የለንደን ፖሊስ የታገደውን የፍልስጤም ድርጅት ደግፈው ሰልፍ የወጡ 474 ሰዎችን አሰረ

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የለንደን ፖሊስ የታገደውን 'ፓላስታይን አክሽን' የተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት በመደገፍ ሰልፍ የወጡ 474 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ።
የከተማዋ ፖሊስ 466 ሰልፈኞች ድርጅቱን በመደገፍ፣ አምስት ሰልፈኞች የፖሊስ መኮንኖች ላይ ጥቃት በማድረስ፣ሁለት ሰዎች ደግሞ ሕዝባዊ ስርዓት በመጣስ እንዲሁም አንድ ግለሰብ ደግሞ ዘርን መሠረት ያደረገ ጥሰት በመፈፀም በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።
'ዲፌንድ አወር ጁሪስ" በተባለ ቡድን የተዘጋጀው የድጋፍ ሰልፍ ዌስትሚኒስተር ፓርላማ አደባባይ አካባቢ በርካታ ሰዎች በእጅ የተፃፉ መፈክሮች በመያዝ "የዘር ጭፍጨፋን እቃወማለሁ። ፓሊስታይን አክሽንን እደግፋለሁ" በሚል ድምፃቸውን አሰምተዋል።
የእንግሊዝ መንግሥት ባለፈው ሐምሌ በፀረ ሽብር ሕጉ የድርጅቱ አባል መሆን ወይም መደገፍ እስከ 14 ዓመት እስር የሚያስቀጣ ወንጀል ካደረገው በኋላ የታየ ትልቁ ተቃውሞ ነው።
ክፉኛ የተጎዱ የፖሊስ መኮንኖች የሌሉ ሲሆን ባለፉት 10 ዓመታት ውስጥ ፖሊስ በአንድ ቀን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰልፈኞች አስሯል።
የአገር ውስጥ ሚኒስትር ይቬት ኩፐር ፖሊስ ለሰጠው ምላሽ ምስጋናቸውን ሲያቀርቡ፤ የመብት ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል የጅምላ እስሩን "እጅግ አሳሳቢ" ብሎታል።
በአደባባዩ አካባቢ የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የፖሊስ መኮንኖች አብዛኞቹ ቁጭ ብለው የነበሩ ሰልፈኞችን ይዘዋቸው ከመሄዳቸው በፊት ሲያነጋገሩ አሳይተዋል።
ግላዊ መረጃዎቻቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑ አሊያም ማንነታቸው መለየት ያልተቻሉ ሰልፈኞች ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲወሰዱ ተደርጓል።
አብዛኞቹ ሰልፈኞች ሁነቱን ለመዘገብ በአካባቢው የተገኙ መገናኛ ብዙኸንን ለማነጋገር ፍላጎት ያላሳዩ ሲሆን፤ አንድ ስሙን መግለፅ ያልፈለገ ሰልፈኛ ለቢቢሲ "የፍልስጤም አክሽንን ካገዱ ሌላ ቀጣዩ ድርጅት ማነው? ምንም ነገር መቃወም እስካልተከለከልን ድረስ፤ ይህ የዲሞክራሲ ተቃራኒ ነው" ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ27 ዓመቷ ክላውዲያ ፔና-ሮሃስ "መታሰር የሚፈልግ ሰው ያለ አይመስለኝም። ነገር ግን አሁን ላይ በፍልስጤም ሰዎች ላይ እየሆነ ያለው ነገር የበለጠ ያሳስበኛል። እናም ተመልካች ለመሆን ፈቃደኛ አይደለሁም" ብላለች።
የ86 ዓመት ጃኮብ ኢክልስተን በበኩላቸው "ሀሳብን በነፃነት በመግለፅ አምናለሁ። መንግሥት ለማድረግ እየሞከረ ያለው ትልቅ አምባገነንነት ነው። እናም ይህ በጣም አደገኛ ነው" ብለዋል።
ቀደም ብሎ ተቃውሞው ሲጀመር ፖሊስ በፓርላማው አካባቢ ከ500 እስከ 600 የሚሆኑ ሰዎች እንደታደሙ ገልፆ፤ አብዛኞቹ ተመልካቾች፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና የፍልስጤም አክሽንን ለመደገፍ መፈክር ያላነገቡ ሰዎች ናቸው ብሏል።
አደባባዩ አካባቢ ተቀምጠው የነበሩ ሰዎች መፈክሮቻቸውን ማውጣታቸውን ተከትሎ ወደ ተሰባሰበው ሕዝብ ሲያቀኑ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋል ጀምሯል።
የተቃውሞ ሰልፉ የተደረገው በእንግሊዝ እና ዌልስ ቡድኑን በመደገፍ የተከሰሱ ሦስት ሰዎች ስም ዝርዝር ይፋ በሆነ በቀናት ውስጥ ነው።
ፍልስጤም አክሽን ከባድ ጥቃቶችን በመፈፀም ጠንካራ የደኅንነት ምክር ከቀረበበት በኋላ መታገዱን ይቫን ኩፐር ገልፀዋል።
"በርካታ ሰዎች ስለዚህ ቡድን እውነተኛ መልክ ላያውቁ ይችላሉ። ነገር ግን ግምገማዎች በጣም ግልፅ ናቸው። ይህ ቡድን ሰላማዊ ድርጅት አይደለም። የዩናይትድ ኪንግደም እና የሕዝቡ ደኅንነት ሁሌም ቢሆን ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ ሊሆን ይገባል" ብለዋል።















