አሜሪካ 'ወንጀለኛ' ያለቻቸውን አምስት ስደተኞችን ወደ ደቡብ አፍሪካዊቷ ኢስዋቲኒ አባረረች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ አምስት "ወንጀለኛ ሕገ ወጥ የውጭ አገር ዜጎች" ያለቻቸውን ሰነድ አልባ ስደተኞች ወደ ደቡብ አፍሪካዊቷ አገር ኢስዋቲኒ ማባረሯን ገለፀች።
ወደ ኢስዋቲኒ የተባረሩት የቬትናም፣ ጃማይካ፣ ላኦስ፣ ኩባ እና የመን ዜጎች መሆናቸውን እና ከሕጻናት መድፈር እስከ ግድያ ወንጀሎች የተከሰሱ እንደሆኑ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንነት ቢሮ ረዳት ፀሐፊ ትሪሺያ ማክላውንሊን በማኅበራዊ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።
ማክላውሊን በኤክስ ገጻቸው ላይ "በዚህ በረራ ላይ የተካተቱት በጣም ጨካኝ በመሆናቸው የትውልድ አገሮቻቸው እነሱን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆኑም" ሲል ለምን ወደ አፍሪካዊቷ አገር እንደተባረሩ ጽፈዋል።
አሜሪካ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከሳምንታት መዘግየት በኋላ ከበርካታ አገራት የተውጣጡ ስምንት ስደተኞችን ወደ ደቡብ ሱዳን ልካለች።
ደቡብ ሱዳን በቅድሚያ ስደተኞቹን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረችም።
በዚህ ምክንያት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የደቡብ ሱዳን ፓስፖርት የያዙ ቪዛዎችን በሙሉ ሰርዘዋል። ያ ግን አሁን ተቀይሮ ይሁን ወይም ባለበት ፀንቶ እንደሆነ የታወቀ ነገር የለም።
ባለፈው ሳምንት ናይጄሪያ የቬንዙዌላ ስደተኞችን ወይም የሦስተኛ አገር እስረኞችን ከአሜሪካ እንድትቀበል ከትራምፕ አስተዳደር ለሚደርስባት ጫና እንደማትንበረከክ አሳውቃለች።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምረጡኝ ዘመቻቸው ወቅት ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገራቸው ለማስወጣት ቃል የገቡ ሲሆን፣ ይህም ከፍተኛ ድጋፍ አስገኝቶላቸዋል።
ፕሬዝደንት ትራምፕ በሕገ ወጥ መንገድ በአሜሪካ የሚኖሩ ሰዎችን ማባረር እንደሚፈልጉ የተናገሩ ቢሆንም አሁን ግን ዋይት ሐውስ ይህንን በማስፋት በተማሪ ቪዛ በአገሪቱ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ከአገር ማስወጣት ጀምሯል።
እንዲሁም ከደቡብ አፍሪካ ነጮች በስተቀር ስደተኞችን ላለመቀበል የወሰነ ሲሆን፣ ጊዜያዊ የሥራ ፈቃዶችን እና በቀድሞ ፕሬዝዳንቶች የተሰጡ ከለላዎችን ሰርዟል።
የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን ከአገር ለማባረር በሥራ ቦታዎች ላይ አሰሳ ማድረጉን የቀጠለ ሲሆን፣ ይህም በቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ታግዶ ነበር።
ማክላውሊን በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ተከታታይ ጽሑፎች አምስቱ ስደተኞች የተከሰሱባቸውን ወንጀሎችን ዘርዝረው "የአሜሪካን ማኅበረሰቦች ሲያሸብሩ የነበሩ" ፤"ጨካኝ ጭራቆች" ብለዋቸዋል።
አክለውም "ደኅንነቱ ወደ ተጠበቀ ሦስተኛ አገር የሚደረገው በረራ፣ በደቡባዊ አፍሪካ በምትገኘው ኢስዋቲኒ በሰላም አርፏል።"
በንጉሣዊ ሥርዓት የምትተዳደረው ኢስዋቲኒ ስለ በረራው ምንም የሰጠችው አስተያየት የለም።
ነገር ግን ትንሿ አፍሪካዊት አገር ከአሜሪካ የተባረሩ ስደተኞችን ልትቀበል እንደምትችል በመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ላይ ስሟ ተጠቅሷል።
ቀደም ሲል ስዋዚላንድ እየተባለች ትጠራ የነበረችው ኢስዋቲኒ ከደቡብ አፍሪካ እና ሞዛምቢክ ጋር የምትዋሰን ስትሆን ወደብ አልባ ናት።
እአአ ከ1986 ጀምሮ በንጉሥ ምስዋቲ ሳልሳዊ እየተመራች ትገኛለች።
ባለፈው ወር የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የትራምፕ አስተዳደር ስደተኞችን ከመጡበት አገር ውጪ ወደ ሦስተኛ አገር ማባረሩን እንዲቀጥል ፈቅዷል።
ሩዋንዳ በዚህ ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር መወያየቷን ያረጋገጠች ሲሆን ቤኒን፣ አንጎላ፣ ኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሞልዶቫ በመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ከአሜሪካ የሚባረሩ የሌላ አገር ስደተኞችን ተቀባይ አገራት በሚል ስማቸው ተጠቅሷል።
የትራምፕ አስተዳደር ቀደም ሲል ሰነድ አልባ ስደተኞችን ወደ ኤል ሳልቫዶር እና ኮስታሪካ አባርሯል።















