ደቡብ አፍሪካ የአሜሪካን 'ማንአለብኝነት' እንዳትቀበል ተቃዋሚዎቿ ተናገሩ

ከአሜሪካ የተባረሩት የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢብራሒም ራሱል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከአሜሪካ የተባረሩት የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢብራሒም ራሱል

አሜሪካ በአገሯ የሚገኙትን የደቡብ አፍሪካውን አምባሳደር በ72 ሰዓታት እንዲወጡ ማዘዟን ተከትሎ፤ ደቡብ አፍሪካ ይህንን "ማን አለብኝነት" እንዳትቀበል የአገሪቷ ተቃዋሚዎች ጠየቁ።

በዋሽንግተን መቀመጫቸውን አድርገው የነበሩት የደቡብ አፍሪካ አምባሳደር ኢብራሒም ራሱል ከአሜሪካ ተባረዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ "አሜሪካን የሚጠላ ዘር ላይ የሚያተኩር ፖለቲከኛ" ብለው ከፈረጇቸው በኋላ፤ በአገሪቱ ተቀባይነት የላቸውም ሲሉ ከአገር እንዲወጡ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ትራምፕ ስልጣን መረከባቸውን ተከትሎ በአሜሪካ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተሞላበት ሆኗል።

ይሁን እንጂ የደቡብ አፍሪካ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስትር ሮናልድ ላሞላ "በትዊተር ዲፕሎማሲ ላይ መሳተፉ ጠቃሚ አይደለም፤ ሁለቱ አገራት ፊት ለፊት ሊነጋገሩ ይገባል" ሲሉ ለመንግሥታዊው የዜና ወኪል ኤስኤቢሲ ተናግረዋል።

በሰላ ትችታቸው የሚታወቁት እና በደቡብ አፍሪካ ኢ-ፍትሃዊነትን ለመቀልበስ የሚሰራው ፓርቲ ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ መሪ ጁሊየስ ማሌማ፤ "አገሪቱ ዋይት ሃውስን በተቆጣጠረው ብርቱካናማ ቂል እንድትሸማቀቅ እንዳይፈቅዱ" ሲሉ ለአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የፓን አፍሪካኒስት ኮንግረስ ዋና ጸሐፊ አፓ ፑዎ የአሜሪካን ውሳዘኔ አውግዘው፤ በደቡብ አፍሪካ ሉዓላዊነት ላይ የተፈጸመ ጥቃት እንዲሁም በአገሪቱ ፖሊሲ ላይ የአዛዥነት ሚና ለመጫወት የሚደረግ ሙከራ ብለውታል።

"ደቡብ አፍሪካ የአሜሪካ አሻንጉሊት አይደለችም፤ ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት አገራችንን የማስተዳደር መብት አለን" ብለዋል።

ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ያጸደቀችው የመሬት ፖሊሲ በተወሰኑ "ማኅበሰረሰቦች" ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ለአገሪቱ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ አቋርጠዋል።

ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታድ ስርዓት ከ30 ዓመታት ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬቶች አነስተኛ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ ነው ተብሏል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአንዳንድ ሁኔታዎች ያለ ካሳ መሬት መውረስ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ እንዲሆን ፈርመዋል።

የደቡብ አፍሪካ መንግሥት በመሬት ባለቤትነት ላይ የሚታየው ታሪካዊ ኢፍትሃዊነት እና ዘረኝነት እንዲስተካከል ጥሪዎች እየቀረቡለት ይገኛሉ።

አምባሳደር ኢብራሒም፣ ባራክ ኦባማ በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ከአውሮፓውያኑ 2010-2015 ባለው ጊዜ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።

አምባሳደሩ ከዚህ ቀደም ባላቸው ልምድ እንዲሁም ከዋሽንግተን ጋር ባላቸው ሰፋ ያለ ግንኙነት ድጋሚ በአውሮፓውያኑ 2024 አምባሳደር እንዲሆኑ ተሾመዋል።

ምንም እንኳን አምባሳደሩ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ቢኖራቸውም ከትራምፕ ጋር ፊት ለፊት መገናኘት ተስኗቸዋል።

አምባሳደሩ "ለፍልስጤም የመደገፍ ፖለቲካዊ ታሪክ" ያላቸው ከመሆናቸው አንጻር አሁን ባለው የአሜሪካ አስተዳደር ሊጣጣሙ እንደማይችሉ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የደቡብ አፍሪካ ዲፕሎማት ሴማፎር ለተሰኘ የዜና ወኪል ተናግረዋል።