ፕሬዝዳንት ትራምፕ የአሜሪካ ድምፅን ለመዝጋት ጫፍ ላይ ደረሱ

የቪኦኤ አርማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካን ድምፅ (ቪኦኤ) የፌደራል በጀት የሚያነሳ ትዕዛዝ በመፈረም ጣቢያውን "ፀራ ትራምፕ" እና "አክራሪ" በሚል ከሰዋል።

በእግዱ ላይ መግለጫ ያወጣው ዋይት ሀውስ ትዕዛዙ "ከዚህ በኋላ ግብር ከፋዮች ለአክራሪ ፕሮፓጋንዳ ወጪ እንዳያወጡ ያደርጋል" በማለት የቀኝ ዘመም ፖለቲከኞችን እና የጣቢያው ተቺዎችን ድጋፍ አባሪ አድርጓል።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የናዚን ፕሮፓጋንዳ ለመቀልበስ የተቋቋመው ቪኦኤ አሁንም ድረስ ዋነኛ የሬዲዮ አገልግሎት ጣቢያ ነው።

ጣቢያው በመላው ዓለም በመቶ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ አድማጮች ተደራሽ እንደሆነ ይናገራል።

የቪኦኤ ዳይሬክተር ማይክ አብራሞዊትዝ እርሳቸው እና አንድ ሺህ 300 ሠራተኞች አስተዳደራዊ የሥራ እረፍት እንዲወጡ መደረጉን አስታውቀዋል።

ዳይሬክተሩ ትዕዛዙ ቪኦኤ በተለይም የአሜሪካ ተቃዋሚዎች ኢራን፣ ቻይና እና ሩሲያ ቢሊዮን ዶላሮችን መድበው ዋሽንግተንን እምነት ለማሳጣት ሀሰተኛ ትርክቶችን በሚፈጥሩበት በአሁኑ ጊዜ ወሳኝ የሆነውን ተልዕኮውን እንዳይወጣ ያደርጋል ብለዋል።

የአሜሪካ ጋዜጠኞች ወኪል የሆነው ብሔራዊ የፕሬስ ክለብ ትዕዛዙ "የአሜሪካን የረጅም ጊዜ ነፃ እና ገለልተኛ ፕሬስ የመመስረት ቁርጠኝነት የሚቀለብስ ነው" ብሏል።

"በአንድ ጀምበር የዜና ክፍል ገሸሽ የሚደረግ ከሆነ ፕሬስ ነፃነት ስላለበት ሁኔታ ምን ይነግረናል?" ሲል አክሏል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ሙሉ አንድ ተቋም ቀስ በቀስ እየፈረሰ ነው። ይህ የሠራተኞች ጉዳይ ብቻ አይደለም። በቪኦኤ የገለልተኛ ጋዜጠኝነት እጣ ፈንታን አደጋ ላይ የሚጥል መሰረታዊ እርምጃ ነው" ብሏል።

የፕሬዝዳንቱ ትዕዛዝ የቪኦኤ እናት ኩባንያ በሆነው የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ኤጀንሲ ላይ ያነጣጠረ ሲሆን፤ ኤጄንሲው ለትርፍ ያልተቋቋሙ እና ኮሚኒዝምን ለመከላከል የተመሰረቱ የሬዲዮ ጣቢያዎችንም በገንዘብ ይደግፋል።

ትዕዛዙ የሥራ ኃላፊዎች አፈፃፀማቸውን እንዲቀንሱ፤ በሕግ የሚጠየቁትን አገልግሎት እና እንቅስቃሴያቸውን እንዲገድቡ ይጠይቃል።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ የቪኦኤ ሠራተኞች በሰው ኃይል ኃላፊዎች በኩል በኢሜል ውሳኔውን እንዲያውቁ መደረጋቸውን ዘግቧል።

የትርፍ ሰዓት ሠራኞች እና ዓለም አቀፍ የኮንትራት ሠራተኞች ደሞዝ ለመክፈል ገንዘብ የለም መባላቸውን ምንጮች ለሲቢኤስ ተናግረዋል።

ሲቢኤስ የደረሱት የኢሜል መልዕክቶች የገንዘብ ድጋፍ ይደረግላቸው የነበሩ በእስያ እና አውሮፓ የሚገኙ የሬዲዮ ጣቢያዎች የፌደራል ድጋፉ እንደተቋረጠ የሚያሳውቁ ናቸው።

ቪኦኤ እና በእናት ኩባንያው የሚደገፉ ጣቢያዎች 400 ሚሊዮን አድማጮችን እንደሚያገለግሉ ይናገራሉ። ጣቢያዎቹ በብሪታኒያ መንግሥት በከፊል ገንዘብ ከሚያገኘው የቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት ያህል ግዙፍ ተደራሽነት አላቸው።

ቢሊየነሩ እና የትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ ኢለን መስክ የአሜሪካ መንግሥት ወጪዎችን ለመቀነስ እየሰሩ ሲሆን፤ ንብረታቸው በሆነው ኤክስ ማኅበራዊ የትስስር ገፅ ቪኦኤ እንዲዘጋ ጥሪ ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለቤተ መፅሐፍት እና ሙዚየሞች የገንዘብ ድጋፍ የሚያቀርቡትን ጨምሮ የበርካታ የፌደራል ኤጄንሲዎችን በጀት አቋርጠዋል።