የሚጻረር ነው ሲሉ ተከራክረዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ግለሰቦቹ በከባድ ወንጀሎች የተከሰሱ መሆናቸውን ገልፀው ከእነዚህም መካከል አንዱ የደቡብ ሱዳን ዜጋ ነው ብለዋል።
ደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት አፋፍ ላይ መሆኗን የሚገልጹ ማስጠንቀቂያዎች ከተለያዩ አካላት እየተሰሙ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድረ ገጽ ዜጎቹ በወንጀል፣ በአፈና እና በትጥቅ ግጭት ምክንያት ወደ ደቡብ ሱዳን እንዳይጓዙ ያስጠነቅቃል።
ነገር ግን ከአሜሪካ የተባረሩ ስምንት ሰዎች አሁን ወደ ዋና ከተማዋ ጁባ ተወስደዋል።
የአሜሪካ ፌደራል ፍርድ ቤት ለጊዜው ወደ ደቡብ ሱዳን እንዳይወሰዱ አግዶ የነበረ ሲሆን በምትኩ ጅቡቲ በሚገኘው የአሜሪካ ጦር ሰፈር ከአንድ ወር በላይ ቆይተዋል።
ቀጥሎ ምን እንደተከሰተ እስካሁን ድረስ ግልጽ አይደለም።
ከዚህ ቀደም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደቡብ ሱዳን ከአሜሪካ የተባረሩ ዜጎቿን ለመቀበል ዳተኛ በመሆኗ ምክንያት የደቡብ ሱዳን ፓስፖርት ለያዙ የተሰጠ ማንኛውም ቪዛ መሰረዙ ይታወቃል።
ማርኮ ሩቢዩ በወቅቱ "የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግሥት ወደ አገራቸው የሚመለሱ ዜጎቹን በወቅቱ ባለመቀበሉ" ለችግሩ ተጠያቂ መሆኑን ገልጸው ነበር።
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሚከተሉት አዲሱ የኢሚግሬሽን ፖሊሲ የተነሳ ሕገ ወጥ ስደተኞችን "በጅምላ ከአገር" እያስወጡ ነው።
በግንቦት ወር በቦስተን ለሚገኝ የፌደራል ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን አስገብተው የነበሩ ጠበቆች የምያንማር እና ቬትናም ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ሰነድ አልባ ስደተኞችን የጫነ አውሮፕላን ደቡብ ሱዳን መድረሱን ተናግረው ነበር።
ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት፣ የአሜሪካ መንግሥት ስደተኞችን ወደ ሦስተኛ አገር ከመላኩ በፊት ጉዳያቸውን ለማስረዳት እና ለመከራከር "ተገቢውን ዕድል" መስጠት እንዳለበት ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
ይሁን እንጂ ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፕሬዝዳንት ትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን ከአገራቸው ባለፈ ወደ ሦስተኛ አገር ማባረር እንዲችል ፈቅዷል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት መስሪያ ቤት በወቅቱ ውሳኔውን "ለአሜሪካ ሕዝቦች ደኅንነት እና ጥበቃ ድል ነው" ብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር ስምንቱ ስደተኞች በአሜሪካ ግድያ፣ እሳት ቃጠሎ እና በጦር መሳሪያ ዝርፊያን ጨምሮ "አስከፊ ወንጀሎችን" የፈፀሙ ናቸው ብሏል።
የስደተኞቹ ጠበቃ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ባስገቡት ማመልከቻ አብዛኞቹ ስደተኞች ወንጀለኛ ተብለው የተፈረደባቸው አይደሉም ብለው ነበር።
ከሳሾቹን የወከለው ብሔራዊ የኢሚግሬሽን ሙግት ትብብር የፍርድ ቤቱን ውሳኔ "አስፈሪ" ብሎታል።
የትብብሩ ስራ አስፈፃሚ ትሪና ሪልሙቶ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ደንበኞቻቸውን "ለስቃይ እና ሞት" ያጋለጠ እንደሆነ ተናግረዋል።
ትራምፕ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የወሰዱት የታችኛው ፍርድ ቤት የወሰነውን ባለፈው ወር የቦስተን ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ውሳኔውን ባለመቀልበሱ ነው።
ደቡብ ሱዳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካ አለመረጋጋት እና በግጭት እየታመሰች ትገኛለች።
















