አሜሪካ ለናይጄሪያውያን የምትሰጠውን የቪዛ ቆይታ ጊዜ ማሳጠሯን አሳወቀች

የአሜሪካ እና የናይጄርያ ባንዲራዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቪዛ ፖሊሲዎች በቀጣይ በሚደረግ ግምገማ ላይ የተመሰረቱ ናቸው ብሏል

አሜሪካ ስደተኛ ያልሆኑ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ግዛቷ ለሚገቡ ናይጄሪያውያን የምትሰጠው ቪዛ ላይ የፖሊሲ ለውጦችን ማድረጓን አስታወቀች።

በዚህ ውሳኔ መሠረት ናይጄሪያውያን ተጓዦች ወደ አሜሪካ በሚገቡበትን ቪዛ የቆይታ ጊዜ እና ቅድመ ሁኔታ ላይ ለውጥ አድርጋለች።

ከሰኞ ሐምሌ 1/2017 ዓ.ም. ጀምሮ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለናይጄሪያ ዜጎች የሚሰጠው ስደተኛ ያልሆኑ እና የዲፕሎማቲክ ቪዛዎች ለአንድ ጊዜ መግቢያ ብቻ የሚያገለግሉ እና የሦስት ወራት ቆይታ ብቻ ይኖራቸዋል።

ሚኒስትሩ ይህ ውሳኔ ከዚህ በፊት ከነበረው አሰጣጥ ፍፁም የተለየ መሆኑን ጠቅሶ፣ ከአገራት ጋር በሚኖር ግንኙነት መሠረት የተደረገ ዓለም አቀፋዊ ማስተካከያ አካል ነው ብሏል።

ከዚህ በፊት ለናይጄሪያውያን የሚሰጠው ቪዛ የቆይታው ጊዜ ሁለት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ነበር።

ናይጄሪያ ለጉብኝት ከአሜሪካ ለሚመጡ መንገደኞች ቪዛ የምትሰጠው ለሦስት ወራት የሚቆይ የአንድ ጊዜ መግቢያ ብቻ ነው።

የናይጄሪያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ እስካሁን የሰጠው አስተያየት የለም።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የቪዛ ፖሊሲዎች "በቀጣይ በሚደረግ ግምገማ ላይ የተመሠረቱ ናቸው" ያለ ሲሆን፣ እንዲሁም እንደ ዲፕሎማሲያዊ፣ የደኅንነት እና የኢሚግሬሽን መመዘኛዎች ሊለወጡ እንደሚችሉ ተናግሯል።

መግለጫው አክሎም የአሜሪካ መንግሥት አገሪቱ ቁልፍ ዓለም አቀፍ መስፈርቶችን እንድታሟላ ከናይጄሪያ ባለሥልጣናት ጋር በቅርበት እየሠራ ነው ብሏል።

ይህም ደኅንነቱ የተጠበቀ የጉዞ ሰነዶችን መስጠት፣ የቪዛ መቆያ ጊዜን ማስተዳደር፣ ለሕዝብ ደኅንነት ሲባል የደኅንነት ወይም የወንጀል መረጃን ማጋራት ይገኙበታል።

አሜሪካ በተጨማሪም ከናይጄሪያ ለቪዛ የሚያመለክቱትን ጨምሮ ሁሉም የውጭ አገር ዜጎች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው "ለዜጎች፣ ለባህል፣ ለመንግሥት፣ለተቋማት ወይም አሜሪካ ለተመሠረተችባቸው መርሆች ያላቸውን ጥላቻ የሚጠቁሙ ምልክቶች" እንዲጣራ አዝዟል።

ናይጄሪያውያን በዓለም ላይ ካሉት ከፍተኛ የተማሪ ቪዛ አመልካቾች መካከል ናቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በ2024 የወጣው ኦፕን ዶርስ ሪፖርት በዓለም አቀፍ የትምህርት ልውውጥ፣ ናይጄሪያ ከዓለም አቀፍ ተማሪዎች ሰባተኛ ደረጃን የያዘች ሲሆን፣ ከአፍሪካ ደግሞ ቀዳሚ ናት።

በዚሁ ዓመት 20,029 ናይጄሪያውያን ትምህርታቸውን በአሜሪካ ለመከታተል ዕድል አግኝተው ነበር።

በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ የትምህርት እና የባህል ጉዳዮች ቢሮ የታተመው ሪፖርት ይህ ቁጥር ከ2023 የ13.5 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ይጠቅሳል።

የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ ረዳት ውሳኔውን ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ለናይጄርያ እርምጃ ምላሽ እየሰጠች ሳይሆን በአገሪቱ ያላትን ቅሬታ እየገለፀች መሆኑን እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ባሽር አህመድ በኤክስ ገጻቸው ላይ በጉዳዩ ላይ ያጋሩት ጽሑፍ በጉዳዩ ላይ ውይይት የቀሰቀሰ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ ለብሪክስ ስብሰባ በቅርቡ ያደረጉት የብራዚል ጉብኝት ለዚህ ምክነያት ነው የሚል ሃሳብ ሰንዝረዋል።

"ይህ ለናይጄርያ እርምጃ የተሰጠ ምላሽ ብቻ አይደለም።ይልቁንም፣ናይጄሪያ ዓለም አቀፋዊ ወዳጆቿ ላይ እያደረገች ያለችው ለውጥ፣ በተለይም ከብሪክስ ያገኙት ሞቅ ያለ አቀባበል አሜሪካን ምቾት እንደነሳት የሚያሳይ ይመስላል" ሲሉ ጽፈዋል።

በግንቦት ወር መጨረሻ ላይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በውጭ አገሮች የሚገኙ ኤምባሲዎቹ የተማሪዎች የቪዛ ቀጠሮ እንዳይሰጡ አዝዞ ነበር።

የአመልካቾችን የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች የማጣራት ሂደት ለማስፋት በዝግጅት ላይ እንዳለ ያስተዋወቀው አስተዳደሩ፤ ለተማሪዎች የቪዛ ቀጠሮ እንዳይሰጥ በጊዜያዊነት አግዶ ቆይቷል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ መልዕክት በሰፈረበት ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በተላከ ማስታወሻ ላይ እገዳው "ተጨማሪ መመሪያ እስኪወጣ ድረስ" ይቆያል ተብሏል።

አስተዳደሩ የተማሪዎች አመልካቾች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾችን የማጣራት ስራ አጠናክሮ የሚሠራ ሲሆን ይህም በኤምባሲዎች እና በቆንስላ ጽ/ቤቶች ላይ ትልቅ አንድምታ እንደሚኖረው ተገልጿል።