የአንካራ ስምምነትን ለማጠናከር የሶማሊያ ልዑካን ቡድን ወደ አዲስ አበባ ማቅናቱ ተገለጸ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ
የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን እና ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ

በሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዓሊ ኦማር የሚመራ የልዑካን ቡድን ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ ታኅሣሥ 14/ 2017 ዓ. ም. ወደ አዲስ አበባ ማቅናቱ ተገለጸ።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ፣ ልዑካኑ ወደ አዲስ አበባ ያቀኑት "በአንካራ ስምምነት የተገባውን ቃል ለማጠናከር" ነው።

"በአንካራ በሁለቱም አገራት መሪዎች አማካይነት የተደረሰውን ስምምነት መሠረት በማድረግ ጉብኝቱ ሶማሊያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ቁርጠኛነት ያጠናክራል" ይላል መግለጫው።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርኩ ፕሬዝዳንት አቀራራቢነት አንካራ ላይ በተደረገ ውይይት ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይብ ኤርዶዋን ስምምነቱን "ታሪካዊ" በማለት በሁለቱ አገራት መካከል "ሰላም እና ትብብር ለማምጣት የመጀመሪያ እርምጃ" እንደሚሆን ተስፋቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ከሁለት ቀናት በፊት የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማክሮን በኢትዮጵያ የአንድ ቀን ይፋዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅትም፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር በውይይት እና ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ የባሕር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት እንደሚደግፉ መናገራቸው አይዘነጋም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና እና የሶማሊያው ፕሬዝደንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ታኅሣሥ 2/2017 ዓ. ም. በቱርክ፣ አንካራ ስምምነት መፈረማቸው ይታወሳል።

የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ "የልዑካን ቡድኑ ጉብኝት፣ በመከባበርና በጋራ ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ትብብር የሚጎለብትባቸውን ዕድሎች" ትኩረቱ ያደርጋል ብሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት በሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ላይ ተመርኩዞ ከአጎራባች አገራት ጋር ያለውን ትስስር ለማጠናከር ቁርጠኛ ነው" ሲልም አክሏል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ አንካራ ላይ ተገኝተው ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው ከስምምነት ላይ መድረሳቸው የተገለጸው።

የአገራቱ መሪዎች ከስምምነት ላይ ከደረሱ በኋላ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ስምምነቱ ለወደብ አልባዋ ኢትዮጵያ የባሕር መተላላፊ በር እንድታገኝ የሚያደርግ ነው ማለታቸው ይታወሳል።

በስምምነቱ መሠረት ሁለቱ አገራት ኢትዮጵያ "በሶማሊያ ሉዓላዊ ሥልጣን ሥር አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ዘላቂ የባሕር መተላለፊያ" እንድታገኝ የሚያስችል የንግድ እና የሁለትዮሽ ስምምነት በማድረግ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቅርበት እንደሚሠሩ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በውይይቱ አማካይነት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት መቻሉን አመልከተዋል።

"የኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ የማግኘት ፍላጎት ጎረቤቶቻችንን ጭምር የሚጠቅም ሰላማዊ ጥረት ነው። ይህ ፍላጎት በትብብር መንፈስ እንጂ በጥርጣሬ ሊታይ አይገባውም" ሲሉ የአገራቸውን ፍላጎት ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም "ገንቢ ውይይት" ኢትዮጵያ እና ሶማሊያን "በትብብር፣ በወዳጅነት እና በጠላትነት ሳይሆን በጋራ ለመሥራት ከሚኖር ፈቃደኝነት ጋር ወደ ቀጣዩ ዓመት ያሸጋግራል" ብለዋል።

ከሁለቱ አገራት አልፎ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ላይ ውጥረትን አንግሶ የቆየው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ውዝግብ የተቀሰቀሰው ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ከፈረመች በኋላ ነበር።

የአንካራው ስምምነት ነጥቦች

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በቱርክ ፕሬዝዳንት አማካይነት ውዝግቡ ከጀመረ ለመጀመሪያ ጊዜ አንካራ ላይ ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ከስምምነት የደረሱባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮች የሚያመለክት 'የአንካራ ውሳኔ' የሚል ሰነድ ይፋ መደረጉ ይታወሳል

ይህ በቱርክ መንግሥት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት በኩል የወጣው የአንካራ ስምነት ሰነድ በዋናነት በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል አወዛጋቢ የሆነውን የባሕር መተላላፊያ የማግኘት ጉዳይን ያነሳል።

በተጨማሪም ሶማሊያ ከመጪው ጥር ወር በኋላ ከግዛቷ እንዲወጣ የምትፈልገውን በአፍሪካ ሕብረት ስር የተሰማራውን የኢትዮጵያ ሠራዊትን በሚመለከትም ከዚህ በፊት የተሠረጨውን የሶማሊያን ወቀሳ የሚያነሳ ነጥብም ተካቶበታል።

የአንካራ ስምምነት ዋነኛ ነጥቦች

  • የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች አንዳቸው የሌላኛቸውን ሉዓላዊነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት እና በአፍሪካ ኅብረት ደንቦች ላይ የሰፈሩ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ለማክበር ተስማምተዋል።
  • በወዳጅነት የመከባበር መንፈስ ያለፉ ልዩነቶችን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደኋላ በመተው በትብብር ለጋራ ብልጽግና ወደፊት ለመሥራት ተስማምተዋል።
  • ሶማሊያ በአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ሥር ሆነው በአገሯ የተሰማሩትን የኢትዮጵያ ወታደሮች መስዋዕትነት ዕውቅና ትሰጣለች።
  • የሶማሊያን የግዛት አንድነት ባከበረ ሁኔታ ኢትዮጵያ አስተማማኝ የባሕር መተላላፊያ ማግኘቷ የሚኖረውን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ሁለቱ አገራት ዕውቅና ይሰጣሉ።
  • ሁለቱ አገራት በቱርክ አመቻችነት በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ የቴክኒካዊ ጉዳዮች ድርድር ማድረግ የሚጀምሩ ሲሆን፣ ይህም በአራት ወራት ውስጥ የሚቋጭ ይሆናል።
  • በሉዓላዊ የሶማሊያ መንግሥት ሥር ኢትዮጵያ አስተማማኝ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ዘላቂ የባሕር መተላላፊ እንድታገኝ የሚያስችል ለሁለቱም አገራት ጠቃሚ የሆኑ የኮንትራት፣ የኪራይ፣ እና ተመሳሳይ የንግድ አሠራር መንገዶችን በጋር በመሆን ለማጠናቀቅ ተስማምተዋል።
  • ሁለቱ አገራት የቱርክን ድጋፍ በመቀበል በስምምነቱ አተረጓጎም እና አተገባበር ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ ልዩነቶችን በቱርክ አማካይነት በንግግር እና በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ተስማምተዋል።