አሜሪካ እስያውያንን ወደ ደቡብ ሱዳን ማባረሯን ጠበቆች ለፍርድ ቤት አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ሁለት እስያውያንን በሕገ ወጥ መልኩ ወደ ደቡብ ሱዳን ማባረሩን ጠበቆች ለፍርድ ቤት ተናገሩ።
በቦስተን ለሚገኝ የፌደራል ፍርድ ቤት አቤቱታቸውን ያስገቡት ጠበቆች ማክሰኞ ዕለት የምያንማር እና ቬትናም ዜጎችን ጨምሮ በርካታ ሰነድ አልባ ስደተኞችን የጫነ አውሮፕላን ደቡብ ሱዳን አርፏል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም ፍርድ ቤት በሰጠው ትዕዛዝ መሰረት፣ የአሜሪካ መንግሥት ስደተኞችን ወደ ሦስተኛ አገር ከመላኩ በፊት ጉዳያቸውን ለማስረዳት እና ለመከራከር "ተገቢውን ዕድል" መስጠት እንዳለበት ትዕዛዝ አስተላልፎ ነበር።
ቢቢሲ ለአገር ውስጥ ደህንነት መስርያ ቤትን ጉዳዩን በተመለከተ ጥያቄ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።
ደቡብ ሱዳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካ አለመረጋጋት እና በግጭት እየታመሰች ትገኛለች።
ማክሰኞ ዕለት ናሽናል ኢሚግሬሽን ሊቲጌሽን አሊያንስ ከተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት የተውጣጡ ጠበቆች የፌደራል ፍርድ ቤቱ ከአገር መባረሩ በፍጥነት እንዲቆም ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቀው ነበር።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዝያ 18 ብሪያን መርፊ የተባሉ ዳኛ ሰነድ አልባ ስደተኞች ወደ ሦስተኛ አገር ከመላካቸው በፊት ጉዳያቸውን በሚገባ የማስረዳት እና የመከራከር ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ትዕዛዝ አስተላልፈው ነበር።
የተወሰኑ ስደተኞች ወደ ሊቢያ ይላካሉ የሚል ዘገባ ከወጣ በኋላ በባይደን የስልጣን ዘመን የተሾሙት መርፊ፣ የትኛውም የመንግሥት እርምጃ ይህንን የጣሰ መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል።
የምያንማር ዜጋ የሆነው ስደተኛ ጠበቆች ማክሰኞ ዕለት ለፍርድ ቤት ያስገቡት ማመልከቻ ደንበኛቸው ውስን እንግሊዘኛ የሚናገር መሆኑን ገልፀው፣ የቴክሳስ ግዛት ስደተኛ ማቆያ ማዕከል እንዲፈርም ያቀረበለትን ሰነድ አልፈርምም ማለቱን ተናግረዋል።
ማክሰኞ ማለዳ ጠበቃዋ ደንበኛዋ በአሜሪካ የስደተኞች እና ጉሙሩክ መሥርያ ቤት አለመቅረቡን በመረዳቷ ለማዕከሉ ኢሜል መላኳን በክስ ማመልከቻዋ ላይ ገልጻለች።
በወቅቱ ከአሜሪካ እንዲባረር መደረጉ አንደተገለጸላት አብራርታለች።
ወደ የት አገር አንደተባረረ የጠየቀችው ጠበቃዋ "ደቡብ ሱዳን" የሚል ምላሽ በኢሜል ማግኘቷን ተናግራለች።
ጠበቃዋ አክላም ሌላ የቬትናም ዜግነት ያለው ግለሰብ "ተመሳሳይ እጣ ፈንታ ገጥሞታል" ካለች በኋላ፣ ልክ እንደ ምያንማራዊው ሁሉ "በተመሳሳይ በረራ ውስጥ ነበር ወይንም ነው" ብላለች።
የቬትናማዊው ግለሰብ የትዳር አጋር ለጠበቃው በላከችው ኢሜል "እባካችሁ እርዱኝ" ብላለች።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው ከግለሰቦቹ ጋር ሌሎች የላኦስ፣ታይላንድ፣ፓኪስታን እና ሜክሲኮ ዜግነት ያላቸው 10 ግለሰቦች አብረው ነበሩ።
የስደተናው ባለቤት በኢሜል መልዕክታቸው "ይህንን እንዲያደርጉ ሊፈቀድላቸው አይገባም" ብለዋል።
የአሜሪካ መንግሥት የጉዞ ማስጠንቀቅያ "አገሪቱ ውስጥ ባለው ወንጀል፣ እገታ እና በትጥቅ የታገዘ ግጭት የተነሳ ወደ ደቡብ ሱዳን አትጓዙ" ሲል ያስጠነቅቃል።
እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2011 ነጻነቷን ያገኘችው ደቡብ ሱዳን ደም አፋሳሽ በሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ አልፋለች።












