በዩኬ ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገ 42 ሺህ ጥገኝነት ጠያቂዎች ይግባኝ እየጠበቁ ነው

በጀልባ የሚጓዙ ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዩናይትድ ኪንግደም ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረጉ 42 ሺህ የሚሆኑ ጥገኝነት ጠያቂዎች ይግባኝ ለመጠየቅ እየተጠባባቁ መሆኑ ተገለጸ።

አኃዙ በሁለት ዓመታት ውስጥ በአምስት በእጥፋ ማደጉን ያሳወቀው የስደተኞች ካውንስል መንግሥት የጥገኝነት ጥያቄ ቀውስን ከአንደኛው ተቋም ወደሌላ እያዛወረ ነው ሲል ተችቷል። 40 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች በጥገኝነት መጠየቂያ ሆቴሎች ውስጥ እንደሚኖሩ ተገልጿል።

የአገር ውስጥ ቢሮ በበኩሉ የመጀመሪያ ውሳኔ የሚያገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር በእጥፍ መጨመሩን እና ለፍርድ ቤት ሂደቶችም ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ መድቤያለሁ ብሏል።

መንግሥት የጥገኝነት ሆቴሎችን በጊዜ ሂደት ለማስቆም እና አላግባብ የሆኑ እነዚህን ወጪዎች ለመቀነስ ቁርጠኛ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

በቀደመው የወግ አጥባቂ መንግሥት አስተዳደር ፖሊሲዎች ምከንያት የበርካታ ጥገኝነት ጥያቄዎች ውድቅ እየተደረገ መሆኑን የስደተኞች ካውንስል አስታውቋል።

መንግሥት 'ናሺናሊቲ ኤንድ ቦርደርስ' የተሰኘውን ህግ ማውጣቱን ተከትሎ ከአስሩ አፍጋኒስታውያን ጥገኝነት ጠያቂዎች መካከል አራቱ ብቻ ናቸው ተቀባይነት ያገኙት። ከዚህ ቀደም ጥገኝነት የጠየቁ አፍጋኒስታውያን በሙሉ ተቀባይነት ያገኙ ነበር።

ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረጉት በሙሉ ውሳኔውን ይግባኝ እንደሚሉ ይጠበቃል።

በአሁኑ ወቅት ጥገኝነት ጠያቂዎችን በሚያስተናግዱ ሆቴሎች ውስጥ እንዲሁም በባለፉት ሁለት ዓመታት በጀልባ ወደ ዩኬ የገቡት ከፍተኛውን ቁጥር የያዙት ከአፍጋኒስታን የመጡ ናቸው።

የስደተኞች ምክር ቤት ካውንስል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤንቨር ሶሎሞን የተሻለ እና ፍትሃዊ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በጎ አድራጎት ድርጅቱ ይግባኝ እየተጠባበቁ ያሉትም አሁንም ማረፊያ እንደሚያስፈልጋቸው ጠቁሞ ይህ እስካልተሻሻለ ድረስ ዋጋውን እስከ 1.5 ቢሊዮን ፓውንድ ሊያደርሰው እንደሚችል አስጠንቅቋል።

የመንግሥት ቃል አቀባይ በበኩላቸው "ከዚህ ቀደም ከነበረው አስተዳደር የተቀበልነው የጥገኝነት ጠያቂዎች ስርዓት ተስማሚ አልነበረም። ለዚያም ነው የጥገኝነት ጥያቄን ሂደትን እንደገና ለማስጀመር እንዲሁም ተከማችተው የነበሩ ጉዳዮችን ለማቃለል አፋጣኝ እርምጃ እየወሰድን ነው። ይህም ግብር ከፋዩን ከ4 ቢሊዮን ዶላር ፓውንድ በላይ የሚገመት ገንዘብ በቀጣዩ ሁለት ዓመታት ያድነለታል" ብለዋል።

የፍትህ ሚኒስቴር አኃዛዊ መረጃ እንደሚያሳየው በአውሮፓውያኑ 2024 ላይ 41 ሺህ 987 ጥገኝነት ጠያቂዎች በፍርድ ቤት መዝገብ ውስጥ ተካተው እንዳሉ እና ይህ ቁጥር በአውሮፓውያኑ 2023 7 ሺህ 173 እንደነበር ተጠቅሷል።

የስደተኞች ካውንስል በበኩሉ ባለፈው ዓመት የነበረው የጥገኝነት ማመልከቻ ይግባኞች ከ2023ቱ 71 በመቶ ጭማሬ ማሳየታቸውን ነው።