በዩኬ ከኢትዮጵያዊው ስደተኛ ወሲባዊ ትንኮሳ ክስ ጋር ተያይዞ የጥገኛ ጠያቂዎች ሆቴል እንዲዘጋ የተሰጠው ብያኔ ተቀለበሰ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
በዩናይትድ ኪንግደም፣ ኢሴክስ ግዛት ኤፒንግ ከተማ የ14 ዓመት ታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎች በማድረስ ከተከሰሰው ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ጋር ተያይዞ የጥገኛ ጠያቂዎች ሆቴል በፍርድ ቤት እንዲዘጋ የተወሰነው ብያኔ በመንግሥት አቤቱታ ተቀለበሰ።
ታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎች ማድረስን ጨምሮ አምስት ክሶች የቀረቡበት ኢትዮጵያዊው ስደተኛ ሀዱሽ ገብረ ሥላሴ ቅባቱ ጋር ተያይዞ በተነሳ ተቃውሞ ያረፈበት ዘ ቤል የተሰኘው የጥገኛ ጠያቂዎች ሆቴል በጊዜያዊነት እንዲዘጋ ተወስኖ ነበር።
የዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥገኝነት ጠያቂዎቹ ከሆቴሉ ወጥተው ወደ ሌላ ሥፍራ እንዲዛወሩ እንዲሁም ሆቴሉ እንዲዘጋ በጊዜያዊነት ብያኔ ያስተላለፈው ባለፈው ሳምንት ነበር።
የስደተኞችን ጉዳይ በበላይነት የሚያየው መሥሪያ ቤት 'ሆም ኦፊስ' እንዲሁም የሆቴሉ ባለቤት አቤቱታ ማስገባታቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የጣለው እግድ ተነስቷል።
በኤፒንግ ከተማ የሚገኘው የቤል ሆቴል ጠበቆች እና መንግሥት 138 ጥገኝነት ጠያቂዎች እስከ መስከረም 2/ 2018 ዓ.ም ባለው ጊዜ ሆቴሉን ለቀው እንዲወጡ የተወሰነውን የከፍተኛ ፍርድ ቤት ብያኔ ተቃውመው አቤቱታ ለፍርድ ቤት አስገብተዋል።
ውሳኔውን የሻሩት የይግባኝ ፍርድ ቤት ዳኛ ቢን የከፍተኛው ፍርድ ቤት ብያኔ "በጣም የተሳሳተ መርህ ላይ የተመሰረተ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
ዳኛው በዚህ ብያኔያቸው ጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ሌላ ሥፍራ ከማዘዋወር ጋር ተያይዞ የሚመጡ ችግሮችን ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከግምት ውስጥ ማስገባት አልቻለም ብለዋል።
የጥገኝነት ጠያቂዎቹ ሆቴል ቢዘጋ መንግሥት በሌላ ሥፍራ ሌላ ጣቢያ ማቋቋም እንዳለበት ፍርድ ቤቱ በሰጠው ብያኔ የዘነጋ እንደሆነም ተገልጿል።
የይግባኝ ፍርድ ቤት ይህንን ውሳኔ የቀለበሰው በጊዜያዊነት ሲሆን ሆቴሉ በቋሚነት መዘጋት አለበት ወይ በሚለው ላይ የከፍተኛው ፍርድ ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት ወር ቀጠሮ ተይዟል።
ጥገኛ ጠያቂዎቹ በሆቴሉ መቆየት ይችላሉ የሚለውን ውሳኔ ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ሦስት ግለሰቦች ለእስር ተዳርገዋል።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ውሳኔውን አስመልክቶ የዩናይትድ ኪንግደም የወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ኬሚ ባዴኖዎች " የሕገወጥ ስደተኞች መብት ከብሪታንያ ሕዝብ መብት በላይ ያስቀደመ ነው" ሲሉ ትችታቸውን አቅርበዋል።
ፍርዱን የተቃወሙ ወደ 100 የሚጠጉ ተቃዋሚዎች ከሆቴሉ ውጭ ተሰባስበው የነበረ ሲሆን በፖሊስ ከሥፍራው እንዲወገዱ ተደርገዋል።
የቢቢሲ ጋዜጠኛ አንድ ጥገኝነት ጠያቂ በተቃዋሚዎች ሲዘለፍ ተመልክቷል።
ተቃውሞውን ወደ ሁከት በመቀየር የተጠረጠሩ ሦስት ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የኢሴክስ ፖሊስ ተናግሯል።
ተቃውሞዎች በቼስትነት እና ሄርትፎርድሻየር የሚገኙ የጥገኝነት ጠያቂዎች ሆቴሎች መዛመታቸው ተገልጿል።
ሀዱሽ በ14 ዓመት ታዳጊ ልጆች ላይ ወሲባዊ ትንኮሳዎች፣ ህጻንን ለወሲባዊ ድርጊት ማነሳሳት፣ ወሲባዊ ጥቃት የሚሉትን ጨምሮ አምስት ክሶች ተመስርተውበታል።
ሀዱሽ በኮልቸስተር ከተማ ፍርድ ቤት ረቡዕ፣ ነሐሴ 21/2017 ዓ.ም. በሰጠው ቃል የቀረቡበት ክሶች "ሁሉ የፈጠራ እንደሆኑ እና ምንም ስህተት እንዳልሰራ" ራሱን ተከላክሎ ምላሽ ሰጥቷል።
ከሰሞኑ በዋለው ችሎት ሀዱሽ በከተማዋ ማዕከል ተቀምጠው የነበሩትን ሁለት የ14 ዓመት ታዳጊዎች ከእነሱ "ልጅ መውለድ እንደሚፈልግ" መናገሩ እና ወዳረፈበት ዘ ቤል ሆቴል እንደጋበዛቸው ፍርድ ቤቱ ሰምቷል። ሊስማቸውም እንደሞከረም ተገልጿል።
ሀዱሽ ወደ ዩናይትድ ኪንግደም መደበኛ ባልሆነ መንገድ የገባው ሰኔ 22/2017 ዓ.ም. ሲሆን፣ በቁጥጥር ሥር የዋለውም ከስምንት ቀናት በኋላ ሐምሌ 1 ነበር።
ግለሰቡ የጥገኝነት ጠያቂዎች በሚኖሩበት ቤል ሆቴል ውስጥ ነዋሪ ነበር።
ትንኮሳዎቹንም አደረሰ የተባለው የትምህርት ቤት ጓደኞች ተሰባስበው ተቀምጠውበት በነበረው የኤፒንግ የከተማ ማዕከል ነው።
ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተከትሎ በዚህ ሳምንት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በቤል ሆቴል አቅራቢያ ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ አሰምተዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ዘረኝነትን የሚቃወሙ የድጋፍ ሰልፎች ተደርገዋል።
ከተቃውሞው ጋር ተያይዞ በተነሳው ሁከት 16 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።
ፍርድ ቤቱ በሀዱሽ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ለነሐሴ 29/ 2017 ዓ.ም ሰጥቷል።















