ዝምድና ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸም ጋብቻ የጤና ችግርን ያስከትላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) ብራድፎርድ ውስጥ ነው።
ሦስት እህትማማቾች ሰገነት ላይ እየተጨዋቱ ነው። ቤቱ በሳቅ እና በጨዋታ ተሞልቷል።
በ20ዎቹ ዕድሜ የሚገኙት ሦስቱ ሴቶች ስለ ባል እና ትዳር ያወራሉ።
እህትማማቾቹ በሳምንቱ መጨረሻ ለሚደገስ የቤተሰብ ሰርግ እየተዘጋጁ ነው - ሙሽሪት እና ሙሽራው የአክስት ልጆች የሆኑበት ሰርግ።
ለብዙ ሰዎች ይህ አስደንጋጭ ሊመስል ይችላል።
በዩኬ፣ ብራድፎርድ እና አካባቢው ግን በጣም የተመለደ ነው።
ከሦስቱ እህትማማቾች ትልቋ አይሻ 29 ዓመቷ ነው። በአውሮፓውያኑ 2017 ነበር የአጎቷን ልጅ ያገባችው። ሁለት ልጆች ወልደዋል። በትዳሯ ደስተኛ እንደሆነች ትናገራለች።
የአጎቷን ልጅ ማግባት በወቅቱ ችግር ሆኖ አልተሰማትም ነበር። ብዙዎቹ የፓኪስታን ስደተኞች እናቶቻቸው ለልጆቻቸው እንዲያ እንዲያደርጉ ይሻሉ።
ከሦስቱ ታናሽ የሆነችው የ26 ዓመቷ ሳሊና ግን "የምወደውን ነው የማገባው" ትላለች።
ከቤተሰብ ውጪ ትዳር መመሥረትን ታስባለች። ይህ ነገር ቤተሰቡን አሳስቦታል።
ማሊካ ደግሞ አለች። ሦስተኛዋ እህታቸው።
ከወዲሁ ''እኔ ብሞት ዘመዴን አላገባም'' የሚል አቋም ይዛለች።
ማሊካ "በእህቶቼ ላይ አልፈርምድ፤ እኔ ግን አላደርገውም" ትላለች።ምንድን ነው ችግሩ?
ምን ያህል አሳሳቢ ነው?
በዩኬ እና በመላው አውሮፓ ከአጎት/ከአክስት ልጅ ጋር የሚፈጸም ጋብቻ ላይ ክርክሮች አሉ።
አንዳንድ አገሮች በሕግ ከልክለዋል። አንዳንዶቹ ገና ጥናት ላይ ናቸው።
ሐኪሞች በቅርብ ቤተሰብ መካከል የሚፈጸም ጋብቻ ብዙ የጤና ችግሮችን ያስከትላል ይላሉ።
ይህን በተጨባጭ ለመረዳት አንድ ትልቅ ጥናት እና ምርምር በብራድፎርድ እየተደረገ ነው።
ጥናቱ 18 ዓመት ሆኖታል።
ተመራማሪዎች በከተማው ውስጥ ከ13,000 በላይ ሕፃናትን በመመልመል ከልጅነታቸው ጀምሮ እስከ ጉርምስና ዕድሜ ድረስ በቅርብ እየተከታተሏቸው ነው።
በጥናቱ ውስጥ የተካተቱት ልጆች የአጎት/የአክስት ልጅ ካገቡ ጥንዶች የተወለዱ ናቸው።
የቅርብ ቤተሰብን ማግባት የጤና ተጽእኖ እንደሚኖረው ለማረጋገጥ እጅግ ጠቃሚ ከሚባሉ ጥናቶች አንዱ ነው።
ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ በታተመ አንድ ጥናት መሠረት ተመራማሪዎቹ የመጀመሪያ የአጎት/አክስት አግብቶ መውለድ ቀደም ሲል ከታሰበው በላይ ሰፊ መዘዝ ሊኖረው እንደሚችል ደርሰውበታል ።
ከደም ጋር የተገናኙ ጥንድ ወላጆች በልጁ ላይ የጤና ስጋትን የሚጨምሩበት ዋናው ምክንያት የዘረ-መል ድግግሞሽ ስለሚከሰት ነው።
ይህ ደግሞ የሚወለዱ ልጆች በሽታ እንዲወርሱ ያደርጋቸዋል።
በዚህም የተነሳ ዝምድና ካላቸው ወላጆች የተወለዱ ልጆቹ መካከል የቋንቋ እና የንግግር ችግር 11 በመቶ ሲሆን፣ ዝምድና በሌላቸው መካከል ደግሞ 7 በመቶ ሆኗል።
ዝምድና ካላቸው ወላጆች የተወለዱ ልጆች "ጤናማ የዕድገት ደረጃ" ላይ ለመድረስ 54 በመቶ ዕድል ብቻ ሲኖራቸው፤ ዝምድና ከሌላቸው ወላጆች የተወለዱ ልጆች ግን መጠኑ 64 በመቶ ነው።
ምን ያህል ልጆች በድግግሞሽ እየታመሙ ሐኪም ጎበኙ የሚለውም ስለ ጤንነታቸው የበለጠ ግንዛቤ የሰጠ ሆኗል።
የአክስት/የአጎት ልጅ አግብተው የወለዱ ልጆቻቸው በአማካይ በዓመት አራት ጊዜ ሐኪም ለማየት ተገደዋል።

የቻርለስ ዳርዊን ነገር
ይህ የአጎት/የአክስት ልጅ የማግባቱ ባሕል በመላው አውሮፓ የሕግ አውጪዎችን ቀልብ የሳበ ሆኗል።
ውሳኔ ላይ ለመድረስ ግን የማያዳግም ሳይንሳዊ መረጃን ይፈልጋሉ።
ሁለት የስካንዲኔቪያ አገራት ኖርዌይ እና ስዊድን የአክስት/የአጎት ልጅ ጋብቻን ሙሉ በሙሉ ሕገ ወጥ አድርገው ፈርጀውታል።
ኖርዌይ ውስጥ ባለፈው ዓመት ሕገ ወጥ ተግባር ተብሎ ታውጇል። በስዊድን ደግሞ ዕገዳው ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል።
በዩኬ ውስጥም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
የወግ አጥባቂው የፓርላማ አባል ሪቻርድ ሆልደን ድርጊቱን ለማስቀረት ትግል ጀምረዋል።
የሌበር ፓርቲ ግን እገዳ ለመጣል ለጊዜው ምንም ዕቅድ የለም ብሏል።
ለጊዜው ዩናይትድ ኪንግደም የቅርብ ዘመድ ጋብቻ ስለሚያስከትላቸው ጉዳቶች ለመረዳት በእርግዝና ወቅት ተጨማሪ ምርመራ እንዲያደርጉ ዜጎችን የሚበረታታበትን የ"ጄኔቲክ ምክር" ፖሊሲን እየተከተለች ነው።
በእርግጥ ለብሪታኒያውያን የአጎት እና የአክስት ልጅ ማገባት በዚህ ዘመን እንግዳ ነገር ነው።
በቀድሞ ጊዜ ግን የመሳፍንት ቤተሰቦች ዘንድ በተለይ ይዘወተር ነበር።
'የዝግመተ ለውጥ አባት' ተብሎ የሚጠራው የሥነ ፍጥረት ተመራማሪው ቻርለስ ዳርዊን የአጎቱን ልጅ ኤማ ዌድዉድን ነው ያገባው።
ቻርለስ ዳርዊን ከቅርብ ዘመዱ ኢማ ዌድዉድ 10 ልጆችን ወልዷል። ሆኖም 7ቱ ብቻ ናቸው 10ኛ ዓመት ልደታቸውን ማክበር የቻሉት።
አንዱ ልጃቸው ጆርጅ ዳርዊን ሳይንቲስት ነበር። እርሱ እንደጻፈው በ19ኛው ክፍለ ዘመን ከኖሩ መሳፍንት ከ20 ጋብቻዎች ቢያንስ የአንዱ ከቅርብ ዘመድ ጋር የሚደረግ ነበር።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን ግን በዩናይትድ ኪንግደም የአክስት እና የአጎት ልጅ ማገባት ወደ 1 በመቶ ቀንሷል። ሆኖም በአንዳንድ የእስያ ማኅበረሰቦች ዘንድ አሁንም ቀጥሏል።
ከቅርብ ዓመታት በፊት የፓኪስታን ማኅበረሰብ ግማሽ ያህሉ (46 በመቶ) እናቶች የአጎት ወይም የአክስት ልጅ ያገቡ ነበር።
የሩቅ ዘመድ ማግባትስ?
ፕሮፌሰር ኦዲ በብራድፎርድ የዘረመል ጤና ዋነኛው አደጋ የአጎት/የአክስት ልጅ ጋብቻ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ወይም የሩቅ ዘመድ ማግባትም ነው ይላሉ።
በሩቅ ዘመድ ነካከልም ቢሆን በአንድ ትንሽ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚደረግ የጋብቻ ትስስር አደጋ አለው።
የቅርብ ማኅበረሰብ አባላትን የሚያገቡበት በእንግሊዝኛው 'ኢንዶጋሚ' በመባል የሚታወቅ ጉዳይ ነው።
በጠባቡ የተሳሰረ ጥብቅ ማኅበረሰብ ውስጥ ሰዎች የጋራ ቅድመ-አያት እና ዘረመል የመጋራት ዕድላቸው ሰፊ ነው።
ይህ የዘመዳሞች ጋብቻ በፓኪስታኒዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን በአይሁዶች፣ በአሚሾች እና በፈረንሳይ ካናዳውያን ዘንድም ይዘወተራል።
ፕሮፌሰር ኦዲ እንደሚሉት "ተመሳሳይ ጂን በተወሰነ ቡድን ውስጥ በብዛት ይከሰታል፤ በዚህ ምክንያት ሁለቱም ወላጆች የተጎዳውን ጂን ይይዛሉ፤ ይወርሳሉ" ይላሉ።
ይህ ደግሞ ለጤና ችግር ያጋልጣቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሕግ መከልከል ያዋጣል?
ጥናቱ ቀጥሏል። የአክስት/አጎት ልጅ ጋብቻ ለጤና ጠንቅ እንደሆነ ብዙ አስረጂዎች እየወጡ ነው።
ነገር ግን በሕግ መከልከል ያዋጣል?
በፓኪስታን ማኅበረሰብ ውስጥ ላሉ ሰዎች ይህ ዓይነቱ ጋብቻ የዘረመል አደጋ እንዳለው ለማሳወቅ በብራድፎርድ ውስጥ ለብዙ ዓመታት ዘመቻ ሲደረግ ቆይቷል። ሐኪሞች ልዩ ምክር ይሰጣሉ።
ለአዲስ ተጋቢዎች አደጋውን ያስረዳሉ። ብዙዎች መልዕክቱ እየገባቸው ነው።
በዚህ ጽሑፍ መነሻ የተጠቀሱት ሦስቱ ሴቶች በቅርብ ዘመድ ጋብቻ ዙሪያ አስተሳሰቦች እየተለወጡ እንደመጡ ምስክር ናቸው።
ይህም የሆነበት ምክንያት በጤና ጠንቅ ዙሪያ ግንዛቤ መጨመሩ ነው።
የትዳር አጋሬን ከቅርብ ዘመዶቼ ሳይሆን በፍቅር ከምወድቅለት ሰው ጋር ነው የምመሠርተው የምትለው ሳሊና የአስተሳሰብ ለውጡ ቀስ በቀስ የሚመጣ ነው ትላለች።
"እናቴ ከፓኪስታን ወደ ዩናይትድ ኪንግደም በመጣችበት ወቅት የነበረው ቤተ ዘመድ ትንሽ ነበር። በዚህ የተነሳ አንዳንድ አመለካከቶች ነበሯት። ነገር ግን እነኛ ቀስ በቀስ ተለውጠዋል'' ትላለች።
''እናቴ ከነበሯት ጠንካራ አመለካከቶች አንዱ ልጆቿን ለቅርብ ዘመድ መዳር ነበር። አሁን ግን 'እማዬ! የአጎቴን ልጅ እንዳገባ መገፋፋት ምን ይጠቅማል?' ስላት፣ 'ልክ ነሽ' ትለኛለች።''
ታላቅ እህቷ ማሊካ በዚህ ትስማማለች። ሁኔታዎች መለወጥ የቻሉት በማኅበራዊ ሚዲያ መስፋፋት እና የማኅበረሰብ ለመረጃ በመጋለጥ ምክንያት ነው ትላለች።
በዚህ ዘመን "አዲስ ግንኙነት አለህ . . . ከወላጆቻችን ዓይን ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር በቀላሉ መገናኘት እንችላለን።''
በአጎት ልጅ ትዳር ውስጥ ያለችው ታላቅ እህት አይሻ እንኳን ከሁለቱ ልጆቿ መካከል "አንዳቸውም የአጎታቸውን ልጆች ያገባሉ ብዬ አላስብም" ትላለች።
እሷ የአጎቷን ልጅ ባገባችበት ወቅት፣ "ከዚያ የተለየ አላውቅም ነበር፣ ወላጆቼ በባህላቸው ጠንካራ ነበሩ" ስትል አሁን ግን ነገሮች እየተለወጡ እንደሆነ ታብራራለች።
በእርግጥ በብራድፎርድ አሁን አሁን ይህ ባሕል እያሽቆለቆለ ነው።
የቦርን ኢን ብራድፎርድ ፕሮጀክት ዋና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጆን ራይት እንዳሉት ይህ እየሆነ ያለው በአጋጣሚ አይደለም።
ቡድኑ በዩናይትድ ኪንግደም የአጎት/የአክስት ልጅ ጋብቻ አደጋ ዙሪያ ማስረጃዎችን ያሳተመው በቅርብ ጊዜ እንደሆነ ጠቁሟል።
"ከ10 ዓመት በፊት ከማኅበረሰቡ ጋር ስንነጋገር ሰዎች ስለጉዳቱ እንደማያውቁ በጣም በግልፅ ነበር የሚነግሩን። ነገር ግን አሁን ሁሉም ወላጆች ለልጆቻቸው የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ ይፈልጋሉ። ጤናማ ልጆች መውለድ ይፈልጋሉ" ይላሉ።
ለዚህ ደግሞ ትምህርት ቁልፍ ጉዳይ ነው።
የምዕራብ ባሕል ወረራ?
ከጤና ስጋት በተጨማሪ አንዳንድ ሰዎች የአጎት/የአክስት ልጅ ጋብቻ ተከልክለው ማየት የሚፈልጉበት ሌላ ምክንያት አለ፤ በማኅበራዊ ትስስር ላይ ያለው ተጽእኖ።
በስካንዲኔቪያ ያለውን ክርክር በዋናነት ያነሳው ይህ ነው።
ባለፈው ዓመት የአጎት/የአክስት ልጅ ጋብቻ በተከለከለበት ኖርዌይ ድርጊቱ ከግዳጅ ጋብቻ ጋር የተያያዘ መሆኑን ሕግ አውጪዎች ገልጸው፤ አንዳንድ የደቡብ እስያ ስደተኛ ሴቶች ከዘመዶቻቸው ጋር እንዲጋቡ መገደዳቸውን ያነሱ ነበር።
አንዳንድ ቤተሰቦች በባሕል ከሌላው ማኅበረሰብ ጋር ላለመተሳሰር ሲሉ የቅርብ ዘመድ ጋብቻን ያበረታታሉ።
ይህ የሚሆነው ባሕላችን ይጠፋል፤ እንዋጣለን ከሚል ፍርሃት ነው።
የኖርዌይ ከፍተኛ የፖሊስ መኮንን ጃስሚና ሆልተን ባለፈው ዓመት ከኖርዌይ ብሮድካስቲንግ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ አንዳንድ የአጎት/አክስት ልጅ ጋብቻ እንዲፈጽሙ የተገደዱ ሴቶች ራሳቸውን ድንገት አደገኛ ወጥመድ ውስጥ እንዳገኙ እና ነጻነታቸውን እንደተቀሙ ገልጸዋል።
በዘመዶቻቸው የገንዘብ እና የሥነ ልቡና ጥገኝነት ስር ስለሚወድቁ ፍቺ እንኳ መፈጸም የማይችሉበት ደረጃ ላይ ይደርሳሉ።
የአጎት/አክስት ልጅ ጋብቻን መከልከል ያንን አስነዋሪ ሰንሰለት ሊሰብር ይችላል ባይ ናቸው።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ በጋብቻ የተጠረነፉ ሴቶች ፍቺ ጠየቁ ማለት ከዚያ ማኅበረሰብ ፈጽሞ መገለልን ያስከትልባቸዋል።
በተመሳሳይ የስዊድን የፍትህ ጉዳዮች ፀሐፊ ጉናር ስትሮመር አገራቸው የአጎት/አክስት ልጅ ጋብቻን መከልከሏ ሴቶችን ከ"ጨቋኝ" ሥርዓት ነፃ እንደሚያወጣ ተናግረዋል።
ይህ የጦፈ የባሕል ክርክርን ያስከተለ ጉዳይ ነው።
አንዳንዶች ውሳኔውን የሌላውን ባሕል መናቅ አድርገው ይመለከቱታል። የባሕል ብዝኃነትን እና የግል ምርጫን አለማክበር አድርገውም ያዩታል።
በስካንዲኒቪያን አገራት ዕገዳው ቢቀጥልም አንዳንድ ጥንዶች በሕገወጥ እና ባልተመዘገቡ ማኅበራት በኩል የአጎት/አክስት ልጆችን ማግባታቸውን ሊቀጥሉ ይቻላሉ የሚል ፍርሃት አለ።
ምናልባት 18 ዓመታት የፈጀው የብራድፎርድ ምርምር እና ጥናት ውጤት ይፋ ሲሆን ስለ ቅርብ ዘመድ ጋብቻ አዲስ መረጃን ይፈነጥቅ ይሆናል። እስከዚያው ግን ክርክሩ እንደቀጠለ አለ።












