ሐማስ የመንግሥት ደሞዝ ለመክፈል የሚጠቀምበት ሚስጥራዊ መንገድ

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሐማስ ከእስራኤል ጋር ለሁለት ዓመታት ያህል ጦርነት ካካሄደ በኋላ ወታደራዊ አቅሙ በጣም ሲዳከም፣ የፖለቲካ አመራሩም በከፍተኛ ጫና ውስጥ ወድቋል።
ሆኖም በጦርነቱ ጊዜ ሁሉ ሐማስ ለ30,000 የመንግሥት ሠራተኞች ሚስጥራዊ በሆነ መንገድ ደሞዝ ከፍሏል።
ክፍያው ጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሰረተ ስርዓትን በመጠቀም የተፈጸመ ሲሆን እስካሁን በአጠቃላይ 7 ሚሊዮን ዶላር ያህል መክፈል ችሏል።
ቢቢሲ ባለፈው ሳምንት እያንዳንዳቸው 300 ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማግኘታቸውን ያረጋገጡ ሦስት የመንግሥት ሠራተኞችን አነጋግሯል።
እነዚህ ግለሰቦች በየ10 ሳምንቱ ከጦርነቱ በፊት ከሚያገኙት ደሞዝ ውስጥ 20 በመቶ ያህሉን ብቻ መቀበላቸውን ከቀጠሉት በአስር ሺዎች ከሚቆጠሩ ሠራተኞች መካከል እንደሆኑ ይታመናል።
የዋጋ ግሽበቱ በፍጥነት እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ ከጠቅላላው የገንዘብ መጠን በጣም ያነሰ የሆነው ክፍያ በታማኝ የፓርቲ አባላት ላይ ቅሬታ እየፈጠረ ነው።
በጋዛ ከባድ የዕለት ምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ቀጥሏል።
የእርዳታ ኤጀንሲዎች ለእጥረቱ በእስራኤል የተጣለውን እገዳ ተጠያቂ ያደርጋሉ።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ አንድ ኪሎ ግራም ዱቄት ከመቼውም ጊዜ ከፍ ባለ ዋጋ እስከ 80 ዶላር ተሽጧል።
በጋዛ ውስጥ ምንም የሚሰራ የባንክ ሥርዓት ስለሌለ ደሞዝን መቀበል ውስብስብ እና አንዳንድ ጊዜም አደገኛ ነው።
እስራኤል የቡድኑን የአስተዳደር አቅም ለማደናቀፍ በመፈለግ የሐማስ ደሞዝ አከፋፋዮችን በየጊዜው እየለየች ዒላማ ታደርጋለች።
የሐማስ ሠራተኞች፣ ከፖሊስ አባላት እስከ ታክስ ኃላፊዎች ብዙ ጊዜ ምስጢራዊ መልዕክት በራሳቸው ወይም በትዳር አጋራቸው ስልክ ይደርሳቸዋል።
በዚህ መልዕክት ላይም ወደ አንድ የተለየ ቦታ በተቀመጠላቸው ሰዓት ውስጥ እንዲሄዱ እና "ጓደኛህን ለሻይ አግኘው" የሚል መመሪያ ይቀመጣል።
በዚህ የመገናኛ ስፍራ ሠራተኛውን አንድ ወንድ ወይንም አልፎ አልፎ ሴት አግኝቶት ያለምንም ተጨማሪ ንግግር ገንዘቡን የያዘውን የታሸገ ፖስታ በሚስጥር አስረክቦት ይሰወራል።
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የሐማስ የሃይማኖት ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ ደሞዙን በመቀበል ወቅት ያለውን አደጋ አብራርተዋል።
"ደሞዜን ለመውሰድ በሄድኩ ቁጥር ባለቤቴን እና ልጆቼን እሰናበታለሁ። እንደማልመለስ አውቃለሁ" ብለዋል።
"በተለያዩ አጋጣሚዎች የደመወዝ ማከፋፈያ ቦታዎች ላይ እስራኤል ጥቃት አድርሳለች። እኔም በጋዛ ከተማ በተጨናነቀ ገበያ ላይ ካነጣጠረ ጥቃት ተርፌያለሁ።"
ማንነቱን ለመደበቅ ሲል አላ በሚል ስም መጠራት የመረጠው ሌላ ግለሰብ ደግሞ ስድስት የቤተሰብ አባላት እንዳሉት ገልጾ፣ በሐማስ በሚመራው መንግሥት በመምህርነት መቀጠሩን ተናግሯል።
"1000 ሸክል (300 ዶላር ገደማ) ያረጁ የብር ኖቶች ተቀብያለሁ። እነዚያን ገንዘቦች የትኛውም ነጋዴ አይቀበላቸውም። 200 ሸክል ብቻ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፤ የተቀረውን በእውነቱ ምን እንደማደርግበት አላውቅም" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
"ከሁለት ወር ተኩል ረሃብ በኋላ ዋጋ የሌለው ገንዘብ ይከፍሉናል።ልጆቼን ለመመገብ የተወሰነ ዱቄት ለማግኘት ተስፋ በማድረግ ብዙ ጊዜ ወደ እርዳታ ማከፋፈያ ቦታዎች ለመሄድ እገደዳለሁ። አንዳንድ ጊዜ ተሳክቶልኝ ትንሽ ማምጣት እችላለሁ፤ ነገር ግን ብዙ ጊዜ አይሳካልኝም።"
በመጋቢት ወር የእስራኤል ወታደራዊ ኃይል በካን ዮኒስ በሚገኘው ናስር ሆስፒታል ላይ በፈጸመው ጥቃት የሐማስ የፋይናንስ ኃላፊን ኢስማኢል ባርሆምን መግደሉን ተናግሯል።
ግለሰቡን ገንዘብ ለሐማስ ወታደራዊ ክንፍ በማስተላለፍ ይወነጅሉታል።
ሐማስ አብዛኛው የአስተዳደር እና የፋይናንስ መሠረተ ልማቶቹን ወድመው የደመወዝ ክፍያውን እንዴት መቀጠል እንደቻለ ግልፅ አይደለም።
በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ያገለገሉ እና የሐማስ የፋይናንስ ስራዎችን ጠንቅቀው የሚያውቁ አንድ የሐማስ ነባር ሠራተኛ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ቡድኑ መስከረም 26 2015 ዓ.ም. በደቡብ እስራኤል ካደረሰው አስከፊ ጥቃት በፊት ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሸቅል በዋሻዎች ውስጥ በድብቅ አከማችቷል ።
ይህም በሐማስ መሪ ያህያ ሲንዋር እና ወንድሙ መሀመድ በቀጥታ ቁጥጥር እና ክትትል ይደረግበት ነበር።
ሁለቱም በእስራኤል ጦር መገደላቸው ተገልጿል።
ለሐማስ ደጋፊዎች የተሰጠው እርዳታ እና የቀሰቀሰው ቁጣ
ሐማስ የፋይናንስ ምንጩ የተመሰረተው በጋዛ ሕዝብ ላይ በጣለው ከባድ የገቢ ቀረጥ እና ታክስ እንዲሁም ከኳታር በሚያገኘው በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ነው።
በተለየ የፋይናንስ ስርዓት የሚንቀሳቀሰው የሐማስ ወታደራዊ ክንፍ፣ የቃሳም ብርጌድ፣ በዋናነት ወጪውን የሚሸፈነው ከኢራን በሚያገኘው ድጋፍ ነው።
በግብፅ የታገደው እና በዓለም ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ከሆኑ እስላማዊ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የሙስሊም ወንድማማቾች ከፍተኛ ባለስልጣን ከበጀታቸው 10 በመቶ የሚሆነው ለሐማስ ፈሰስ መደረጉን ተናግረዋል።
በጦርነቱ ወቅት ገቢን ለማግኘት ሐማስ በነጋዴዎች ላይ ቀረጥ መጣሉን የቀጠለ ሲሆን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው ሲጋራን ከመደበኛ መሸጫ ዋጋው እስከ 100 እጥፍ በተጋነነ ዋጋ በመሸጥ ላይ ይገኛል።
ከጦርነቱ በፊት አንድ 20 ሲጋራዎችን የሚይዝ ፓኬት 5 ዶላር ያወጣ የነበረ ሲሆን አሁን ከ 170 ዶላር በላይ ይሸጣል።
ከጥሬ ገንዘብ ክፍያ በተጨማሪ ሐማስ ለአባላቱ እና ቤተሰቦቻቸው በአካባቢ የአደጋ ጊዜ ኮሚቴዎች አማካኝነት የምግብ እሽጎችን ያከፋፍላል።
የእነዚህ ኮሚቴዎች መሪዎች በእስራኤል ተደጋጋሚ ጥቃቶች የተነሳ ቦታቸውን ለመቀያየር ተገድደዋል።
ይህ ደግሞ በጋዛ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ሐማስ እርዳታውን ለደጋፊዎቹ ብቻ እንደሚያከፋፍል እና ሰፊውን ሕዝብ አግልሏል በሚል ሕዝባዊ ቁጣ እንዲባባስ አድርጓል።
እስራኤል በጥር ወር በተደረሰው የተኩስ አቁም ወቅት ወደ ጋዛ የገባውን እርዳታ በመስረቅ ሐማስን የከሰሰች ቢሆንም ቡድኑ ግን ውንጀላውን አስተባብሏል።
ይሁን እንጂ በዚህ ወቅት ከፍተኛ መጠን ያለው እርዳታ በሐማስ መወሰዱን የቢቢሲ ምንጮች ተናግረዋል።
ከአምስት ዓመት በፊት ባለቤቷ በካንሰር የሞተባት እና ሦስት ልጆቿን ብቻዋን የምታሳድገው ኒስሪን ካሌድ ለቢቢሲ ስትናገር "ረሃቡ እየባሰ ሲሄድ ልጆቼ የሚያለቅሱት በረሃቡ ብቻ ሳይሆን ከሐማስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ጎረቤቶቻችን የምግብ እሽግ እና ዱቄት ሲረከቡ በማየታቸው ነበር።
" የስቃያችን ምክንያት እነርሱ አይደሉምን? የመስከረም 26 ጀብዳቸውን ከመጀመራቸው በፊት ለምን ምግብ፣ ውሃ እና መድሃኒት በበቂ እንዲኖረን አላደረጉም?" ስትል ትጠይቃለች።















