ሶማሊያ ለአሜሪካ ቁልፍ ወደብ ለመስጠት ያቀረበችውን ሃሳብ ሶማሊላንድ ውድቅ አደረገች

ራሷን በነጻ አገርነት ያወጀችው ሶማሊላንድ፣ የሶማሊያ መንግሥት በበርበራ የሚገኘውን ወደብ እና ወታደራዊ አየር ማረፊያ አሜሪካ በብቸኝነት እንድትቆጣጠር ያቀረበውን ሃሳብ ውድቅ አደረገች።
በርበራ በሶማሌላንድ ሰሜናዊ የባህር ዳርቻ በሚገኘው የኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ ትገኛለች።
እአአ በ1991 ሶማሊያ ወደ እርስ በርስ ጦርነት ስትገባ ነፃነቷን ያወጀው ሶማሊላንድ፣ ተቋሞቿ ሞቃዲሾ በችሮታ የምትሰጣቸው አለመሆናቸውን ገልጻለች።
በሶማሊያው ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለአሜሪካ አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ መጋቢት 7 2017 ዓ.ም. የተጻፈው እና ሮይተርስ የተመለከተው ደብዳቤ፣ አሜሪካ በብቸኝት ልትቆጣጠራቸው የሚችሉ የጦር ሰፈሮች እና የወደብ አማራጮችን ዘርዝሯል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ፕሬዚዳንቱ አሜሪካ በብቸኝነት እንድትቆጣጠራቸው ያቀረቡላቸው ባሊዶግሉ እና በርበራን በጦር ሰፈርነት እንዲሁም የበርበራ እና ቦሳሶ ወደቦችን ነው።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በዚሁ ደብዳቤ ላይ አራቱም የቀረቡት አማራጮች የአሜሪካ የደህንነት ስራዎችን ያጠናክራሉ ሲሉ መግለጻቸው ተዘግቧል።
የሶማሌላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲራህማን ዳሂር አዳን "ተስፋ የቆረጠ" አካል እርምጃ ነው ሲሉ ደብዳቤውን አጣጥለውታል።
ትራምፕ ሁለተኛውን የስልጣን ዘመናቸውን ከመጀመራቸው በፊት በነበሩ ጭምጭምታዎች ሶማሌላንዳውያን አሜሪካ ለ34 ዓመታት ያህል በዲሞክራሲያዊ መንግሥትነት ለቆየችው ሶማሌላንድ እውቅና በመስጠት በዓለም የመጀመሪያዋ አገር ትሆናለች የሚል ተስፋ ሰንቀው ነበር።
ሚስተር አዳን ለደብዳቤው በኤክስ ገጻቸው ላይ በሰጡት ምላሽ "ለሶማሊላንድ የሚሰጠውን እውቅና ለማስቆም ማድረግ የሚችሉት ምንም ነገር የለም" ብለዋል ።
የአሜሪካ የቅርብ አጋር የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ንብረት በሆነው ዲፒ ወርልድ የሚመራው የበርበራ ወደብ በቅርቡ ማስፋፊያ ተደርጎለታል።
ሚኒስትሩ ለሮይተርስ እንደተናገሩት "አሜሪካ ሞኝ አይደለችም፤ በርበራ ወደብን በሚመለከት ከማን ጋር መነጋገር እንዳለባት ታውቃለች" ብለዋል።
ሶማሊያ ከአልቃይዳ እና ሌሎች ታጣቂዎች ጋር በምታደርገው ውግያ አሜሪካ መረጃ በመስጠት እና የአየር ድብደባ በመፈጸም ትልቅ ሚና ትጫውታለች።
በደቡባዊ እና መካከለኛው ሶማሊያ የሚገኙ አካባቢዎችን የሚቆጣጠረው አልሸባብ፣ የአልቃይዳ አጋር ነው ተብሎ ይታሰባል።
ሞቃዲሾ ትራምፕ በመጀመሪያው የስልጣን ዘመናቸው እንዳደረጉት የሚሰጡትን ድጋፍ ይቀንሳሉ ብለው እንደሚሰጉ ታዛቢዎች ይናገራሉ።
በታሕሳስ ወር የሶማሊያ መንግሥት በአሜሪካ እና ሶማሊያ ግንኙነት ላይ ተገቢውን የምክር ድጋፍ ለማግኘት በሚል ከአንድ ከፍተኛ የዋሽንግተን አማካሪ ድርጅት ጋር ለአንድ ዓመት የ600 ሺህ ዶላር ስምምነት ተፈራርሟል።
የሶማሊያው ፕሬዚደንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ አሜሪካ በብቸኝነት እንድትቆጣጠራቸው ያቀረቧቸው ባሊዶግሉ እና በርበራን በጦር ሰፈርነት እንዲሁም የበርበራ እና ቦሳሶ ወደቦችን ነው።
ይህም አሜሪካ በቀጠናው እንደ ቻይና እና ሩሲያ ያሉ ተፎካካሪዎቿ ላይ የበላይነት ይሰጣታል ተብሏል።
"እነዚህ ስልታዊ ይዞታዎች አሜሪካ በቀጣናው የምታደርገውን ተሳትፎ የማጠናከር እድል ይሰጣሉ። የማይቋረጥ ወታደራዊ እና ሎጂስቲክ መዳረሻዎችን [ለአሜሪካ] በማረጋገጥ ሌሎች የውጭ ተወዳዳሪዎች በዚህ ወሳኝ ኮሪደር ውስጥ እንዳይገኙ ይከላከላሉ" ሲል ደብዳቤውን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ አስነብቧል።
ባሊዶግል ከዋና ከተማይቱ ሞቃዲሾ በስተሰሜን ምዕራብ በ90 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ የቦሳሶ ወደብ ከፊል ራስ ገዝ በሆነችው ፑንትላንድ ትገኛለች።
በዚህም የተነሳ የፌደራል መንግሥቱ ለአሜሪካ በችሮታ ለመስጠት ያቀረበውን ጥያቄ፣ የፑንትላንድ አስተዳደር ውድቅ ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።
የፑንትላንድ ባለስልጣናት በደብዳቤው ላይ እስካሁን አስተያየት የሰጡ ባይሆንም፣ ጋሮዌ ኦንላይን የተባለው የመገናኛ ብዙኃን ግን የሞቃዲሾው መንግሥት ለአሜሪካ ደብዳቤውን የጻፈው እነርሱን ሳያማክር እንደሆነ ገልጿል።
ይህም በፑንትላንድ እና በሞቃዲሾ መካከል ያለውን ግንኙነት የበለጠ ሊያሻከረው ይችላል።
በደብዳቤው ላይ የተገለፀው ሁለተኛው ወታደራዊ አየር ማረፊያ የሚገኘው ከዋና ከተማው በስተሰሜን ምዕራብ በምትገኘው ባሌዶግሌ ውስጥ ሲሆን በዚህ ስፍራ የሶማሊያ ወታደሮችን አልሸባብን ለመዋጋት የሚያደርጉትን ጥረት ለማገዝ የአሜሪካ ወታደሮች ስልጠና እየሰጡ ይገኛሉ።
በሶማሊላንድ ወደብ የውዝግብ መንስኤ ሲሆን ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጣናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ መሆኑ ይታወሳል።
በምላሹም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ለመስጠት እንዲሁም ከልማት ተቋማቷ ድርሻ ይኖራታል የሚል ነው።
ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ያቋረጠ ቁርሾ ውስጥ ከገቡ በኋላ በቱርክ አደራዳሪነት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።












