በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ክፉኛ አቁስላ፣ ማርካ ያከመችው የጁባላንዱ ፕሬዚዳንት ማዶቤ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"የብዙ ኢትዮጵያዊ ደም ነው የወሰደው። የኢትዮጵያ ደም ነው ያለህ እንለዋለን" ይህ በሶማሊያ የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው ለአሁኑ የጁባላንድ ግዛት ፕሬዚዳንት ማዶቤ በቀልድ መልኩ ጣል ያደርጉላቸው ነገር ነው።
ይህ በቀልድ የተለወሰ መሪር እውነታ ነው።
እውነታው የሶማሊያዋን ራስ ገዝ ጁባላንድን ላለፉት 12 ዓመታት ያስተዳደረው ማዶቤ በአንድ ወቅት በኢትዮጵያ ጦር ክፉኛ ቆስሎ በአዲስ አበባ ህክምና አድርጓል።
አምባሳደር ወንድሙ፤ ማዶቤ በኢትዮጵያ፣ ከኢትዮጵያውያን የተሰጠውን በርካታ የደም ልገሳ ለመግለጽ ነው ይህንን አገላለጽ የተጠቀሙበት።
ማዶቤ ቆስሎ የተማረከው በአገሩ ሶማሊያ ውስጥ ነው፣ ከዛሬ 19 ዓመታት በፊት ወደዚያው ዘልቆ በገባው የኢትዮጵያ ጦር።
በወቅቱ በ40ዎቹ ዕድሜ ገደማ የነበረው ማዶቤ የአልሻባብ ቡድን መሥራች እንዲሁም የቡድኑ ቀኝ እጅ ነበር።
ከታጣቂ ቡድኑ አመራርነቱ ጋር ተያይዞ በአፍሪካ ቀንድ በአሸባሪነት በኢትዮጵያ እንዲሁም በአሜሪካም ጭምር መታደን ጀመረ።
የፀረ ሽብር ዘመቻ ማፋፋሟን ይፋ ያደረገችው አሜሪካ ጥቃት ከፈጸመባት አልቃይዳ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ማዶቤን በጥቁር መዝገቧ ማካተቷን አስታወቀች።
አሜሪካ ማዶቤን ለመማረክ እንዲሁም ለመግደል ሙከራዎችን አድርጋለች።
ይባስ ብሎ በቀጥታ በእሱ ላይ ያነጣጠሩ የአየር ጥቃቶችን በሶማሊያ ላይ ፈጽማለች።
አልተሳካም እንጂ ከተማረከም በኋላ ስጡኝ ብላለች።
የኢትዮጵያም ወታደሮች በበኩላቸው ማዶቤን የመግደል ሳይሆን የመማረክ ተልዕኮን አንግበው ጦሩን ይመሩ ከነበሩት አንዱ እና ማዶቤን የማረኩት ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር አለምሰገድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ ማዶቤ በአገሪቱ እንዲሁም በቀጣናው ታዋቂ ጦረኛ መሆኑንም የተፋለሙት ይመሰክሩለታል።
ማዶቤ የሶማሊያን የሽግግር መንግሥትን ደግፎ ጣልቃ የገባውን የኢትዮጵያ ጦር የፈተነ የጦር አዛዥ እንደሆነ ይነገርለታል።
በቀድሞ አልኢትሃድ ኢስላሚያ እንዲሁም እሱን ተከትሎ በመጣው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አመራር የተመሠረተው ራስ ካምቦኒ ብርጌድ የተሰኘው የጦር ክንፍን በማንቀሳቀስ በበርካታ ግንባሮች ተፋልሟል።
ማዶቤ ቅጽል ስሙ ነው፤ በቤተሰቡ ውስጥ የቆዳው ቀለም ከሌሎቹ ጠቆር በማለቱ የተሰጠው ስም።
ማዶቤ ጥቁሩ እንደማለት ሲሆን ትክክለኛ ስሙ መሐመድ አህመድ ኢስላም ነው።
የሼክነት ማዕረግም አለው።
ማዶቤ ቁልፍ የአልሻባብ ሰው ብቻ ሳይሆን አልሻባብንም በአንድ ወቅት በምክትልነት መርቷል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጦሯን ያዘመተችበት እንዲሁም የአልሻባብ ወላጅ የሆነው የሶማሊያ እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አመራር፣ የደቡባዊቷ ሶማሊያ ከተማ ኪስማዮ ሊቀመንበርም ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በ60ዎቹ አጋማሽ ዕድሜ ላይ የሚገኘው የአሁኑ ማዶቤ በደቡባዊ ሶማሊያ ራስ ገዝ ከሆኑት ግዛቶች ጠንካራ የሆነችው የጁባላንድ መሪ ነው።
2.5 ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት ጁባላንድ የአገሪቱ የስበት ማዕከል እንዲሁም ባላት የተፈጥሮ ሃብት የተነሳ የሶማሊያ የዳቦ ቅርጫት ትሰኛለች።
የግዛቲቱ ዋና ከተማ ኪስማዮ፣ ከአገሪቱ ታላላቅ ከተሞች እንዲሁም ትልቅ ወደብ አንዷ ናት።
በተፈጥሮ የዘይት፣ ጋዝ እና ከሰል ሃብት ክምችት የታደለችው ምርታማዋን ኪስማዮን/ጁባላንድን ለመቆጣጠር አልሻባብን ጨምሮ ሌሎች የሶማሊያ ሚሊሻዎች ተፋልመዋል።
ማዶቤ፤ ኬንያ እና ኢትዮጵያ በሚያዋስኗት ጁባላንድ እንደ ፕሬዚዳንት እንዲያውም ከማዕከላዊው መንግሥት በላይ ነው የሚታየው።
የፌደራሉ መንግሥትን ሥልጣንን ይገዳደራል።
ካልተስማማበት ፍንክች የሚል ሰው አይደለም።
ጦርም ለመማዘዝም ወደኋላ አይልም።
ፈገግታ የማይለየው ማዶቤ በቅርቡ ከሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ጋር ከምርጫ ጋር በተያያዘ እሰጣገባ ውስጥ ገብቶ ነበር።
የፌደራሉ መንግሥት ከእኔ እሽታ ውጭ ምርጫ አድርጓል ባለው ማዶቤ ላይ የእስር ትእዛዝ ሲያወጣ፣ አይነኬው ማዶቤ ዝም ብሎ አልተመለከተም።
በምላሹ ማዶቤ በፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ መሐመድ ላይ የእስር ትዕዛዝ አወጣ።
ፕሬዚዳንቱን በሀገር ክህደት፣ የእርስ በርስ ጦርነት በማነሳሳት፣ የሀገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማደፍረስ ሞክረዋል አላቸው።
በእስር ትዕዛዝ ብቻ አልተወሰነም።
ከራስ ካምቦኒ በኋላ የመሠረተው ዳርዊሽ የተሰኘ ልዩ ኃይሉ ከሶማሊያው ብሔራዊ ጦር ጋር ግጭት ውስጥ ገብቷል።

የፎቶው ባለመብት, SM
የማዶቤ መማረክ
አልኢትሃድ አል ኢስላሚያን በአውሮፓውያኑ 1980ዎቹ በመቀላቀል የተዋጊነት ሕይወቱ የተጀመረው ማዶቤ ከአልሻባብ መሥራቾች አንዱ ነው።
ወቅቱ በአውሮፓውያኑ 2006 ነበር።
ሞቃዲሾ እና ደቡባዊ መካከለኛ ሶማሊያ የሚገኙ አካባቢዎች በእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት ቁጥጥር ስር የነበሩበት ወቅት ነው።
በቡድኑ ውስጥ ያሉ አንዳንድ መሪዎች ኅብረቱ ትክክለኛ ጂሃድ እያካሄደ አይደለም በማለት ጠንከር ያለ የተዋጊ ክንፍ መመሥረት ፈለጉ።
ሃራካት አል ሻባብ አል ሙጃሂዲን (የታጋይ ወጣቶች ንቅናቄ) ወይም በአጭሩ አልሻባብ ተመሠረተ።
አህመድ ማዶቤም በምክትል መሪነት ተመረጠ።
ማዶቤ 'አልሻባብ ዊክንድ' በሚል በ2012 በወጣ የቪኦኤ እንግሊዝኛው ጽሁፍ ላይ ባደረገው ቆይታ "በፓኪስታን የተማረው ኢስማኤል አራሌ መሪ እንዲሆን ሐሳብ ቀርቦ እኔ ራስካምቦኒን ወክዬ በምክትልነት ተመረጥኩ" ብሏል።
ቡድኑ በኅብረቱ ውስጥ የራሱን የበላይነት ለመጫን እንዲሁም አገዛዙን ለማስፋት እየሞከረ ባለበት ወቅት የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሶማሊያ ገቡ።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጦሯን ካስገባች በኋላ የአልሻባብ/የኅብረቱ አመራሮችን በጽኑ ማደን ጀመረች።
በዓመቱም የአልሻባብ ምክትል የሶማሊያ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የኪስማዮ ሊቀመንበር ማዶቤ ተማረከ።
በስምንት ጥይት ተመትቶ፣ ክፉኛ ቆስሎ ነበር የተማረከው።
ተማርኮም ወደ አዲስ አበባ ተወሰደ።
በዚያን ወቅት ማርከው ወደ አዲስ አበባ ያመጡት የኢትዮጵያን ክፍለ ጦር ሲመሩ ከነበሩት አንዱ ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር አለምሰገድ ናቸው።
ማዶቤ "የኢትዮጵያን ጦር እልህ አስጨራሽ በሆነ ሁኔታ ተፋልሟል" ይላሉ ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር።
ኢትዮጵያ ከኅብረቱ እንዲሁም ከሌላኛው የኅብረቱ ክንፍ አልሻባብ ጋር ስትዋጋ ሙሉ የጁባላንድን የጦር ግንባር ይዞ እስከ ሽግግር መንግሥቱ መቀመጫ በነበረችው ባይዶዋ ጫፍ ድረስ የተፋለመው ኃይል የማዶቤ እንደነበር ኮሌኔሉ ያወሳሉ።
ማዶቤ በተፋለመባቸው ግንባሮች የኢትዮጵያን ክፍለ ጦር ሲመሩ የነበሩት ጄነራል ገብሬ ዲላ እና ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር ሲሆኑ፤ የማረኩትም እነዚሁ የጦር አመራሮች ናቸው።
ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር እንደሚሉት የኢትዮጵያ ጦር ማዶቤን ለመማረክ ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ዘመቻ ነበር የተካሄደው።
ማዶቤ እንዳይገደል እና እንዲማረክ "መመሪያ ከበላይ ተሰጥቶን ነበር" ሲሉ ኮሎኔሉ ያስታውሳሉ።
"እሱን በሕይወት ለመያዝ ተጠንቅቀን እንደተባልነው ነው የያዝነው። እሱም ወታደሮቻችንን እያቆሰለ እስከ መጨረሻው ተዋጋን።"
በመጨረሻም ማዶቤ በስምንት ጥይት ተመትቶ ወደቀ።
ክፉኛ ቆስሎ በደቡባዊ ሶማሊያ በርዳሌ በምትባል ስፍራ፣ ተማረከ።
ኮሌኔሉ እንደሚሉት በነበረው ውጊያ ከስምንት ታጣቂዎች በሕይወት የተረፈው ማዶቤ ብቻ ነበር።
በወቅቱ በከባድ ሁኔታ ቆስሎ ስለነበረ "ሕይወት አልነበረውም" ይላሉ ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።
በሞት እና በሕይወት መካከል የነበረው ማዶቤ ወደ አዲስ አበባ ተወሰደ።
ኮሌኔል ገብረእግዚአብሔር "ራሴ ነኝ በሄሊኮፕተር ወደ አዲስ አበባ የወሰድኩት" ሲሉ ያስረዳሉ።
በወቅቱ የደቡብ አፍሪካው ሜይል ኤንድ ዘ ጋርዲያን ጥር መጨረሻ 2007 ይዞት የወጣው ጽሁፍ ላይ ኢትዮጵያ አቁስላ የማረከችውን ማዶቤን "ግዳይ የመጣል ያህል" ስታሳይ ነበር ብሏል።
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ጦር ግንባር ከገደለቻቸው ውስጥ በምሥራቅ አፍሪካ የአልቃይዳ ርዕዮተ ዓለም እንዲሁም ስትራቴጂክ ከፍተኛ መሪ የነበረው ታሪቅ አብዱላህ ወይም አቡ ታልሃ አል ሱዳኒ ተጠቃሽ ነው።
አል ሱዳኒ የኦሳማ ቢንላንደን ቅርብ ሰው እና በቦምብ ዕውቀቱ የረቀቀ ነው ይባል የነበረ ሲሆን፣ አሜሪካም በጥብቅ ትፈልገው ነበር።
አሜሪካ ለ220 ሰዎች ሞት ምክንያት ለሆኑት በታንዛኒያ እና በኬንያ ኤምባሲዎቿ ላይ በተፈጸሙት ጥቃቶች ውስጥ አል ሱዳኒ እጁ አለበት ትላለች።
አሜሪካ ከዚህ ቀደም በአየር ጥቃት ልትገድለው ሞክራ ከ70 በላይ አርብቶ አደሮች ቢገደሉም አል ሱዳኒ አምልጧል።
ሆኖም የኢትዮጵያ ጦር በፈጸመው ጥቃት እንደተገደለ ኮሌኔል ገብረእግዚአብሔር እና አምባሳደር ወንድሙ አረጋግጠዋል።

የፎቶው ባለመብት, SM
በሶማሊያ የመሐመድ ሲያድ ባሬ አገዛዝ መውደቅን ተከተሎ ከጎሳ በተጨማሪ የእስልምና እምነትን መሠረት ያደረጉ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ማንሰራራታቸውን Stabilization and Common Identity: Reflections on the Islamic Courts Union and Al-Itihaad' የተሰኘ ጽሁፍ ይጠቅሳል።
ከነዚህም ውስጥ ተጠቃሾቹ የሲያድ ባሬን ከሥልጣን መውደቅ ተከትሎ ተፈጥሮ የነበረውን የደኅንነት እና የፀጥታ ክፍተት በመሙላት ተንሰራፍተው የነበሩ ወንጀሎችን ይቆጣጠሩ የነበሩት እስላማዊ ፍርድ ቤቶች ናቸው።
ፍርድ ቤቶቹ ማዕከላዊ መንግሥት ባልነበራት ሶማሊያ ሕግ እና ሥርዓትን ለማስፈን ይሞክሩ እንደነበር ይኸው ጽሁፍ ይጠቅሳል።
ከፍርድ ቤቶቹ በተጨማሪ በእስልምና እምነት ላይ ፖለቲካን መሠረት አድርጌያለሁ የሚለው እና በአውሮፓውያኑ 80ዎቹ እንዲሁም 90ዎቹ ይንቀሳቀስ የነበረው አልኢትሃድ አል ኢስላሚያም ሌላኛው ንቁ ድርጅት ነበር።
ሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት ተንኮታኩቶ ሥርዓት አልባ ሆና በጦር አበጋዞች እጅ ስትወድቅ ኢትዮጵያም የተለያዩ ወገኖችን ትደግፍ እንደነበር የተለያዩ ጽሁፎች ዋቢ ያደርጋሉ።
አጋር የሚሆናትንም ማዕከላዊ መንግሥትን አጥብቃ ትሻ ነበር።
አብዱላሂ የሱፍ በ2004 (እአአ) የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ፕሬዚዳንት ሆነው ወደ ሥልጣን እንዲመጡ ከፍተኛ ሚና ተጫውታለች።
ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ሲአይኤም የጦር አበጋዞችን በማስታጠቅ እና በገንዘብ ድጋፍ ያደርግ ነበር።
በጆርጅ ቡሽ የሚመራው መንግሥት ይህ እንዳላዋጣው ሲያውቅ ደካማውን የሽግግር መንግሥት መደገፍ ጀመረ።
ሆኖም የፍርድ ቤቶቹ ስብስብ የሆነው የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት የጦር አበጋዞችን ጥምረት በማሸነፍ በ2006 ሞቃዲሾን ተቆጣጠሩ።
በወቅቱ አገሪቱን ይመሩ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት አብዛኛው አመራር ከአል ኢትሃድ አል እስላሚያ የመጣ መሆኑ ለአገራቸው ስጋት የጋረጠ መሆኑን ተናገሩ።
የኢትዮጵያን ኦጋዴን ግዛትን ያካተተች ታላቋን ሶማሊያን ለመፍጠር ያለመው አል ኢትሃድ በርካታ የቦምብ ጥቃቶችን በኢትዮጵያ ፈጽሟል።
አል ኢትሃድ በ1990ዎቹ በድሬዳዋ በገበያ ላይ የቦምብ ጥቃት ፈጽሞ አስራ አምስት ሰዎች ተገድለዋል፤ እንዲሁም በአዲስ አበባ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተፈጸመው ጥቃት አራት ሰዎች ሲገደሉ 20 ሰዎች ቆስለዋል።
አል ኢትሃድ የኢትዮጵያ የትራንስፖርት ሚኒስትር የነበሩትን አብዱል መጂድ ሁሴንን ለመግደል ሙከራ በ1996 አድርጎ ኃላፊነት መውሰዱን በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ በ2016 የወጣውና የታጣቂ ቡድኖችን እንቅስቃሴ የሚከታተለው 'ማፒንግ ሚሊታንት ኦርጋናይዜሽንስ' ጽሁፍ ያስረዳል።
ኢትዮጵያ በአልኢትሃድ መሪዎች እንዲሁም የጦር ሰፈሮች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ለመፈጸም ጦሯን ወደ ሶማሊያ አስገብታ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄዷ ይታወሳል።
የእስላማዊ ፍርድ ቤቶችን ኅብረት መሪ ሼክ ሐሰን ዳሂር አዌይስ በአንድ ወቅት የአል ኢትሃድ አል ኢስላሚያ መሪ ነበር።
ሼክ ሐሰን አዌይስ ሶማሊያን በእስላማዊ ፍርድ ቤቶች አንድ ለማድረግ እንዲሁም እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ከፍተኛ እንቅፋት የሆነችባቸው ኢትዮጵያ እንደሆነች አወጁ።
የአዌይስና የሌሎች አመራሮች ኦጋዴንን ያካተተች ሶማሊያን የመመሥረት እንዲሁም የኅብረቱ ማዕከላዊ ሥልጣንን መቆጣጠር ኢትዮጵያ አልቀበለውም አለች።
መቀመጫውን ባይዶዋ አድርጎ የነበረው የሽግግር መንግሥቱ ለኢትዮጵያ ባደረገው ግብዣ ጦሯን ወደ ሶማሊያ በማስገባት ጣልቃ ገባች።
ወረራ ነው ያሉት የኅብረቱ አመራሮች ሁሉም ሶማሊዎች ኢትዮጵያን ለመታገል በአንድነት እንቁም አሉ። ጂሃድ (ቅዱስ ጦርነትም) አወጁ።
በታኅሣሥ 2006 ገደማ ኅብረቱ በኢትዮጵያ ጦር ተሸነፈ።
የኢትዮጵያ ጦር የኅብረቱ ጠንካራ ይዞታ ከነበረው የደቡባዊ ግዛት ለማስወጣት ሳምንታት ብቻ ነበር የወሰደበት።
በርካታ አመራሮቹም ሀገር ጥለው ተሰደዱ።
የኅብረቱ መሪ ሼክ አዌይስ ከዚህ ቀደም ኅብረቱን ትደግፍ ወደነበረችው ኤርትራ ማፈግፈጉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ያጠናቀረው መረጃ ያሳያል።
ሼክ አዌይስ በአሥመራም ሆኖ በሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ እና ኬንያ ለሚሞከሩ ጥቃቶች የገንዘብና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ያሰባስብ እንደነበር ግለሰቡን አስመልክቶ የፀጥታው ምክር ቤት ያሰፈረው መረጃ ጠቅሷል።

የፎቶው ባለመብት, SM
ኢትዮጵያ በሶማሊያ ለሁለት ዓመት ከቆየች በኋላ የጽንፈኞችን ስጋት አስወግጃለሁ በማለት በአውሮፓውያኑ 2009 አካባቢ ወጣች።
ኅብረቱ ቢበተንም ሌላኛው ታጣቂ ክንፍ አልሻባብ ተጠናክሮ ወጣ።
የአልሻባብ መጠናከር ብቻ ሳይሆን በርካታ የሶማሊያ ግዛቶችን መቆጣጠር ቻለ።
ከአልቃይዳ ጋርም አጋርነትን መሠረተ።
ማዶቤ በኢትዮጵያ ጦር ከተማረከ ከሦስት ወራት በኋላ የአልሻባብ መሪ እስማኤል አራሌ ወደ ኤርትራ ለማቅናት ጂቡቲ ላይ እያለ በሲአይኤ በቁጥጥር ዋለ።
አሜሪካም በሽብር እጠረጥራቸዋለሁ የምትላቸውን እንዲሁም ከፍተኛ ስቃይ ትፈጽመበታለች ወደሚባለው ጓንታናሞ ቤይ ተላከ።
አልሻባብ ለመሪዎቹ መያዝ ፈጣን ምላሽ ሰጠ፤ ሁለቱንም በሌላ ተካቸው።

የፎቶው ባለመብት, The Ministry of Foreign Affairs of #Ethiopia
የማዶቤ የአዲስ አበባ ቆይታ
በከፋ ሁኔታ ቆስሎ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ማዶቤ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወሰደ።
በአዲስ አበባ የጦር ኃይሎች እና ፖሊስ ሆስፒታል ታክሟል።
የጦር መሪው በእነዚህ ሆስፒታሎች ከፍተኛ ህክምና ተደርጎለታል።
ማዶቤ የተሰጠውን የደም ልገሳ ለመግለጽ "የኢትዮጵያዊ ብዙ ደም ነው የወሰደው" ይላሉ አምባሳደሩ በፈገግታ።
እሱንም "የኢትዮጵያ ደም ነው ያለህ እንለዋለን። ከሞት ነው የዳነው። እንዳይሞት ብዙ ጥረት ተደርጓል" ሲሉም አምባሳደሩ ያክላሉ።
የማዶቤን መትረፍ "ከሞት አፋፍ ነው ያመለጠው" ሲሉ ነው ኮሌኔል ገብረ እግዚአብሔር እና አምባሳደር ወንድሙ የሚገልጹት።
ማዶቤ በአዲስ አበባ ሁለት ዓመት ቆየ።
"እየተኮላተፈም ቢሆን አማርኛ መናገር ቻለ" ይላሉ አምባሳደሩ።
በወቅቱ የወጡ የሚዲያ ዘገባዎች ማዶቤ በእስር ላይ እንደነበረ ቢገልጹም አምባሳደሩም ሆኑ ኮሌኔሉ "በጭራሽ" በማለት ያስተባብላሉ።
"እንደ እስረኛ ሳይሆን እንደ የኋላ የሰላም አጋር ለማድረግ ነው ያሰብነው። የሶማሊያ ጉዳይ በእስር የሚፈታ አይደለም" ሲሉ አምባሳደር ወንድሙ ያስረዳሉ።
እንዲያውም እንደ ልዩ እንግዳ ነበር ኢትዮጵያ ያስተናገደችው ይላሉ።
ሆኖም በርካታ ጠላት የነበረው ሰው ስለነበር ጥበቃ እንደነበረውም ኮሎኔሉ ያስታውሳሉ።
ኮሎኔሉ እንደሚሉት "ከታወቀ ጎሳ፣ ከታወቀ ቤተሰብ ነው የመጣው፤ ወንድማችን ነው። እስር ቤት ሳይሆን መወያየት ተመራጩ መንገድ ነበር።"
ከኦጋዴን ጎሳ የመጣው ማዶቤ በሶማሌ ክልልም ትልቅ ስፍራ ያለው ሲሆን፣ ቤተሰቦቹ እና ዘመድ አዝማዶቹ በክልሉ ነዋሪዎች ናቸው።
የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩት አብዲ ኢሌና ማዶቤ - ሬር አብዲሌ የተሰኘው የኦጋዴን ንዑስ ጎሳ አባል ናቸው።
ኦጋዴኖች በሶማሌ ክልል እንዲሁም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልቅ ስፍራ እንዳላቸው አምባሳደር ወንድሙ ያስረዳሉ።
ማዶቤ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ ውስጥ ባሉ ኦጋዴኖች እንደ ታላቅ መሪ ይታያል።
በኮሎኔል ገብሬ አገላለጽ ማዶቤ "እንደ ጋሻ እና ጦር የሚተማመኑበት ፤የጎሳ ከለላ እንዲሁም ተቀባይነትም ያለው ነው።"
ማዶቤ ህክምናውን ካጠናቀቀ በኋላም መቆያውን ያደረገው በብሔራዊ ሆቴል የነበረ ሲሆን፣ በነጻነትም ነበር የሚንቀሳቀሰው።
ኮሌኔል ገብሬ እንደሚሉት ማዶቤ በኢትዮጵያ ቆይታው ሚስት አግብቷል።
"ኧረ እንዲያውም ልጅ ወልዷል" ይላሉ።
ዋነኛው የማዶቤ የአዲስ አበባ ቆይታ ያተኮረው ጎራ ማስቀየር ነበር።
ኮሎኔሉ እንደሚሉት "ዋነኛው ሥራችን እሱን ዲራዳካላይዝ [ከጽንፈኝነት ማውጣት] ነበር።"
ማዶቤን ከአልሻባብም ሆነ ከኅብረቱ በተጻራሪ ለማስቀመጥ ወይም በኮሌኔል ገብሬ ቃል 'ማዶቤን በመለወጥ' የላይኛው አመራሮች 'ኢንቨስት አድርገውበታል'።
ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ፣ በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን እንዲሁም የጤና ከነበሩት ቴድሮስ አድሃኖም ጋር በተደጋጋሚ ይገናኝ ነበር።
እንደ ኮሌኔል ገብሬ ከሆነ "ጽንፈኝነት ማንንም እንደማይጠቅም፤ ሶማሊያንም ሆነ ኢትዮጵያን ያፈርሳል። ኢትዮጵያን ይበታትናል" የሚሉ ውይይቶች በተደጋጋሚ ከማዶቤ ጋር የሚነሱ ነበሩ።
"መታከም ብቻ አይደለም" ኮሌኔል ገብሬ የማዶቤን የኢትዮጵያውን ቆይታ ሲገልጹ "'ብሬይን ዋሽድ' ሆነ። ከዚያ ጽንፈኝነት፣ ከአክራሪነት ወጣ።"
"ማዶቤን ከሽብርተኝነት እንዲሁም ከጽንፈኝነት ማውጣት ትርጓሜው ለእኛ ቀላል አይደለም" ይላሉ።
አክለውም "አህመድ ማዶቤ ምስጋና ይግባውና ትክክል ነው ብሎ ሃሳቡን ተቀበለው። በጣም የምናንደንቀው ጓደኛችን ነው" ሲሉም ለአስራ አምስት ዓመታት በሶማሊያ የቆዩት ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር ይናገራሉ።
የአንድ ወቅት ማራኪው ኮሎኔሉ ከማዶቤ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው።
በፖለቲካ ቋሚ ጠላት የለም የሚለው የማዶቤም ሕይወት ማሳያ ነው።
ጦረኛው እና ፖለቲከኛው ማዶቤ ቅራኔያቸው በማይታረቁ በሚመስሉ ጎራዎች ተሰልፏል።
ከአል ኢትሃድ የሚጀምረው የትግል ሕይወቱ ከኢትዮጵያ ጋር ለዘመናት በተጻራሪ ጎን አስቁሞታል።
ከኢትዮጵያ ጋር በተቃራኒ ጎን ተሰልፎ ለአልሻባብ እና ለኅብረቱ ቆሞ በጽኑ ተፋልሟል።
ከአዲስ አበባ ቆይታው በኋላም የኢትዮጵያ ቅርብ አጋር ሆኗል።
ከአልሻባብ ተጻርሮ የቀድሞ ቡድኑን ወግቷል።
ማዶቤ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሶማሊያ ፖለቲካ እጇን የምታስገባው ኬንያ ጋር ቅርብ አጋርነት መፍጠር ችሏል።
ወደ ጁባላንድ ፕሬዚዳንትነት ለመምጣት ኬንያ እና ኢትዮጵያ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውለታል።
ኢትዮጵያ ማዶቤን አቁስላ እና ማርካ ከጎኗ የማሰለፍ ዕቅድን የጠነሰሰችው ብዙ ፈላጊዎች በነበሩት ሁኔታ ነው።
በሽብር እፈልጋቸዋለሁ የምትላቸውን ተጠርጣሪዎችን ወደ ጓንታናሞ ቤይ እየወሰደች የነበረችው አሜሪካ ማዶቤ አዲስ አበባ ከተወሰደ በኋላ አሳልፋችሁ ስጡኝ ብላ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ማዶቤን ለመስጠት ፍላጎት አልነበረውም።
"የኢትዮጵያ መንግሥት ማዶቤ እንዲገደል ሆነ እንዲታሰር ፈቃደኛ አልነበረም" ይላሉ ኮሎኔሉ።
አምባሳደር ወንድሙም ይህንኑ ያጠናክራሉ "አሜሪካውያኑ እንዳያጠፏቸው ጥንቃቄ ስለምናደርግ፤ አናስረክብም አልናቸው።"
ኢትዮጵያ ጦሯን ወደ ሶማሊያ ስታስገባ በአሜሪካ ተልካ እንዳልሆነ የሚጠቅሱት አምባሳደሩ ዋነኛው ምክንያታቸው "የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ነው" ይላሉ።
ለዚህም ምክንያቱ "አንደኛ ራሳችን ነው የያዝነው። ሁለተኛው ዓላማችን እንደእነዚህ ዓይነት መሪዎች ለቀጣዩ ፌዝ [ሂደት] ለሰላሙ ሥራ ይረዳሉ ብለን ስላሰብን፤ አሜሪካውያኖቹ እንዳያጠፏቸው ጥንቃቄ ነበረን" በማለት ይገልጻሉ።
ሆኖም የአሜሪካ የስለላ ሳተላይቶች መረጃ ከኢትዮጵያ መከላከያ ጋር መቀያየርን ጨምሮ በጥብቅ በጋራ ይሠሩ እንደነበር አምባሳደር ወንድሙም ሆነ ኮሎኔሉ የሚያምኑት ጉዳይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ ማዶቤን ለምን ፈለገችው?
አሜሪካ መስከረም 11/2011 (እአአ) በኒው ዮርክ የሚገኘውን የዓለም የንግድ ማዕከል ያወደመውን የአውሮፕላኖች ጠለፋ የአየር ጥቃት ተከትሎ ፀረ-ሽብር በሚል በተለያዩ አገራት ላይ ጥቃቶችን ያፋፈመችበት ወቅት ነው።
ጥቃቱ ከደረሰ ከስድስት ዓመታት በኋላ በአፍሪካ ቀንዷ ሶማሊያ መሽገዋል ያለቻቸውን የአልቃይዳ ከፍተኛ አመራሮችን ለመያዝ ወይም ለመግደል ዘመቻ ጀመረች።
በዚህም አልቃይዳ ጋር ትስስር አላቸው በተባሉት በአልኢትሃድ፣ በእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ኅብረት እና በአልሻባብ አመራሮች ላይ አነጣጥራ ነበር።
አልኢትሃድን በወቅቱ ሱዳን መቀመጫውን አድርጎ በነበረው በአልቃይዳው ቁንጮ ሰው እና የሳዑዲው ቱጃር ቢንላንደን በገንዘብ ይደገፍ የነበረ ሲሆን፣ ከመስከረሙ ጥቃት ጋር ተያይዞ በአሜሪካ በአሸባሪነትም ተፈርጇል።
አሜሪካ በተለይም በ1998 በኬንያ እና ታንዛኒያ ኤምባሲዎቿ ላይ በተፈጸመው ጥቃቶች እጃቸው አለባቸው ያለቻቸውን የአልቃኢዳ መሪዎች በሶማሊያ እየፈለገች ነበር።
በእነዚህ ኤምባሲዎች የተፈጸሙ ጥቃቶች ከኅብረቱ ጋር ቁርኝት ያለው የራስ ካምቦኒ ብርጌድ የጦር ካምፕ አልቃይዳን ጨምሮ ለሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ለማሠልጠኛነት ጥቅም ላይ ውሏል የሚለው ነው።
የራስ ካምቦኒ ብርጌድ መሥራች ሐሰን አብዱላህ ኼርሲ አል ቱርኪ ከ1990ዎቹ ጀምሮ ከአልቃይዳ ጠንካራ ግንኙነት እንደነበራቸው በስታንፎርድ ዩኒቨርስቲ የወጣውና የታጣቂ ቡድኖችን እንቅስቃሴ የሚከታተለው 'ማፒንግ ሚሊታንት ኦርጋናይዜሽንስ' ጽሁፍ ያስረዳል።
አል ቱርኪ የኅብረቱ እንዲሁም ከዚያ ቀድሞ የነበረው አል ኢትሃድም እንዲሁ የጦር አዛዥ ነበሩ።
አሜሪካ በ2007 በሶማሊያ ላይ የአየር ጥቃቷን ስትፈጽም የተጠቀመችው የምሥራቃዊ ኢትዮጵያ አየር ማረፊያን እንደሆነ በወቅቱ 'U.S. Used Base in Ethiopia to Hunt Al Qaeda' በሚል ርዕስ የወጣው የኒውዮርክ ታይምስ ጽሁፍ አስነብቧል።
አሜሪካ ምሥጢራዊ የሆነ 'ታስክ ፎርስ 88' የሚባል ግብረ ኃይል አቋቁማ በኢትዮጵያ እና በኬንያ በኩል ወደ ሶማሊያ ጦር ማስገባቷን ይኸው ዘገባ ያትታል።
ይህም ኢትዮጵያ በሶማሊያ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ጥቃት ከጀመረች ከዓመት በኋላ ማለት ነው።
በዚያው ዓመት ታኅሣሥ መጨረሻ ሁለት ኤሲ 130 የተሰኙ የጦር አውሮፕላኖች በምሥራቃዊ ኢትዮጵያ ትንሽ አየር ማረፊያ ደረሱ።
ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው አፍጋኒስታን ውስጥ የሠለጠነው ወታደራዊ አዛዥ እና ከእስላማዊ ፍርድ ቤቶች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች አንዱ እና ሌላኛው የአልሻባብ አመራር በሆነው አደን ሃሺ አይሮ ላይ ነበር።
ጥቃቱ ከተፈጸመ ከበርካታ ሰዓታት በኋላ የኢትዮጵያ ወታደሮች እና አንድ የአሜሪካ ልዩ ኦፕሬሽን ቡድን ወደ ስፍራው ደርሰው ስምንት ሰዎች መሞታቸውን እንዲሁም ሦስት ሰዎች መቁሰላቸውን አረጋግጠዋል።
በፍርስራሹ ውስጥ የአደን በደም የተጨማለቀ ፓስፖርት እና ሌሎች እቃዎች ማግኘታቸውን ተከትሎ ሳይጎዳ ወይም ሳይሞት አልቀረም አሉ።
ሁለተኛ ጥቃት ያነጣጠረው በእስላማዊ ፍርድ ቤት ከፍተኛ አመራር በሆነው ሼክ አህመድ ማዶቤ ላይ እንደነበር ዘገባው አስነብቧል።
ማዶቤ ከዚህ ጥቃት ተርፏል።
በኋላ ላይ በኢትዮጵያ መማረኩን የአሜሪካ ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።
ማዶቤ ከኢትዮጵያው ቆይታ በኋላ
ከህመሙ ያገገመው ማዶቤ ከሁለት ዓመታት የኢትዮጵያ ቆይታ በኋላ ወደ ጂቡቲ አመራ።
በጂቡቲ የሶማሊያ ብሔራዊ መንግሥት ይመሥረት በሚል የተለያዩ ቡድኖች አንድ ላይ የሚመጡበት ጉባኤ ተካሄደ።
ጉባኤውን በማስተባበር የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ትልቅ ሚና ነበረው።
ለሶማሊያ አመራሮች ማዶቤ የዚህ ሂደት አካል መሆን አለበት በሚል ማሳመን የነ ኮሎኔል ገብሬ ተግባር ነበር።
በጊዜው የኢትዮጵያ መንግሥት እና ኢጋድን ወክለው በጂቡቲው ሂደት ላይ ነበሩ ራሳቸው ኮሌኔል ገብረእግዚአብሔር።
ከሶማሊያ አመራሮች ጋር ተስማምተው ከተማመኑ በኋላ ለኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ሪፖርት አደረጉ።
የኢትዮጵያ መንግሥት አመራሮች ደግሞ በቀጥታ በአውሮፕላን ማዶቤን ወደ ጂቡቲ ላኩላቸው።
ከጂቡቲ አየር ማረፊያ የተቀበሉትም ራሳቸው ኮሌኔሉ ነበሩ።
በዚህም ጉባኤ የሽግግር ጊዜ መንግሥቱን ይመሩ የነበሩት አብዱላሂ የሱፍ ሥልጣናቸውን ለቀው ሸሪፍ ሼክ አህመድ በ2009 ፕሬዚዳንት ሆኑ።
ጉባኤውን የተቀላቀለው ማዶቤ የፌደራሉ መንግሥት የፓርላማ አባል ሆኖ ወደ ኪስማዮ አቀና።
ነገር ግን በፓርላማ አባልነቱ የቆየው ለጥቂት ጊዜ ነበር፤ ወዲያውኑ "አላሠሩኝም" ብሎ ከፓርላማ አባልነቱ ለቀቀ።
ሆኖም ኢትዮጵያ ከነበረው ቆይታ በኋላ አጋርነቱን ቀየረ።
ኢትዮጵያ ጋር የተደረሰ ስምምነት ነበር?
እንደ ማዶቤ ያሉ መሪዎች በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንደሚኖር አምባሳደር ወንድሙ አጽንኦት ይሰጣሉ።
"እንደ ልጅ አትልኪያቸውም" ሲሉም ንግግራቸውን ያጠናክራሉ።
አልሻባብን ለማዳከም እና ለመቆጣጠር ከወታደራዊ መንገድ በላይ ፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ መፍትሄ ያስፈልገዋል በሚል ፖሊሲ ኢትዮጵያ ትመራ እንደነበር ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ በወቅቱ ወታደራዊ ጣልቃ መግባትን ጨምሮ በሶማሊያ ላይ ከፍተኛ ትኩረት ያደረገ የውጭ ፖሊሲን የምትከተል ይመስል ነበር።
ለአራት ዓመታት ያህል በሶማሊያ በአምባሳደርነት ያገለገሉት አምባሳደር ወንድሙ "ሶማሊያ ላይ ያለን ትኩረት ተመጣጣኝ ያልሆነ [ዲስ ፕሮፖርሽናል] ይመስላል" ሆኖም እውነታው ይህ አልነበረም ይላሉ።
በ1980ዎቹ እና 90ዎቹ በነበረው "የሽብርተኝነት እንቅስቃሴ" እንዲህ ዓይነት እርምጃዎችን ባትወስድ "ኢትዮጵያ አደጋ ውስጥ ትገባ ነበር" ሲሉ ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ በተለይም እንደ ባይዶዋ፣ ጌዶ ያሉ አዋሳኝ ስፍራዎችን እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ትኩረት ትሰጣቸዋለች ይላሉ።
ለአስራ አምስት ዓመታት በሶማሊያ የሠሩት ኮሎኔል ገብሬ 38 የሚደርሱ የሶማሊያ ጎሳዎችን ለያዘችው ኢትዮጵያ የሁለቱ አገራት ቁርኝት በጣም የጠበቀ ነው ይላሉ።
በሶማሊያ ጉዳይ "ኢትዮጵያ ትልቅ ባለ ድርሻ ናት" ይላሉ ኮሎኔሉ የነገሩን ክብደት ሲያስረዱ።

የፎቶው ባለመብት, SM
የማዶቤ የትግል ሕይወት
ማዶቤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በሞቃዲሾ ማጠናቀቁን 'ዘ አፍሪካን ሪፖርት' ከ12 ዓመት በፊት ባወጣው የሕይወት ታሪኩ ላይ ጠቅሷል።
ማዶቤ በኢትዮጵያ፣ ኦጋዴን እንደተወለደ እንደሚነገር ጽሁፌ ቢያትትም እሱ ግን ይህንን ሲናገር ተደምጦ አያውቅም።
በዩኒቨርስቲ ውስጥ የእስልምና ሕግ አጥንቷል።
የትግል ሕይወቱ የሚጀምረው አል ኢትሃድ ሶማሊያን በመቀላቀል ነው።
አል ኢትሃድ በሶማሊያ ትጥቅን ከሃይማኖት ጋር በማቆራኘት ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ይነገራል።
ለዓመታት ያህል የራስ ካምቦኒ ብርጌድን መርቷል።
የኢትዮጵያ ጦር መውጣቱን ተከትሎ እንዲሁም ማዶቤ ወደ ሶማሊያ ከተመለሰ በኋላ የራስ ካምቦኒ ብርጌድ ከሦስት ሌሎች ድርጅቶች ጋር ተቀላቀለ።
አራቱ ቡድኖች ሂዝቡል ኢስላምን ፈጠሩ።
በአልቱርኪ የሚመራው ራስ ካምቦኒ ብርጌድ ከአልሻባብ ጋር ጥምረት መፍጠሩ ለማዶቤ ተቀባይነት አልነበረውም።
ይህንንም ተከትሎ ማዶቤ በበኩሉ ከሂዝቡል ኢስላም ወጥቶ ራስ ካምቦኒ 'ሙቭመንት' የተሰኘ ጦር አቋቋመ።
የማዶቤ ራስ ካምቦኒ ጦር አልሻባብን በከፍተኛ ሁኔታ የሚጻረር ሆነ።
ማዶቤ የቀድሞ ቡድኑን አልሻባብ ለሶማሊያ ወሳኝ ስጋት ነው ሲል አወጀ።
ከአልሻባብም ጋር ኪስማዮን ለመቆጣጠር ፍልሚያ ተደረገ።
አልሻባብ የኪስማዮ ወደብን መቆጣጠሩን ተከትሎ የማዶቤ ጦር ወደ ኬንያ ድንበር አፈገፈገ።
ሆኖም ከኬንያ ባገኘው ድጋፍ አልሻባብን በ2012 መዋጋት እንደጀመረ ዘ አፍሪካ ሪፖርት በዚያው ዓመት ባወጣው ጽሁፍ አስነብቧል።
በመጨረሻም ማዶቤ አሸነፈ።
አልሻባብ ከኪስማዮ ከተባረረ በኋላ የማዶቤ ራስ ካምቦኒ ሙቭመንት ከተማዋን ተቆጣጠረ።
ማዶቤም ወደ ኪስማዮ ተመልሶ አስተዳዳሪ ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጁባላንድ መመሥረት
ራስ ገዟን የጁባ ላንድ ግዛት ለመመሥረት ረዘም ያለ ጊዜ ወስዷል።
በ2013 የራስ ካምቦኒ አባላትን ጨምሮ በርካታ ጎሳዎች የተሳተፉበት ሥልጣን የመጋራት ድርድር አካሄዱ።
በወቅቱ መሪ በነበሩት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼክ አህመድ እና በማዶቤ መካከል ግጭት ሲፈጠር ኢትዮጵያ የማደራደሩን ዋነኛ ሚና ተረከበች።
በኢጋድ ጥላ ስር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የተሳተፉበት ሞቃዲሾ እና ጁባላንድ ተደራደሩ።
የአዲስ አበባ ስምምነት ተብሎ የሚጠራው ቀጣናዊ ጅማሮም ተሳካ።
የጁባላንድ ጉባኤን ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ኬንያ የሚደግፉት ማዶቤ የራስ ገዟ ጁባላንድ ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ።
የጁባላንድ መንግሥት ምሥረታ ላይ አምባሳደር ወንድሙ ተሳትፈዋል።
በዚህም ጁባላንድ እንደ ራስ ገዝ ሆና የወጣችበት እና ማዶቤም ለአስራ ሁለት ዓመታት አካባቢውን እንዲመራ ያስቻለ ሁኔታ ተፈጠረ።
ኮሎኔል ገብረ እግዚአብሔር እንዲሁም አምባሳደር ወንድሙ ማዶቤ የተለያዩ ጎሳዎችን በማሳተፍ በእርቅ እና በመሳተፍ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካን ይመራል ይሉታል።
ግጭት በማያጣው አካባቢ ለ12 ዓመታት በሥልጣን መቆየት "በአጋጣሚ የሚመጣ" እንዳልሆነም ነው አምባሳደሩ የሚያስረዱት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ማዶቤ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ በኢትዮጵያ እና በማዶቤ መካከል የግንኙነት መሻከር ታይቷል።
ሥልጣን በፌደራሉ/በማዕከላዊ መንግሥት እንዲከማች የሚፈልጉት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ወይም በቅጽል ስማቸው ፎርማጆ እና ማዶቤ ውጥረት የተሞላ ግንኙነት ነበራቸው።
በዚህም ፕሬዚዳንት ፋርማጆ ከፊል የራስ ገዝ ክልሎችንም በማዕከላዊ መንግሥት ቁጥጥር ስር ለማድረግ ተንቀሳቅሰዋል።
በተለያዩ ግዛቶች አጋሮችን መሾም ቢችሉም በጁባላንድ ይህንን ማሳካት አልቻሉም።
የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥትን መጠናከር በደገፈ መልኩ የተንቀሳቀሰው የዐቢይ አስተዳደር ለፋርማጆ ድጋፉን መስጠት ጀመረ።
ኢትዮጵያ ለሌሎች ግዛቶች፣ የጎሳ ሚሊሻዎች እና የፖለቲካ እና የፀጥታ ተዋናዮች ትሰጠው የነበረውን ድጋፍ ቀለበሰች።
የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግሥት መጠናከር ከመደገፍ በተጨማሪም ማዶቤ የዐቢይ ተቀናቃኝ ከሆነው ህወሓት (ኢህአዴግ) ጋር ጥሩ ግንኙነት መኖሩንም አስተዳደራቸው የድጋፍ ሚዛኑን ወደ ፋርማጆ እንዲያጋድል ማድረጉን፤ 'ኢንዲንግ ዘ ዴንጀረስ ስታንድ ኦፍ ኢን ሳውዘርን ሶማሊያ' የሚለው ከአምስት ዓመት በፊት የወጣው የክራይሲስ ግሩፕ ጽሁፍ ያስረዳል።
ኢትዮጵያ በአንዳንድ የክልል ግዛቶች ጦሯን ማሰማራቷን ተከትሎ ፋርማጆ አጀንዳውን ለማስፈጸም የአዲስ አበባን ድጋፍ እየተጠቀመ ነው ተብሎ ተከሰሰ።
ከእነዚህም መካከል የሳውዝ ዌስተርን ተቃዋሚ ዕጩ የሆኑት ሙክታር ሮቦው እስር አንዱ ነው። በተጨማሪም የሶማሊያን ማዕከላዊ መንግሥትን የማጠናከር ማዕቀፍ አድርጎ በተያዘው በጌዶ እና ዶሎው- ባይዶዋ መስመር የኢትዮጵያ ጦር እንቅስቃሴ መጨመሩንም ክራይሲስ ግሩፕ በሪፖርቱ አካቷል።
ማዶቤን ለማሰር ያልተሳኩ ሙከራዎችም እንደነበሩ ተጠቅሷል።
ጁባላንድ ምርጫ በምታደርግበት በአውሮፓውያኑ 2019 የኢትዮጵያን ጦር የያዘ አውሮፕላን በኪስማዮ አየር ማረፊያ ለማረፍ ቢሞክርም በጁባላንድ እና በኬንያ ወታደሮች መከልከሉን የክራይሲስ ግሩፕ ጽሁፍ ያስረዳል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን እና ማዶቤን ልታስማማ እንደሞከረች አንዳንድ ዘግባዎች አመልክተዋል።
ማስታወሻ፦ በጽሑፉ ላይ የተጠቀሱት ሁሉም የዘመን አቆጣጠሮች በአውሮፓውያኑ ነው።












