የዩኬ ፖሊስ በሕግ የታገደውን 'ፓሊስታይን አክሽን' ደግፈው ሰልፍ የወጡ ከ425 በላይ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ለፍልስጤማውያን መብት የሚታገለው 'ፓሊስታይን አክሽን' የተባለውን ቡድን መታገዱን በመቃወም በለንደን አደባባይ የወጡ ከ425 በላይ ሰዎች ታሰሩ።
በማዕከላዊ ለንደን በሚገኘው የፓርላማ አደባባይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የቡድኑን መታገድ በመቃወም የተሰበሰቡ ሲሆን አንዳንዶቹም "የዘር ማጥፋት ወንጀልን እቃወማለሁ፣ፓሊስታይን አክሽንን እደግፋለሁ" የሚል መፈክር ይዘው ታይተዋል።
የሜትሮፖሊታን ፖሊስ አብዛኞቹ የታሰሩት እገዳ የተጣለበት ድርጅትን በመደገፋቸው ነው ብሏል።
ከ25 በላይ ሰዎች በፖሊስ አባላት ላይ በፈጸሙት ጥቃት እና በሕዝብ ፀጥታን በማደፍረስ ወንጀሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።
መንግሥት በሐምሌ ወር ፓሊስታይን አክሽን የተሰኘውን ድርጅት የሽብር ሕጉን በመጥቀስ አግዶታል።
በዚህ ሕግ መሠረት የቡድኑ አባል መሆን ወይም መደገፍ እስከ 14 ዓመት እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል ነው።
የከተማዋ ፖሊስ የፀጥታ ኃይሎች "ከፍ ያለ ጥቃት ደርሶባቸዋል" በማለት "ከቃል ስድብ በተጨማሪ ቡጢ፣ካልቾ፣ መተፋት እንዲሁም እቃዎች ተወርውረውባቸዋል" በማለት የደረሰባቸውን ጥቃቶች ዘርዝሯል።
አክሎም "የፖሊስ አባላቱ ተግባራቸውን እንዳይወጡ የተቀናጀ ጥረት ሲደረግ ነበር" ያለ ሲሆን የፖሊስ መኮንን ላይ ጥቃት የፈፀመ ማንኛውም ሰው "ሕግ በሚፈቅደው መጠን ይጠየቃል" ብሏል።
የድጋፍ ሰልፉን ያዘጋጀው 'ዲፌንድ አወር ጁሪስ' የተሰኘው ድርጅት "ፖሊስ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በማሰብ አዛውንቶችን ጨምሮ መፈክር የያዙ ሰላማዊ ሠልፈኞች ላይ የኃይል ጥቃት ፈጽሟል" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
አንድ የፖሊስ አባል አዛውንት ሠልፈኛን መሬት ላይ ሲወረውር የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስልም አጋርቷል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ቀደም ሲል እንደተናገሩት "ይህን አስነዋሪ እገዳ የሚቃወሙ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ ነው" ብለዋል።
ሰላማዊ ሰልፉ የፓሊስታይን አክሽንን እገዳ "ለማስፈፀም የማይቻል እና ከንቱ የሀብት ብክነት" መሆኑን ያሳያል ሲሉ አክለዋል።
የከተማዋ ፖሊስ የተቃውሞ ሠልፈኞቹ የተጠቀሙት ዘዴ "የፍትህ ስርዓቱን ማጨናነቅ ... ከሌላ አካባቢ የፖሊስ ኃይል እንዲመጣ ማድረግ ሲሆን ይህም በሌሎች የለንደን ነዋሪዎች ላይ ጫና የፈጠረ ነው" ብሏል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሠልፈኞች፣አብዛኞቹ ጡረተኞች የሆኑ፣ የፓሊስታይን አክሽንን የሚደግፉ መፈክሮችን እና መልዕክቶችን የያዙ ወረቀቶችን በመያዝ አደባባይ ወጥተው ታይተዋል።
በተመሳሳይ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሠልፈኞቹን በመደገፍ ዙሪያቸው በመቆም ሲመለከቷቸው ነበር ተብሏል።
እነዚህ ግን የተከለከለውን ቡድን እንደሚደግፉ የሚጠቁሙ መፈክሮችን አልያዙም።
ሠልፈኞቹ ከተሰባሰቡ ከ15 ደቂቃ በኋላ ፖሊሶች መፈክር የያዙ ተቃዋሚዎችን በመለየት በቁጥጥር ስር ማዋል ጀምሯል።
የከተማዋ ፖሊስ ቀደም ሲል ለቡድኑ ድጋፍ የሚያሳዩ ሰዎች እንደሚታሰሩ አስጠንቅቋል።
ብዙ ተቃዋሚዎች የሠልፉ አዘጋጆቹ ወደ አደባባዮቹ ለሚሄዱ የሰጡትን ምክር በመከተል በግልጽ የሚታይ መፈክር ከመያዝ ተቆጥበዋል።
ፖሊስ ተቃዋሚ ሠልፈኞቹን በቁጥጥር ስር ባዋለበት ወቅት "ማፈሪያ ናችሁ" የሚል ዘለፋ የገጠማቸው ሲሆን ሌሎች አስፀያፉ ቃላትም የተጠቀሙ ተቃዋሚዎች ነበሩ።
ተቃዋሚ ሠልፈኞቹ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በሚውሉበት ወቅት ስማቸውን እና አድራሻቸውን ከመግለጽ እንዲቆጠቡ የተነገራቸው ቢሆንም ምን ያህሉ ይህንን እንደተከተሉ ማወቅ አይቻልም።
ሠልፈኞቹ ስም እና አድራሻቸውን ካልተነገሩ በዋስ ከመለቀቅ ይልቅ ወደ እስር ቤት እንዲወሰዱ ይደረጋሉ።
ፖሊስ ሠልፈኞቹን በቁጥጥር ስር እያዋለ ባለበት ወቅት፣ "የዘር ማጥፋትን ትደግፋላችሁ" የሚል ድምጾች በተደጋጋሚ በዙሪያው ከተሰበሰቡ ሰዎች ተሰምቷል።
በተቃዋሚ ሠልፈኞቹ እና በፖሊስ መካከል ያለው ውጥረት እየተካረረ ሲመጣ ተጨማሪ የፖሊስ ባልደረባዎች ወደ ስፍራው እንዲመጡ ተደርጓል።
የሠልፉ አዘጋጆች ቅዳሜ ዕለት ለተቃውሞ የወጣው ሰው ቁጥር 1500 እንደሚደርስ ገምተዋል።















