"የሰላም ስምምነቱ ዩክሬን የኔቶ አባል ከመሆን የሚያግድ መሆን አለበት"- ሩሲያ

የዩክሬን ውድመት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሩሲያ በሰላም ስምምነቱ፣ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል እንዳትሆን የምትታገድበትን ዋስትና እንደምትጠይቅ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገለጹ።

በተጨማሪም ከማንኛውም የሰላም ስምምነት እንድትገለል ሩሲያ እንደምትፈልግ ሚኒስትሩ አክለዋል።

"ጠንካራ የደህንነት ዋስትናዎች የዚህ ስምምነት አካል እንዲሆኑ እንጠይቃለን" ሲሉ አሌክሳንደር ግሩሽኮ ለሩሲያው የዜና ወኪል ኢዝቨስቲያ ተናግረዋል።

"ዩክሬን ገለልተኛ የምትሆንበት እንዲሁም የኔቶ አገራት የአባልነት ጥያቄዋን ውድቅ ማድረግ የእነዚህ ዋስትናዎች አካል ሊሆኑ ይገባል" ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ለሶስት ዓመታት የዘለቀውን የዩክሬንን ጦርነት ሰላማዊ እልባት ለመስጠት ውይይቶች የቀጠሉ ሲሆን፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዲሁም የሩሲያ አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን በመጪዎቹ ቀናት ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

አሜሪካ እና ዩክሬን ለሩሲያ የ30 ቀናት የተኩስ አቁም ሃሳብ ለማቅረብ ስምምነት ላይ ደርሰዋል።

ፕሬዚዳንት ፑቲን የተኩስ አቁሙን ቢደግፉም ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ከበድ ያለ ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።

ከመወዛገቢያዎቹ መካከል የሩሲያው ምዕራባዊ ኩርስክ ግዛት ነው። የዩክሬን ጦር ባለፈው ነሐሴ ወረራ ፈጽሞ የተወሰኑ ስፍራዎችን መቆጣጠር ችሏል። ፑቲን የኩርስክ ግዛትን አገራቸው ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥራለች ያሉ ሲሆን በስፍራው ያሉ የዩክሬን ወታደሮችም "ተቆርጠዋል" ብለዋል።

በተጨማሪም የተኩስ አቁም ስምምነቱ በምስራቅ የጦር ግንባር ሊኖረው የሚችለው ቁጥጥር እና ክትትል ላይ በርካታ ጥያቄዎችን አንስተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ፑቲን አፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች "ለማበላሸት" እየጣሩ ነው ሲሉ ከሰዋል።

ሞስኮ ውስጥ ከፑቲን ጋር የተገናኙት የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮቭ ትራምፕ እና ፑቲን በዚህ ሳምንት በስልክ እንደሚያወሩ ይጠበቃል ሲሉ ለሲኤንኤን ተናግረዋል።

ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ስልጣን በተረከቡባት ዕለት ጦርነቱን አቆመዋለሁ ሲሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ተስምተዋል።

ትራምፕ ጦርነቱን ለማስቆምና ድርድር ለመጀመር ከፑቲን ጋር 90 ደቂቃ የፈጀ የስልክ ውይይት አድርገዋል።

ልዩ መልዕክተኛው ሩሲያ በኃይል የያዘቻው የዩክሬን ግዛቶች በስምምነቱ ምን አይነት እልባት ሊሰጣቸው እንደሚችል የቀረበላቸውን ጥያቄ ከመመለስ ተቆጥበዋል። ሩሲያ በአሁኑ ወቅት አንድ አምስተኛውን የዪክሬንን ግዛት ተቆጣጥራ ትገኛለች።