15 ኤርትራውያን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት በማቀዝቀዣ መኪና ውስጥ ተደብቀው ተገኙ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በርካታ ኤርትራውያን አትክልቶችን በሚያጓጉዝ የማቀዝቀዣ ከባድ ተሽከርካሪ ውስጥ በአደገኛ ሁኔታ ተደብቀው ሲጓዙ መገኘታቸው ተገለጸ።
አንድ ሕጻንን ጨምሮ ብዛታቸው 15 መሆኑ የተነገረው ኤርትራውያኑ ከፈረንሳይ ተነስተው በማቀዝቀዣ መኪናው ውስጥ ተደብቀው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ሊያመሩ እንደነበረ የፈረንሳይ የዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) ዘግቧል።
ኤርትራውያኑ ስደተኞች በከባድ መኪናው የማቀዝቀዣ ክፍል ውስጥ የተገኙት ቅዳሜ ዕለት ሲሆን፣ በኃይለኛ ቅዝቃዜ ምክንያት የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማታቸውን የመኪናው አሽከርካሪ ገልጿል።
የፈረንሳይ ሕክምና ባለሙያዎች ሕገ ወጥ ስደተኞቹ በከባድ ቅዝቃዜ በመጎዳታቸው የሕክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ማድረጋቸውን የዜና ወኪሉ ዘግቧል።
ወደ ዩናይትድ ኪንግደም አትክልቶችን ጭኖ እያመራ የነበረው መኪና በሰሜን ፈረንሳይ ለእረፍት ሲቆም አሽከርካሪው የለቅሶ እና የድረሱልኝ ጩኽት መስማቱን ለአካባቢው ባለሥልጣናት አመልክቷል።
የአካባቢው አስተዳደር ሠራተኛ የሆነው ክርስቲያን ቬዴላጎ ኤርትራውያኑ ስደተኞች በተሽከርካሪው ውስጥ "የነበሩበት የቅዝቃዜ ደረጃ በመኪናው ውስጥ ለበርካታ ሰዓታት መቆየታቸውን ያሳያል" ብሏል።
አሽከርካሪው ስለሁኔታው ከአካባቢው ባለሥልጣናት ካሳወቀ በኋላ ፖሊስ እና የሕክምና ባለሙያዎች ደርሰው ስደተኞቹን ከቀዝቃዛው የመኪና ክፍል እንዲወጡ አድርገዋል።
ከመካከላቸውም በቅዝቃዜው የተጎዱ አራት ስደተኞች ወደ ሆስፒታል ተወስደው ሕክምና እየተደረገላቸው ሲሆን፣ አራቱ ከ18 ዓመት በመሆናቸው እንክብካቤ ለሚያደርግ ድርጅት ተላልፈው መሰጠታቸውን ተገልጿል።
ከ15 ሰዎች መካከል አንዷ ሴት መሆኗን የአካባቢው ባለሥልጣን ጨምሮ ገልጿል።
የፈረንሳይ ፖሊስ የታደጋቸው አብዛኞቹ ስደተኞች በሕገወጥነት ተፈርጀው ከአገሪቱ ለቅቀው እንዲወጡ ታዘው የተነሩ መሆናቸው ታውቋል።
ኤርትራውያኑ ተደብቀውበት የነበረው የቀዘቀዙ አትክልቶችን ያጓጉዝ የነበረው የጭነት ተሽከርካሪ ሹፌር ላይ በፖሊስ ምንም ዓይነት ምርመራ እንዳልተደረገለት የኤኤፍፒ ዘገባ ያሳረዳል።
በሰሜን ፈረንሳይ ወደ ብሪታኒያ በሚሄዱ መርከቦች እንዲሁም ሁለቱን አገራት በሚያገናኘው በእንግሊዝ ቻናል ላይ ጥብቅ ፍተሻ ቢደረግም ስደተኞች አሁንም ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በሚሄዱ መኪኖች ላይ ተደብቀው መሳፈራቸው አልቀረም።
ከፈረንሳይ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በሚደረጉ ጉዞዎች አሁንም ተመራጩ መንገድ በአነስተኛ ጀልባዎች ማቋረጥ ነው።
ባለፉት ሰባት ወራት በኢንግሊሽ ቻናል አነስተኛ ጀልባን በመጠቀም 25,436 ስደተኞች ወደ ዩኬ አቋርጠዋል።
በአዲሱ የዩኬ መንግሥት አሰራር መሰረት በአነስተኛ ጀልባ ዩኬ የሚገቡ ስደተኞች ተይዘው ወደ ፈረንሳይ እንዲመለሱ ይደረጋል።
በእያንዳንዱ በሚመለስ ስደተኛ ምትክ ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ወደ ዩኬ በጀልባ ለማቋረጥ ያልሞከረ ጥገኝነት ጠያቂ የደህንነት እና የተገቢነት መስፈርቶችን ካለፈ ይቀበላል።
ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት አይኦኤም እአአ በ2024 82 ስደተኞች በአነስተኛ ጀልባ ወደ ለማቋረጥ ሲሞክሩ መሞታቸውን ገልጿል።
በ2025 ሰኔ ወር መጨረሻ ደግሞ 18 ሰዎች ሞተዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር እስከ መጋቢት 2025 ድረስ በአነስተኛ ጀልባ ሆነው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ለመግባት ከሞከሩ ዜጎች መካከል ቀዳሚዎቹ አፍጋኒስታናውያን ሲሆኑ (5,766)፣ ከሶሪያውያንን በመቀጠል (4,368)፣ ኤርትራውየን በ4,229 በሦስተኛነት ተቀምጠዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም በትናንሽ ጀልባዎች የሚገቡ ስደተኞችን ለማስቀረት በሚል ጥረት ከሌሎች አገራት ጋር የተለያዩ ስምምነቶች ላይ ደርሳለች።















