ሶማሊያ፣አሜሪካ በብቸኝነት የምትቆጣጠራቸው ወደቦችን እና የጦር ሰፈሮችን እሰጣለሁ አለች

የሶማሊያው ፕሬዚዳን ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍሪካ ቀንድ አገሯ ሶማሊያ አሜሪካ በብቸኝነት የምትቆጣጠራቸው ስልታዊ ወደቦችን እና የጦር ሰፈሮችን ለመስጠት ሃሳብ ማቅረቧን ሮይተርስ ዘገበ።

የሶማሊያው ፕሬዚዳን ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለአሜሪካ አቻቸው ዶናልድ ትራምፕ በጻፉት እና ሮይተርስ መመልከቱን በገለጸበት ደብዳቤ ላይ ነው አሜሪካ በብቸኝት ልትቆጣጠራቸው የሚችሉ የጦር ሰፈሮች እና ወደቦች አማራጮች የቀረቡት።

ጉዳዩን በሚያውቁ የቀጣናው ዲፕሎማት ትክክለኛነቱ መረጋገጡን የዜና ወኪሉ የገለጸው ደብዳቤ የተጻፈው መጋቢት 7/ 2017 ዓ. ም. ነው።

እንደ ሮይተርስ ዘገባ ከሆነ ፕሬዚዳንቱ አሜሪካ በብቸኝነት እንድትቆጣጠራቸው ያቀረቡላቸው ባሊዶግሉ እና በርበራን በጦር ሰፈርነት እንዲሁም የበርበራ እና ቦሳሶ ወደቦችን ነው።

አሜሪካ በሶማሊያ እና በቀጣናው የሚገኙ ጽንፈኛ ታጣቂዎችን ስጋት ለመመከት በአፍሪካ ቀንድ ጠንካራ ወታደራዊ ይዞታን ያስገኝላታል ተብሏል።

"እነዚህ ስልታዊ ይዞታዎች አሜሪካ በቀጣናው የምታደርገውን ተሳትፎ የማጠናከር እድል ይሰጣሉ። የማይቋረጥ ወታደራዊ እና ሎጂስቲክ መዳረሻዎችን [ለአሜሪካ] በማረጋገጥ ሌሎች የውጭ ተወዳዳሪዎች በዚህ ወሳኝ ኮሪደር ውስጥ እንዳይገኙ ይከላከላሉ" ሲል ደብዳቤውን ዋቢ አድርጎ ሮይተርስ አስነብቧል።

ባሊዶግል ከዋና ከተማይቱ ሞቃዲሾ በስተሰሜን ምዕራብ በ90 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ የቦሳሶ ወደብ ከፊል ራስ ገዝ በሆነችው ፑንትላንድ ትገኛለች።

ሶማሊያ ለአሜሪካ በብቸኝነት እንደ ጦር ሰፈር እንድትጠቀምበት እና በወደብነት እንድትቆጣጠር ካቀረበችው ውስጥ የበርበራ ወደብ አንዱ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በርበራ ራሷን በነጻ አገርነት ባወጀችው ሶማሊላንድ የሚገኝ ሲሆን፤ የሶማሊያ እርምጃ ሁኔታውን ወደ ግጭት ሊያመራ ሊያደርገው እንደሚችል ይጠበቃል።

ይህንን የበርበራ ወደብን አስመልክቶ ሮይተርስ ጥያቄ ያቀረበላቸው የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዲራህም ዳሂር አደን "የምን ትብብር ነው? አሜሪካ ይህንን ሶማሊያ የተባለ የተበላሸ አገዛዝን ተስፋ ቆርጣበታለች። አሜሪካ ለዓለም ሰላማዊ፣ የተረጋጋና ዲሞክራሲ የሰፈነባት አገር መሆኗን ካሳየችው ሶማሊላንድ ጋር ለመደራደር ዝግጁ ናት" የሚል ምላሽ ሰጥተተዋል።

"አሜሪካ ደደብ አይደለችም። በርበራ ወደብን በተመለከተ ከማን ጋር መነጋገር እንዳለባቸው ያውቃሉ" ሲሉ አክለዋል።

በባይደን አስተዳደር ወቅት የዩኤስኤ አፍሪካ ኮማንድ (አፍሪካ) አዛዥን ጨምሮ ከፍተኛ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የበርበራ ወደብን ጎብኝተዋል።

በኋላ ላይ ለአሜሪካ የጠፈር መንኮራኩሮች ድንገተኛ ማረፊያ ተብሎ መለየቱም ተነግሯል።

ከሦስት ዓመታት በፊት የአሜሪካ የመከላከያ 'አውቶራይዜሽን አክት' ተብሎ የሚጠራው የፀጥታ ትብብርን በማጎልበት ለጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መንገድ ይከፍታል በሚል ሶማሊላንድ እንድትካተት ተሻሸሏል።

ሶማሊላንድን እንደ አንድ የግዛቷ አካል አድርጋ የምታየው ሶማሊያ ከሶማሊላንድ ጋር የሚደረግ ስምምነትንም ሆነ እውቅናን እንደማትቀበለው በተደጋጋሚ ትናገራለች።

ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጣናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ መሆኑ ይታወሳል።

በምላሹም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ ዕውቅና ለመስጠት እንዲሁም ከልማት ተቋማቷ ድርሻ ይኖራታል የሚል ነው።

ሶማሊያ እና ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ያቋረጠ ቁርሾ ውስጥ ከገቡ በኋላ በቱርክ አደራዳሪነት ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

በቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶዋን አደራዳሪነት ታኅሣሥ 2/2017 ዓ.ም. የተደረሰው የአንካራ ስምምነት ለአንድ ዓመት ያህል በቃላት ጦርነት ሲወዛገቡ የነበሩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ልዩነታቸውን በድርድር ጠረጴዛ ለመፍታት እንዲቀመጡ ያደረገ ነው።

ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ ጋር በተደረሰው የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት ለመጀመሪያ ጊዜ ዕውቅና አገኛለሁ የሚል ተስፋ ነበራት። ሆኖም በዚህ የመግባባቢያ ስምምነት ቁርሾ ውስጥ የገቡት ኢትዮጵያና ሶማሊያ ልዩነታቸውን ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ተከትሎ የመግባቢያ ስምምነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ከሶማሊያ ባለሥልጣናት በኩል ይህ የመግባቢያ ስምምነት እንደተሻረ ቢናገሩም ኢትዮጵያ በይፋ ያለችው ነገር የለም።

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ሶማሊላንድ በአሜሪካ ዕውቅና ልታገኝ ነው የሚለው መነጋገሪያ ሆኗል።

ኃያላን እና ተደማጭነት ያላቸው ሪፐብሊካኖች የሶማሊላንድን ዕውቅና የማግኘት ፍላጎት በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ አጀንዳ አድርገውታል።

ከጥቂት ወራት በፊት የአሜሪካ የምክር ቤት አባል ስኮት ፔሪ አሜሪካ ለሶማሊላንድ መደበኛ እውቅና እንድትሰጥ ረቂቅ ሕግ አቅርበዋል።

ይህ ረቂቅ በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 2023 ሁለተኛውን የትራምፕ የፕሬዚዳንትነት የሥልጣን ዘመንን በማስመልከት የወጣውን ፍኖተ ካርታ የተከተለ ነው።

'ፕሮጀክት 2025' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፍኖተ ካርታ በቀኝ አክራሪው ሄሪቴጅ ፋውንዴሽን በተሰኘው እና ከ100 በላይ ወግ አጥባቂ ድርጅቶች የተነደፈ ነው።

ሰነዱ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ሁለት አገራትን ብቻ ይጠቅሳል፣ ሶማሊላንድ እና ጂቡቲን። "አሜሪካ በጂቡቲ ያላትን ተጽእኖ ማሽቆልቆል ለመቋቋም ሶማሊላንድን እንደ አገርነት ዕውቅና መስጠት" የሚል ነው።

በትራምፕ የቀድሞ አስተዳደር ወቅት በአፍሪካ ጉዳዮች የቀድሞ ረዳት ፀሐፊ እና በኢትዮጵያ በአምባሳደርነት ያገለገሉት ቲቦር ናዥ እና የአፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ፒተር ፋም የሶማሊላንድን ነጻነት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያቀነቅኑ ናቸው።

በአሁኑ ወቅት ሶማሊያ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ያለው ግንኙነት ስላሳሰባት አንድ ወትዋች (ሎቢ) ቡድን ቀጥራለች። ሶማሊያ በዋሺንግተን መቀመጫውን ላደረገው ቢጂአር ለተሰኘው የሎቢ ድርጅት 600 ሺህ ዶላር ለመክፈል ተስማምታለች።