ዩኬ "ህገወጥ ስደትን ለመግታት" 40 አገራት የሚሳተፉበት ጉባኤ ልታካሂድ ነው

ስደተኞች በዩኬ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ዩናይትድ ኪንግደም አለም አቀፍ ስጋት ያለችውን "ህገወጥ ስደትን" ለመግታት 40 አገራት የሚሳተፉበት የሁለት ቀናት ጉባኤ ልታካሂድ ነው።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የሚያሰናዱት ይህ ጉባኤ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር "አስከፊ ንግድ" የሚፈጽሙ ወሮበሎችን ለማስቆም እንዲሁም አገራት ስደትን አስመልክቶ "እርስ በርስ የሚናቆሩበትን" ሁኔታን ለመቅረፍ ያለመ ነው ተብሏል።

በያዝነው ሰኞ የሚጀመረው እና በዓይነቱ ልዩ ነው የተባለው ይህ ጉባኤ "ተጨባጭ ውጤቶችን" ለማምጣት እንዲሁም አለም አቀፍ ትብብርን ለማሳደግ ያለመ ነው።

ስደት በዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲካ ውስጥ ቁልፍ የመንግሥት አጀንዳ ተደርጎ የሚታይ ሲሆን ፤ ተቃዋሚዎቹ ወግ አጥባቂ ሆነ ሪፎርም ዩኬ ፓርቲዎች ገዢው ሌበር ፓርቲ ጉዳዩን በቁጥጥር ስር ሊያውል አልቻለም ሲሉ ይከሱታል።

ከጉባኤው ቀደም ብሎ የሃገር ውስጥ ጽህፈት ቤት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መረቦችን ለመበጣጠስ እንዲሁም ክሶችን ለመጨመር 33 ሚሊዮን ፓውንድ በጀት ተይዟል ብሏል።

በርካታ ስደተኞች ወደ ዩኬ የተጓዙባቸው እንደ ቬትናም፣ አልባኒያ እና የኢራቅ ባለስልጣናትን ጨምሮ የፈረንሳይ፣ ቻይና እና አሜሪካ ተወካዮች በለንደን ላንካስተር ሃውስ በሚካሄደው ጉባኤ ተሳታፊ ናቸው።

በተጨማሪም የኩርዲሽ ክልላዊ መንግሥት ተወካዮች፣ ኢንተርፖል እና የማህበራዊ ሚዲያዎቹ ሜታ፣ ኤክስ፣ እና ቲክ ቶክ ተወካዮች ይገኛሉ።

ተወካዮቹ በዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር ይዘዋወርበታል ተብሎ የሚገመተው ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ንግድን እንዴት መቆጣጠር ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ይመክራሉ።

ከጥር ወር ጀምሮ ከ6 ሺህ በላይ የሚሆኑ ስደተኞች በአነስተኛ ጀልባዎች ተጭነው ወደ ዩናይትድ ኪንግደም ገብተዋል።

ይህ ቁጥር እስካሁን ከተመዘገቡት በክብረ ወሰንነት የተያዘ አኃዝ ነው ተብሏል።

ዩናይትድ ኪንግደም በትናንሽ ጀልባዎች የሚገቡ ስደተኞችን ለማስቀረት በሚል ጥረት ከሌሎች አገራት ጋር የተለያዩ ስምምነቶች ላይ ደርሳለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር መደበኛ ባልሆኑ የስደት ጉዞዎች ላይ የሚደረጉ ምላሾችን አገራቸው በአለም አቀፍ ደረጃ እንድትመራ ይፈልጋሉ።

የዩኬ መንግሥት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር መቆም የሚችለው በአለም አቀፍ ትብብር ብቻ መሆኑን በዚህ ጉባኤ ላይ ማሳመን ይፈልጋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪም ይህ ጉባኤ የዩናይትድ ኪንግደም ድንበሮች እንዲጠናከሩ፤ ሸክሙን ከአገሪቱ ህዝባዊ ተቋማት ላይ የሚያወርድ እና የስደተኞች መቆያ ሆቴሎችን በመመለስ የአካባቢዎች ኢኮኖሚ እንዲጠናከር መልሶ መስጠት የሚያስችል ነው የሚል ሃሳብ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

ጉባኤው በአውሮፓ፣ በእስያ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአፍሪካ እና በሰሜን አሜሪካ ላሉ አገራት "ተጨባጭ ውጤቶችን" እንደሚያስገኝ የሃገር ውስጥ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።