ኢትዮጵያ ወታደሮቿ የሶማሊያ ጦር ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል መባሉን አስተባበለች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ኃይሎች በሶማሊያ ጦር ላይ ጥቃት አድርሰዋል ሲል ያቀረበውን ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት አስተባበለ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማክሰኞ ታኅሣሥ 15/2017 ዓ. ም. ባወጣው መግለጫ፣ "የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሶማሊያዋ ከተማ ዱሎው ለተፈጠረ ክስተት የኢትዮጵያ ወታደሮችን መክሰሱ ኢትዮጵያን አሳስቧታል" ብሏል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ዱሎው በተባለችው የጁባላንድ ከተማ "የኢትዮጵያ ኃይሎች ጥቃት ፈጽመዋል" ሲል ከሷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በምላሹ "የተስተካከለውን የሶማሊያና የኢትዮጵያ ግንኙነት ማወክ በሚፈልጉ ኃይሎች የተፈጠረ ክስተት ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት "ሦስተኛ ወገን" ያላቸው አካላት "የአፍሪካን ቀንድ ለመናጥ ቆርጠው የተነሱ የቀጣናው ሰላም አደፍራሾች" ናቸው ሲል ገልጿል።
መግለጫው "ሦስተኛ ወገን" ያላቸውን አካላት በስም አልጠቀሰም።
የሶማሊያ መንግሥት "ሰኞ ጠዋት 4፡00 አካባቢ የኢትዮጵያ ኃይሎች ዱሎው በሚገኘው የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር መቀመጫ ላይ ያለምንም ትንኮሳ ያልተጠበቀ ጥቃት ፈጽመዋል" ሲል ከሷል።
"ይህ የታቀደበት እና ሆነ ተብሎ የተፈጸመ ጥቃት ሦስት ቁፍል የሶማሊያ ጦር፣ የብሔራዊ ደኅንነት ኤጀንሲ እና የሶማሊያ ፖሊስ ኃይል መቀመጫዎች ላይ የተፈፀመ ነው" ሲልም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ኃይሎች ፈጸሙት የተባለው ጥቃት "የአንካራ ስምምነት እንዲሁም የሁለቱን አገራት ጎረቤታዊ ግንኙነት የሚጥስ ነው" ሲልም ወቅሷል።
የሶማሊያ መንግሥት መሰል ጥቃቶችን "በዝምታ እንደማይመለከት፤ ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነቱን እንደሚያስከብር" ገልጿል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ በለቀቀው መግለጫ "የቀጣናው ሰላም አደፍራሾች" ያላቸው አካላት "ሁለቱ አገራት በአንካራ ስምምነት አማካይነት ለሰላም ያሳዩትን ቁርጠኛነት እንዲያደናቅፉ ሊፈቀድላቸው አይገባም" ብሏል።
በሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዓሊ ኦማር የሚመራ የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ሰኞ ወደ አዲስ አበባ ማቅናቱ ከተገለጸ ከሰዓታት በኋላ ነበር የሶማሊያ መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደሮች ጥቃት ሰንዝረዋል ሲል የከሰሰው።
የሶማሊያ መንግሥት "በአንካራ ስምምነት መሠረት የሰላም ሂደቱን ለማጠናከር እየጣረ ባለበት እና ከፍተኛ ልዑክ ወደ አዲስ አበባ በላከበት ወቅት ነው ይህ ጥቃት የተፈጸመው" ብሏል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ልዑካኑ ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት "በአንካራ ስምምነት የተገባውን ቃል ለማጠናከር" ነው ብሎ ነበር።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና እና የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ታኅሣሥ 2/2017 ዓ. ም. በቱርክ፣ አንካራ ስምምነት ፈርመዋል።
የሶማሊያን ክስ በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት በሰጠው ምላሽ "የኢትዮጵያ መንግሥት ተመሳሳይ ክስተቶች እንዳይፈጠሩ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ቁልፍ አካላት ጋር አብሮ መሥራት ይቀጥላል" ብሏል።
የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ወታደሮች "ጥቃት የሶማሊያ ኃይሎች ላይ ሞት እና ቁስለት ደርሷል እንዲሁም በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል" ቢልም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን በወታደሮቹ ጥቃት እንዳልተፈጸመ አስታውቋል።
"በአንካራ ስምምነት መሠረት የሁለቱን አገራት ወንድማዊ ግንኙነት ለማጠናከር ኢትዮጵያ ቁርጠኛ ናት" ሲልም መግለጫው አትቷል።
"የሁለቱ አገራት ቆራጥነትና ጽናት የሁለትዮሽ ግንኙነቱንና ቀጣናዊ ትብብሩን አጠንክሮ ይቀጥላል" ሲልም አክሏል።
ክስተቱን አስመልክቶ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የጁባላንድ ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርጎ "በሥፍራው የሚገኙት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጣልቃ የገቡት ባለሥልጣናትን ለመጠበቅ ነበር" ብሏል።
የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት እና ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው ጁባላንድ ባለፉት ሳምንታት ግጭት ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል።
ኤኤፍፒ፤ የጁባላንድ ደኅንነት ሚኒስትር ዩሱፍ ሑሴን ኦስማን በዱሎው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "ክስተቱ የተፈጠረው (የፌዴራል) ኃይሎች የጁባላንድ ግዛት ልዑካንን የጫነች አውሮፕላን መትተው እንዲጥሉ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተከትሎ ነው" ማለታቸውን አስነብቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ዓሊ ሞሐመድ ኦማር ጋር መወያየታቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ከሶማሊያው አቻቸው አብዱላሂ ሞሐመድ ጋር መወያየታቸውን በማኅበራዊ ሚድያቸው ገልጸዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ ዓሊ ሞሐመድ ኦማር ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ሁለቱ አገራት አንዳቸው የሌላቸውን "ሉዓላዊነት፣ ነጻነትና የግዛት አንድነት በማክበር በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሠሩ" መነጋገራቸውን የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒቴር በኤክስ ገጹ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ዓሊ ሞሐመድ ኦማር የኢትዮጵያ ወታደሮች በሶማሊያ ጦር ላይ "ጥቃት ማድረሳቸውን መኮነናቸውን" መግለጫው ጠቅሶ፣ አቶ ምስጋኑ በበኩላቸው፣ "መንግሥታቸው ስለ ክስተቱ በአፋጣኝ ምርመራ ለማድረግና ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር ተባብሮ ለመሥራት ያለውን ቁርጠኛነት" መግለጻቸው ተጠቅሷል።
ውይይቱ ሰላምና ደኅንነትን በቀጣናው ማስጠበቅን፣ ሽብርተኛነት መዋጋትን፣ የሁለትዮሽ ግንኙነትን ማጠናከርን እና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ልዩነት የፈታውን የአንካራ ስምምነት ሙሉ ትግበራን የተመለከተ መሆኑም ተግቧል።












