ትራምፕ በዩክሬን ተኩስ አቁም ጉዳይ በፕሬዝደንት ፑቲን 'እጅግ መበሳጨታቸውን' ተናገሩ

ፑቲን እና ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ለሳምንታት በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ሲሞክሩ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን "እጅግ ተበሳጭቻለሁ" አሉ።

ኤንቢሲ ከተባለው ጣቢያ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአሜሪካው ፕሬዝደንት፤ ፑቲን የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተዓማኒነት ላይ ጥቃት በመሰንዝራቸው መናደዳቸውን ተናግረዋል።

ትራምፕ፤ ፑቲን የተኩስ አቁም ስምምነት ካልፈረሙ ከሩሲያ ነዳጅ የሚገዙ ሀገራት ላይ የ50 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ዝተዋል።

"በዩክሬን ያለውን ደም መፋሰስ ለማስቆም እኔ እና ሩሲያ ከስምምነት የማንደርስ ከሆነ እና የሩሲያ ጥፋት ነው ብዬ ካሰብኩ - ላይሆንም ይችላል - ከሩሲያ የሚወጣ ነዳጅ ላይ ታሪፍ እጥላለሁ" ብለዋል።

ትራምፕ የሰጡት አስተያየት በሩሲያ ጉዳይ ያላቸው አቋም መለወጡን የሚያሳይ ነው ተብሏል።

ዋይት ሐውስ ፕሬዝደንቱ ባሰሙት ንግግር ዙሪያ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

አውሮፓውያን መሪዎች ትራምፕ በዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ጉዳይ የፕሬዝደንት ፑቲንን አቋም እያንፀባረቁ ነው የሚል ትችት ያሰማሉ።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ትራምፕ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪን ወደ ኦቫል ኦፊስ ጠርተዋቸው በቀጥታ በተላለፈ ስርጭት እሰጥ አገባ ውስጥ ገብተው እንደነበር ይታወሳል። በሌላ በኩል ደግሞ የሩሲያውን ፕሬዝደንት ስም ሲያወድሱ ተሰምተዋል።

አሜሪካ በዩክሬን ተኩስ አቁም ጉዳይ ሩሲያን ስትወቅስ እና ዛቻ ስታሰማ ይህ የመጀመሪያው ሲሆን ከሩሲያ የሚመጣው ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ይጠበቃል።

ምንም እንኳ ትራምፕ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪን አምባገነን መሪ ናቸው፤ ምርጫ ሊያካሂዱ ይገባል ብለው ወቅሰው ቢያውቁም ከኤንቢሲ ጋር በነበራቸው የስልክ ቃለ ምልልስ ፑቲን የዜሌንስኪን ተዓማኒነት በመውቀሳቸው "መናደዳቸውን" ተናግረዋል።

ትራምፕ ስለ ፑቲን ሲያወሩ መበሳጨታቸውን ክሬምሊን እንደሚያውቅ ጠቁመው ነገር ግን ከሩሲያው መሪ ጋር "በጣም መልካም ግንኙነት" እንዳላቸው ተናግረዋል። አክለው "እሱ ትክክለኛውን ነገር ካደረገ ብስጭቱም ብን ብሎ ይጠፋል" ብለዋል።

ፑቲን በዚህ የማይስማሙ ከሆነ ግን ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀብ እንደሚጥሉ ዝተዋል። ከሩሲያ ነዳጅ የሚገዙ ሀገራት ላይ 50 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉም አሳውቀዋል። ከሩሲያ ብዛት ያለው ነዳጅ የሚገዙ ሀገራት ቻይና እና ህንድ ናቸው።

ዜሌንስኪ በማኅበራዊ ሚድያ ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት "ሩሲያ ምክንያት እየፈለገች ይህ ጦርነት እንዲራዘም ነው የምትፈልገው" ብለዋል።

ትራምፕ በያዝነው ሳምንት መገባደጃ ከፑቲን ጋር እንደሚያወሩ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ከቴሌቪዥን ጣቢያው ጋር ባደረጉት ቆይታ ምንም እንኳን ሕገ-መንግሥቱ ባይፈቅድላቸውም ለሶስተኛ ጊዜ ለፕሬዝደንትነት የመወዳደር ዕቅድ እንዳላቸው ጠቁመዋል።

"በጣም ብዙ ሰዎች እንዳደርገው ይፈልጋሉ። ያው እንግዲህ ገና ብዙ ርቀት መጓዝ ይጠበቅብናል" ብለዋል።

በሌላ በኩል ኢራን የኒውክሌር ስምምነት ካልተፈራረመች ቦምብ እንደሚጥሉባት ዝተዋል። ትራምፕ ለኢራን አገዛዝ በላኩት ደብዳቤ ድርድር ያስፈልጋል ሲሉ መጠየቃቸው ይታወሳል።

የኢራኑ ፕሬዝደንት ማሱድ ፔዜሽኪያን እሑድ በሰጡት አስተያየት ከዋሺንግተን ጋር ቀጥተኛ ድርድር ውስጥ ባይገቡም በሶስተኛ ወገን ውይይት ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል።