የመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሐመድ ወደ ሶማሊያ መጓዛቸው ተገለጸ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, EHPR

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሐመድ ወደ ሶማሊያ ማቅናታቸው ተገለጸ።

ሮይተርስ የዜና ወኪል የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዓሊ ኦማርን ጠቅሶ እንደዘገበው ሚኒስትሯ ሞጋዲሾ ገብተዋል።

ሚኒስትሯ በምን ጉዳይ ዙርያ ውይይት እንደሚያደርጉ እንዳልተገለጸና በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል እስካሁንም ምንም እንዳልተባለም ዘገባው አትቷል።

ሚኒስትሯ ወደ ሶማሊያ ያቀኑት ሁለቱ አገራት የሻከረ ግንኙነታቸውን ለማደስ እየሞከሩ ባለበት ወቅት ነው።

ብሉምበርግ ባወጣው ዘገባ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታን ጠቅሶ፣ ሚኒስትሯ ወደ ሶማሊያ ያቀኑት የኢትዮጵያ ወታደሮች በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ስለሚኖራቸው ተሳትፎ ውይይት ለማድረግ ነው ብሏል።

ሚኒስትር ዴዔታው "በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ውዝግብ በአንካራ ስምምነት መፈታቱን ተከትሎ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን በአውሶም ለማካተት እያሰበች ነው" ማለታቸውንም ዘገባው አክሏል።

ሶማሊያ የኢትዮጵያን ወታደሮች በአውሶም ውስጥ ላለማካተት አስተላልፋ የነበረውን ውሳኔ ለመቀልበስ ማሰቧንም የብሉምበርግ ዘገባ ያትታል።

የሶማሊያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ፊቂ "በሶማሊያና በኢትዮጵያ መካከል ያለው አለመግባባት ተፈትቷል" ማለታቸውን ቢቢሲ ሶማሊ አስነብቧል።

የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) የሚተካው የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) ውስጥ የኢትዮጵያን ወታደሮች ማካተት እንደማትሻ ሶማሊያ የጠቆመች ሲሆን፣ ሁለቱ አገራት የሻከረ ግንኙነታቸውን በአንካራ ስምምንት ካደሱ በኋላ ውጥረቱ የረገበ ይመስላል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አትሚስን ለሚተካው አውሶም ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል።

የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ወደ ግዛቱ እንድታስገባ ከጠየቀበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 17 ዓመታት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሚገኘው የሰላም አስከባሪ ኃይል ኢትዮጵያ ሠራዊቷን አሰማርታ ትገኛለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኢትዮጵያ በአትሚስ ስር 3 ሺህ ገደማ ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።

ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ስምምነት መፈራረሟን ተከትሎ ግን ሶማሊያ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከግዛቷ እንዲወጡ መጠየቋ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ አለመኖር ከአል-ሸባብ ጋር የሚደረገው ትግል ላይ ከፍተኛ ክፍተት ሊፈጥር እንደሚችል ስጋቶች ሲስተጋቡ ቆይተዋል።

ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን አስከትሏል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ከስምምነቱ በኋላ በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ ዓሊ ኦማር የሚመራ የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ ከባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርጎ ተመልሷል።

ውይይቱ እየተካሄደ ሳለ ሶማሊያ የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበር አልፈው የሶማሊያ ወታደሮች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ማለቷ ሌላ ውጥረት አስነስቷል። ኢትዮጵይ ለክስተቱ "ሶስተኛ ወገን" ተጠያቂ አድርጋ ይህንን ክስ አስተባብላለች።

ለዓመታት በሶማሊያ ውስጥ ሰላም ሲያስከብር የቆየው የኢትዮጵያ ሠራዊት ከግዛቱ እንዲወጣ እንደሚፈልግ የሶማሊያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ መቆየቱ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያውፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ ፊርማቸውን ባኖሩበት የአንካራ ስምምነት መሰረት፤ "ሶማሊያ በአፍሪካ ሕብረት ተልዕኮ ስር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።"

ከዚህ በተጨማሪ ስምምነቱ "የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ" ሲል ያትታል።

የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (አውሶም) የተባለው ሰላም አስከባሪ ኃይል በአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት መባቻ ሥራውን ይጀምራል።

በአሁኑ ወቅት በሶማሊያ የተሰማራው አትሚስ የሰላም አስከባሪ ኃይል ከኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ጂቡቲ ወታደሮች የተውጣጣ ነው። የሰላም አስከባሪው ኃይል አል-ሸባብ የተባለው ታጣቂ ቡድን የሚያደርሳቸውን ጥቃቶች ሲመክት ቆይቷል።

ለቀጣዩ ተልዕኮ አውሶም የሚሰማሩ ወታደሮች ከየትኛው አገር እንደሚሆኑ የመምረጥ ኃላፊነቱ የሶማሊያ ሲሆን ኢትዮጵያ በዚህ ተልዕኮ ወታደሮቿን ታሳትፋለች የሚለው እስካሁን አልታወቀም።

ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድቡ ምክንያት ለዓመታት ውዝግብ ውስጥ ያለችው ግብፅ በአዲሱ የሰላም አስከባሪ ኃይል (አውሶም) ውስጥ ሠራዊቷን እንደምታሰማራ የግብፁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ከዓመት በላይ ውጥረት ውስጥ ሳሉ ግብፅ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያ የሶስትዮሽ ስምምነት መድረሳቸው አይዘነጋም።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንትም ከሦስት ጊዜ በላይ ወደ ኤርትራ መዲና አስመራ ተመላልሰዋል።