ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ድጋፍ አደርጋለሁ አሉ

የሶማሊያና የቱርክ ፕሬዚዳንቶች

የፎቶው ባለመብት, Republic of Türkiye Directorate of Communications

በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተጀመረው ሂደት ዘላቂ ሰላም እስኪያመጣ ድረስ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን ገለጹ።

ፕሬዚዳንት ኤርዶዋን ይህንን የተናገሩት የሶማሊያውን ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ ሞሀሙድን ሐሙስ፣ መጋቢት 18/ 2017 ዓ.ም በፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥታቸው ባገኙበት ወቅት ነው።

ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተደረሰ የባህር በር መግባቢያ ስምምነት ውጥረት ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርኩ ፕሬዝዳንት አሸማጋይነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ችግራቸውን ለመፍታት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ሁለቱ መሪዎች በቱርክ እና ሶማሊያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዲሁም ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በዚህ ውይይት መዳሰሳቸውን የቱርክ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ኤርዶዋን ቱርክ ለሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ ስፍራ እንደምትሰጥ ተናግረዋል።

በዚህም ለሶማሊያ ደህንነት፣ የግዛት አንድነት እና የኢኮኖሚ ልማት አገራቸው የምታደርገው ድጋፍ እንደማያቋርጥ ለፕሬዚዳንቱ አረጋግጠውላቸዋል።

በዚህም አንድምታ ኢትዮጵያን ያነሱት ኤርዶዋን ከኢትዮጵያ ጋር የተጀመረው ሂደት ዘላቂ ሰላም እስኪያመጣ እንዲሁም መረጋጋት እስኪሰፍን ድረስ ድጋፋቸው ባላሰለሰ ሁኔታ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል።

በቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን አደራዳሪነት ታኅሣሥ 2/2017 ዓ.ም. የተደረሰው የአንካራ ስምምነት ለአንድ ዓመት ያህል በቃላት ጦርነት ሲወዛገቡ የነበሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ልዩነታቸውን በድርድር ጠረጴዛ ለመፍታት እንዲቀመጡ ያደረገ ነው።

ሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ልዩነታቸውን በሰላም ቋጭተው ስምምነት ላይ ለመድረስ በሚያደርጉት ጥረት አሸማጋይ የሆነችው ቱርክ፤ የአገራቱን የመጀመሪያ ዙር የቴክኒክ ድርድር የካቲት 11/ 2017 በአንካራ አሰናድታ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በመጀመሪያው ዙር የቴክኒክ ድርድር ሁለቱም ልዑካን የአንካራው ስምምነት መፈጸም ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት ነው ተብሏል።

ልዑካኑ የአገራቱ መሪዎች በአንካራ ስምምነት ላይ ያስቀመጡትን ራዕይ ወደ ተግባር ለመቀየር እንዲሁም ለጋራ የዘላቂ ልማት ተጠቃሚነት መሠረት ለመጣል ተጨባጭ ሥራ መጀመራቸውን የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው አክሏል።

ቀጣዩ የቴክኒክ ድርድርም ለመጋቢት 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ መያዙም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ፊርማቸውን ባኖሩበት የአንካራ ስምምነት መሠረት፤ "ሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።"

ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቱ "የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ" ሲል ያትታል።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ መሆኑ ይታወሳል።

ቱርክ የሶማሊያ የረዥም ጊዜ አጋር ስትሆን የሰብዓዊ እርዳታ፣ ወታደራዊ ስልጠና እና የልማት እርዳታን ታደርጋለች።

የቱርክ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት መግለጫ እንዳስታወቀው መሪዎቹ በተጨማሪ በጸረ-ሽብርተኝነት ዙሪያ ያለውን ትብብር በተመለከተ ተወያይተዋል።

ውይይቶቹ ከጸጥታ ጉዳዮች በተጨማሪ የኢኮኖሚ፣ የንግድ እና የመከላከያ ትብብርን ያካተቱ ናቸው።

ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ ንግድን ለማሳደግ እና የመከላከያ ኢንዱስትሪ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ውይይቶች ማድረጋቸውን ከዳይሬክቶሬቱ የተገኘው መረጃ ያስረዳል።