ጭንቅላት እና ደረታቸውን ተመትተው ስለተገደሉ የጋዛ ሕፃናት ግድያ ምርመራ

ሻህድ (በስተቀኝ) እህቷ ላያን (በስተግራ)

የፎቶው ባለመብት, Al-Majdalawi family

የምስሉ መግለጫ, ሻህድ (በስተቀኝ) እህቷ ላያን (በስተግራ)

*ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ጽሑፍ የሕፃናት ሞት ዝርዝር እና የጉዳት ምሥሎች በመያዙ አንዳንድ አንባቢዎችን ሊረብሽ ይችላል።

በጋዛ ከተማ በሚገኝ መንገድ ላይ አንድ ሕፃን በፊቷ ተደፍታ ወድቃ ምንም እንቅስቃሴ አታሳይም። እግሮቿ ታጥፈው እንቅልፍ የወሰዳት በሚመስል ሁኔታ ጭንቅላቷ ወደ አንድ ጎን አዘንብሏል። አንድ ወንድ ደግሞ ከጎኗ ወድቋል።

ይህ ተንቀሳቃሽ ምሥል በኳታሩ አል አረቢ ቴሌቪዥን በታኅሣሥ መጨረሻ 2023 ተሠራጭቷል። ጨቅላዋ ሕፃን እና ሰውዬው በእስራኤል አልሞ ተኳሾች ጥይት መመታታቸውን ጣቢያው ዘግቧል።

ምን እንደተፈጠረ አሊያም ሟቾቹ ማን እንደሆኑ ዝርዝር አልሰጠም። የቢቢሲ ምርመራ ተጎጂዎቹ መሐመድ አልማጅዳላዊ እና የሁለት ዓመት ልጁ ላያን መሆናቸውን ለማወቅ ችሏል። ሁሉቱም በዚያች ቀን መንገድ ላይ ሕይወታቸው አልፏል።

ቢቢሲ ግጭቱ ከጀመረበት መስከረም 2015 ዓ.ም. እስከ ሐምሌ 2017 ዓ.ም. ድረስ በጋዛ የተገደሉ ላያን እና ከ160 በሚበልጡ ሕፃናት አሟሟት ዙሪያ መረጃ ሰብስቧል።

እስራኤል የውጭ ጋዜጠኞች በነጻነት ወደ ጋዛ እንዲገቡ አለመፍቀዷ፣ በጋዛ የደረሰው ውድመት እና መፈናቀል ዝርዝር መረጃዎችን ለመሰብሰብ አዳጋች አድርጎታል።

ላያን እና አባቷን በሚመለከት በማኅበራዊ የትስስር ገፆች የሚለጠፉ ጽሑፎች እና አስተያየቶች የተንቀሳቃሽ ምሥሉ የተቀረፀበትን ስፍራ ለማወቅ እና ተጎጂዎችን ለመለየት እንዲሁም የሞት ሰርተፍኬታቸውን ለማግኘት አስችሎናል።

ለበርካታ ወራት በሕይወት የተረፉ ዘመዶቻቸውን ከፈለግን በኋላ በመጨረሻም የካቲት 2025 በታወጀው የተኩስ አቁም ስምምነት ወቅት ሰዎች ለመንቀሳቀስ አመቺ ሁኔታ ሲፈጠርላቸው የላያን እናት ሶራያ፣ ታዳጊ ወንድም እና እህቷን አቡድ እና ሻህድን ማግኘት ችለናል።

በዚያች ቀን ምን እንደተፈጠረ እማኝነታቸውን ነግረውናል።

በአል አረቢያ ቴሌቪዥን የተላለፈው ተንቀሳቃሽ ምሥል ሞሐመድ እና ላያን መንገድ ላይ ወድቀው ያሳያል

የፎቶው ባለመብት, Al Araby TV

የምስሉ መግለጫ, በአል አረቢያ ቴሌቪዥን የተላለፈው ተንቀሳቃሽ ምሥል ሞሐመድ እና ላያን መንገድ ላይ ወድቀው ያሳያል

በአውሮፓውያኑ ኅዳር 8/2023 ቀትር ላይ ከአየር ጥቃት ራሳቸውን ለመከላከል ተጠልለውበት ከነበረበት አል ሻቲ ካምፕ ውስጥ ከሚገኘው ትምህርት ቤት የእስራኤል ሠራዊት ለቀው እንዲወጡ የሰጠውን ትዕዛዝ ተከትለው ለቅቀው መውጣታቸውን ቤተሰቡ ይናገራል።

ከትምህርት ቤቱ ወደ ደቡብ ከሄዱ በኋላ በስተምሥራቅ ወደ ሐሚስ መንገድ ሲያቀኑ አንድ የአካባቢው ነዋሪ መንገዱ ሰላም እንደሆነ እንደነገራቸው ይገልፃሉ።

በግድያው ወቅት 12 ዓመቷ የነበረችው ሻህድ በአካባቢው አቅራቢያ ውጊያ እንዳልነበር ለቢቢሲ ተናግራለች።

"አብረን እየተጓዝን ነበር። ከአባታችን ቀድመን እየተራመድን ነበር። እሱ ከላያን ጋር እየዘመረ እና እየተጫወተ ነበር" ትላለች።

ወደ ግራ የሚታጠፍ መንገድ ሲያገኙ ሻህድ ታንክ በማየታቸው መሮጥ መጀመራቸውን ተናግራለች።

ከኋላ የነበረው አባታቸው ላያንን አቅፏት ስለነበረ በዝግታ እየተራመደ እንደነበረ እና "ወደ ኋላ ስንመለከት መሬት ላይ ወድቆ ነበር" ትላለች።

ሻህድ አሷ እና ወንድሟ አባታቸውን ለመርዳት ሲሮጠው ሲመለሱ በጥይት መመታቱን ማወቃቸውን ገልጻለች።

"እህቴን ለማንሳት እጄን ስዘረጋ፤ እኔም እጄን በጥይት ተመታሁ" ትላለች ሻህድ።

"ትታችሁኝ ሂዱ" ብሎ አባቷ እንደጮኽ ትናገራለች።

ሻህድ ከእናቷ እና ከወንድሟ ጋር አካባቢውን ለቀው ሄዱ። ከዚያ በኋላም ሞሐመድንም ሆነ ላያንን በድጋሚ አላገኟቸውም።

ቢቢሲ ከግድያው ሁለት ሰዓት አስቀድሞ የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ የሳተላይን ምሥል አግኝቷል። ምሥሉን ለማተም ፈቃድ ስላላገኘን እንደገና በራሳችን አዘጋጅተነዋል።

ካርታ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምሥሉ ከቤተሰቡ በስተሰሜን አቅጣጫ በ280 ሜትር ርቀት ላይ የእስራኤል መከላከያ ኃይል መኖሩን ያሳያል። በመንገዱ ላይ ሻህድ አየሁ እንዳለችው ታንክ ይታያል።

መቀመጫውን ለንደን ባደረገው ማኬንዚ ኢንተለጀንስ የወታደራዊ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት ስቱዋርት ሬይ ምሥሉን መርምረው ታንክ፣ ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎች፣ ወታደራዊ የቁፋሮ ማሽኖች እና ለመከላከያ የተከመሩ የአሸዋ ከለላዎችን ለይተዋል።

በስፍራው አቅራቢያ ረዣዥም ሕንፃዎች እንዳሉ በመጠቆም የእስራኤል ጦር መቀመጫ እና እግረኛ ወታደሮች ያሉበት እንደሚሆንም ይጠቁማሉ።

በአል አረቢያ ቴሌቪዥን ሞሐመድ እና ላያንን የተመለከቱ ሦስት ምሥሎችን አሠራጭቷል።

እነዚህን ተንቀሳቃሽ ምሥሎች የጦርነት ጉዳቶች ላይ ልምድ ላላቸው ሦስት የፎረንዚክ ምርመራ ባለሙያዎች አሳይተናል።

ሁሉም ባለሙያዎች ማስረጃዎቹ ሞሐመድ እና ላያን በጥይት ተመትተው እንደተገደሉ ያሳያሉ ብለዋል።

በደንዲ ዩኒቨርስቲ የቀድሞ የፓቶሎጂ ኃላፊ ፕሮፌሰር ዴሪክ ፓውንደር የአስከሬኖቹ አወዳደቅ ሁኔታ (ሞሐመድ ላያንን ይዞ) በፍንዳታ ግፊት ሳይሆን በድንገት እንደወደቁ ያሳያል ብለዋል።

አስከሬኑ ላይ በግልፅ የሚታይ ትልቅ ጉዳት አለመታየቱን በማንሳትም "ስለዚህ እያወራን ያለነው ከውጭ የሚታይ አነስተኛ ጉዳት ነው። እናም የጥይት ጉዳት ለዚህ ዋነኛ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

"ከወታደራዊ መሳሪያዎች የሚተኮሱ ጥይቶች በከፍተኛ ፍጥነት በመተኮስ አነስተኛ ቀዳዳ በመፍጠር ከፍተኛ ውስጣዊ ጉዳት ያደርሳሉ" ሲሉ አክለዋል።

እነዚህን ግኝቶች ለእስራኤል መከላከያ ኃይል (አይዲኤፍ) አቅርበናል። "የአይዲኤፍ ወታደሮች ውስብስብ በሆኑ የከተማ ከባቢዎች ውስጥ በሽብር ድርጅቶች ላይ ዘመቻ ያካሂዳል። እናም በውጊያ ወቅት ያልታሰበ ወይም የተሳሳተ ጉዳት ሊደርስ ይችላል" ብሏል።

ጨምሮም "ነገር ግን የአይዲኤፍ ኃይሎች ከሠራዊቱ እሴቶች እና ትዕዛዝ ውጪ እርምጃ ወስደዋል ተብሎ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሲኖር ክስተቱ ተገምግሞ አስፈላጊ በሆነ ጥብቅ ሂደት ይያዛል" ሲሉ ገልጿል።

የዚህን ጉዳይ ዝርዝር "ተመዝግቦ በሚመለከተው አካል እንዲመረምር ይደረጋል" ብሏል።

ሚራ (በስተግራ) ቢጫ ቲሸርት ለብሳ በእጆቿን ሳዒድ አንገት አቅፋ ፈገግ ብላለች። አባቷ ቡናማ ጸጉር እና አጭር ጢም አለው።

የፎቶው ባለመብት, Tanboura family

የምስሉ መግለጫ, ሳዒድ (በስተቀኝ) ልጁ ሚራ ከእስራኤል የፍተሻ ጣቢያ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ መንገድ ላይ መገደሏን ተናግሯል

ቢቢሲ በመረመረው ሌላ ግድያ ደግሞ የስድስት ዓመቷ ሚራ ታንቡራ በጀርባዋ በጥይት መመታቷን አባቷ ሳዒድ ተናሯል። ግድያው በአውሮፓውያኑ ኅዳር 18/2023 በደቡብ ምዕራብ ፋዛ ከተማ ሳላህ አል-ዲን መንገድ በእስራኤል ጦር የፍተሻ ኬላ ላይ መፈጸሙን ገልጿል።

የሳላህ አል-ዲን መንገድ የጋዛን ሰሜኑን ከደቡብ ጋር የሚያገናኝ ዋና መንገድ ሲሆን፣ የእስራኤል ሠራዊት ሰላማዊ ሰዎች ከሰሜኑ ክፍል ለቀው እንዲወጡ ለማድረግ የለየው መስመር ነው።

በዚያች ቀን ጠዋት ላይ ሳዒድ ቤተሰቡ ከሰሜን ጋዛ ከወጣ በኋላ በእስራኤል ሠራዊት ኬላ ተመርምረው እንዳለፉ ይናገራል።

የፍተሻ ጣቢያውን አልፈው አንድ ኪሎ ሜትር ገደማ አካባቢ ላይ ሚራ እና የተቀረው ቤተሰቡ ፈንጠር ብለው ሳለ እሱ ከአንድ የአውቶብስ አሽከርካሪ ጋር እየተነጋገረ እንደነበረ ያስታውሳል።

"ዞር ስል ሚራ ልቧ ላይ በአነጣጥሮ ተኳሽ ተመትታለች። አነጣጥሮ ተኳስ ስለመሆኑ እርግጠና ነኝ። ምክንያቱም አንድ ጥይት ብቻ ነው ልቧን የመታት" ይላል።

"በአፍ እና በአፍንጫዎ ደም ፈሰሳት።"

ሳዒድ ልጁን ዴር አል ባላህ ወደሚገኘው አል-አውዳ ሆስፒታል በፍጥነት እንደወሰዳት እና መሞቷንም የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ነግረውታል።

ቢቢሲ የሚራ ፊት የሚታይበት አስከሬኗ በነጭ ጨርቅ ተጠቅልሎ ደረቷ አካባቢ ደም የሚታይበት ምሥል ተመልክቷል።

ከአንድ ቀን ቀደም ብሎ የተነሳ የሳተላይት ምሥል የእስራኤል ሠራዊት የፍተሻ ኬላ አሳይቷል። ከግድያው ጥቂት ቀናት አስቀድሞ አይዲኤፍ ባሠራጨው ተንቀሳቃሽ ምሥል ጦሩ በአካባቢው ላይ መኖሩን አረጋግጧል።

የቢቢሲ አረብኛ የካሜራ ባለሙያ ጂሃድ ኤል ማሽራዊ ሳዒድ ቤተሰብ ሁለት ቀናት አስቀድሞ ከቤተሰቡ ጋር በዚህ የፍተሻ ኬላ በኩል አልፏል።

ከኬላው ቀጥሎ "ወታደሮች በአሸዋ ክምር እና በፈራረሱ ሕንፃዎች ላይ ተቀምጠው አሊያም በደረታቸው ተኝተው መሳሪያቸውን ለመተኮስ ደቅነው ይታዩ ነበር" ብሏል።

ካርታ

ከፍተሻ ኬላው በአንድ ወይም ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት በመንገዱ ምሥራቃዊ ክፍል በወደሙ ሕንፃዎች ውስጥ እና በአሸዋ ክምሮች አልሞ ተኳሾች እና ሌሎች ወታደሮች መመልከቱን ይገልፃል።

ሳዒድ የተኩስ አቁም ስምምነቱን ተከትሎ በቢቢሲ ጥያቄ አካባቢውን ተመልሶ ተመልክቷል። ሚራ ስትገደል በመንገዱ በስተ ምሥራቅ የእስራኤል ወታደሮች ማየቱን እና "እኛ ላይ ሲያነጣጥሩ ነበር" ብሏል።

በልጁ ላይ የተተኮሰበትን አቅጣጫ ነው ብሎ የሚያምነው ቦታም ጠቁሟል። በዚያ አቅጣጫም የአሸዋ መከለያ እንዳለ በሳተላይት ምሥል ላይ ይታያል።

ሚራ በጥይት በተመታችበት ወቅት ከሐማስ ጋር በፍተሻ ጣቢያው አካባቢ ግጭት ስለመኖሩ የሚያሳይ ምንም ሪፖርት አላገኘንም። ይህም በተኩስ ልውውጡ መካከል በተባራሪ ጥይት ተመትታ ነው የሚለውን ዕድል ዝቅ ያደርገዋል።

አባቷ "የእስራኤል ጦር በሳላህ አል-ዲን መንገድ አስተማማኝ ኮሪደር መከፈቱን ነግሮን ነበር። ወደ ሳለህ አል-ዲን መንገድ እንድንሄድ ካደረጋችሁን በኋላ ንፁኋን ሕፃን ገደላችኋት" ይላል።

በዚህ ጉዳይ የእስራኤል ጦር የቀረበበትን አቤቱታ ስናቀርብ "የጉዳት ውንጀላ በራሱ የሕግ ጥሰትን አያመለክትም" የሚል ምልሽ ሰጥቷል።

እንደ ላያን ግድያ ሁሉ የዚህ መዝገብ ዝርዝር "በሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ይመረመራል" ብሏል።

ከጦርነቱ መጀመር አንስቶ ሐኪሞች በጋዛ በጥይት ስለሚመቱ ሕፃናት ሲያስጠነቅቁ ቆይተዋል። ለዚህ ዘገባ ቢቢሲ 30 ሐኪሞች እና ነርሶችን ያናገረ እና በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥሎችን እና ተንቀሳቃሽ ምሥሎችን እንዲሁም በርካታ የሕክምና ማስረጃዎችን ተመልክቷል።

"ሕጻናትን ጨምሮ በርካታ ቁጥር ያላቸው በጥይት ጭንቅላታቸውን ወይም ደረታቸውን የተመቱ ሰዎችን ተመልክተናል" ይላሉ ጋዛ ውስጥ በነሐሴ 2024 ለአንድ ወር ያህል ሕክም የሰጡት በዩናይትድ ኪንግደም መቀመጫቸውን ያደረጉት ጡረተኛው የቀዶ ሕክምና ሐኪም ፕሮፌሰር ኒዛም ማሞዴ።

ከሕክምና የተገኙ ሦስት ምስሎች የልጆችን ጭንቅላት ውስጥ ጥይት መግባቱን ይሳያሉ

የፎቶው ባለመብት, Dr Mimi Syed/ Dr Razan Al-Nahhas

የምስሉ መግለጫ, የሕክምና ምስሎች እድሜያቸው (ከግራ ወደ ቀኝ) በ12 ዓመት፣ ስምንት ወር እና አራት አመት እድሜ ያላቸው ሕፃናት አንጎላቸው ውስጥ ጥይት ተቀምጦ እንደነበር ያሳያል።

በአብዛኞቹ የጭንቅላት ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በኒሮሰርጅን ባለሙያዎች መታየታቸውን ቢናገሩም፤ አንድ የራጅ ምሥል "በሦስት ዓመት ሕፃን አንጎል ውስጥ ጥይት" ማሳየቱን ይናገራሉ።

በጥይት ተመትተው ያከሟቸው የቆሰሉ ሕፃናት ቁጥርን እንደዘነጉ በመጥቀስ ቁጥራቸው ምናልባትም ከ20 በላይ ይሆናል ብለዋል።

ከዓይን እማኞች እና ከተጎጂ ቤተሰቦች የተሰጡ እና የተረጋገጡ ምስክርነቶችንም ሰብስበናል። አንዳንዶቹም ከሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና ከተረጋገጡ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች የተገኙ ናቸው።

ከዚህ መረጃ የጉዳቱን ሰነዶች የተመለከትናቸውን ጨምሮ 168 ሕፃናት በጥይት ተመትተው መገደላቸውን ተገንዝበናል።

95 የጥቃት ሁነቶች ሕፃናት በጥይት ጭንቅላታቸውን አሊያም ደረታቸውን መመታታቸውን፤ ከእነዚህም ውስጥ 67ቱ ከ12 ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው።

ከ59 ጭንቅላታቸውን ወይም ደረታቸውን በጥይት ስለተመቱ ክስተቶች ከዓይን እማኞች ምን እንደተፈጠረ ምስክርነት በቀጥታ አሊያም በሐኪሞች እና በሰብአዊ መብት ተመራማሪዎች በኩል አግኝተናል።

ከእነዚህ ክስተቶች ውስጥ 57ቱ የእስራኤል ጦር ሕፃናትን ተኩሶ መትቷል ተብሏል።

በሁለት ሌሎች ክስተቶች ህፃናቱ በፍልስጤማውያን መመታታቸውን፣ አንደኛው በደስታ በተተከሰ ጥይት፣ ሌላኛው ደግሞ በወሮበሎች ግጭት ተመትቷል።

በተቀሩት 36 ሁነቶች ምን እንደተፈጠረ መረጃ አላገኘንም። በጋዛ ሪፖርት ለማድረግ ፈቃድ አለማግኘት ስለእያንዳንዱ ሕፃናት ዝርዝር መረጃ ለማግኘት በጣም ከባድ አድርጎታል።

የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ ማቲው ሞሪስ "ዓለም እንደዚህ ዓይነት ጦርነትን በቀላሉ መቀበል የለበትም፤ በሕፃናት ላይ እንዲህ ዓይነት ተፅዕኖን መቀበል የለበትም" ይላሉ።

"ልጆች በቤታቸው ተገድለዋል፤ ተጎድተዋል። በድንኳን ውስጥም ሆነው በመንገድ ላይ እየተራመዱ ጉዳት ደርሶባቸዋል።"

በጋዛ መንገድ ላይ የሚሄዱ ብዙ ሰዎች። ከፊት ለፊት ሁለት ሰዎች ትናንሽ ልጆችን ይዘዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በ2023 መገባደጃ ላይ ጋዛዊያን በእስራኤል ከታዘዙ በኋላ ብዙዎች ሰሜናዊ ጋዛን ለቀው ወጥተዋል

የግድያው ምክንያት ላይ ማረጋገጫ ባይኖረንም እንኳ የሚራ እና ላያን ግድያ በጋዛ የእስራኤል ጦር እንዴት ተልዕኮውን እያካሄደ መሆኑ ላይ ጥያቄ ያስነሳል።

በዚህ ሳምንት የእስራኤል የሰብዓዊ መብቶች ቡድን ቤትሳሌም በጋዛ የእስራኤል ወታደሮች ምንም ዓይነት የጦርነት ደንብን እንደማይከተሉ አስታውቋል።

ለዚህ ዘገባ 'ኬ' እያልን የምንጠራው ወታደር በ2024 መጀመሪያ ላይ በጋዛ የነበረ የተጠባባቂ ጦር አባል ነው።

'ኬ' አራት የተለያዩ ሁነቶችን በመዘርዘር የነበረበት ቡድኑ ሁለት ታዳጊ ልጆችን ጨምሮ ያልታጠቁ ሰዎች መግደሉን ተናግሯል።

እንደሚለው ከደቡብ ወደ ሰሜን በሚወስደው መንገድ "በአጠቃላይ መመሪያው መሠረት ቀጣናው ደኅንነቱ የተጠበቀ እና የማይተኮስበት ነው።"

"ለሰብዓዊ አገለግሎት ከተከፈተው መንገድ የሚወጣ ማንኛውም ሰው ካለ ለመግደል እንተኩሳለን" በማለት የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ገልጿል።

"አዛዣችን ሴት ወይንም ሕፃና ከሆነ አትተኩሱ፤ በቁጥጥር ስር አውሏቸው። ደደብ አትሁኑ [ይለናል]።"

ነገር ግን በጊዜ ሂደት በውጊያው ቡድናቸው ወታደሮች ስለተገደሉበት አስተሳሰቡ መቀየሩን እና "ሁሉንም አውድም፤ ሁሉንም የምታየውን ግደል" ወደ የሚል መቀየሩን ጠቅሷል።

የሚራን እና የላያንን ግድያ ማስረጃዎች እና የሌሎችን ሕፃናትን ግድያ የተመለከቱ ማስታወሻዎችን ያሳየናቸው የውጊያ እና የጦርነት ሕግ ባለሙያዎች፤ ግድያዎቹ የግዴለሽነት፣ የቸልተኝነት ወይም ሆን ተብሎ የተወሰደ እርምጃ ስለመሆናቸው ጥያቄ ያነሳሉ ብለዋል።

"በዓለም አቀፍ ሕግ ወታደሮች ከመተኮሳቸው በፊት የሚተኩሱት ሕጋዊ የጠላት ተዋጊ እንጂ ሲቪል አለመሆኑን የማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው" ብለዋል።

በአሜሪካ ልዩ ተልዕኮ ቡድን ውስጥ ያገለገሉት እና በሰላማዊ ሰዎች ጥበቃ ላይ የአሜሪካንን መከላከያ መሥሪያ ቤት አማካሪ የነበሩት ወታደራዊ ተንታኙ ዌስ ብሪያንት "ብዙ ልጆች በጥይት ሲመቱ እና በተለይም ጭንቅላታቸው ላይ ሲሆን ከባድ ችግር እንዳለ ይነግረናል" ይላሉ።

በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ጃኒና ዲል በዓለም አቀፍ ሕግ ኢላማ የማድረግ ውሳኔዎችን ስንመለከት "ቁርጥ አድርጎ መናገር ይከብዳል፤ መጀመሪያ ደረጃ ሕጋዊ መደምደሚያ ለመድረስ ብዙውን ጊዜ በጣም ከባድ ነው" ብለዋል።

"በዚህ አጋጣሚ ግን ያሉት ማስረጃዎች በቀጥታ ወደ ከባድ የሕግ ጥሰት፣ ምናልባትም የጦር ወንጀልንም ይጠቁማሉ። ይህ አልፎ አልፎ ነው የሚከሰተው" ሲሉም ያክላሉ።

የእስራኤል የመከላከያ ኃይል ስለ ወታደሮች ድርጊት ሲጠየቅ "በሲቪሎች እና በተለይም በሕፃናት ላይ ሆን ተብሎ የሚደርስ ጉዳት በጥብቅ የተከለከለ እና ከዓለም አቀፍ ሕግ እና ከሠራዊቱ አስገዳጅ መመሪያዎች የሚጻረር ነው" ብሏል።

ሐማስ "ሲቪሎችን በተለይም ሴቶችን እና ሕጻናትን እንደ ሰው ጋሻ ይጠቀማል" ሲልም ከስሷል።

ከእስራኤል ጦር ኃይል መመሪያዎች እና እሴቶች የማፈንገጥ ጥርጣሬን ሲፈጠር አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ክስተቶቹ በወታደራዊ ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍል እንደሚጣራም ገልጿል።

በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኝ የአንድ ወንድ ልጅ ጉዳት ደርሶበት ይታያል

የፎቶው ባለመብት, Dr Ammar Darwish

የምስሉ መግለጫ, አንገቱ ላይ በጥይት ተመትቶ በሕይወት የተረፈው ታዳጊ ምሥል ቢቢሲ ካሰባሰበው መረጃ አንዱ ነው

ከተመለከትናቸው 168 ክስተቶች ውስጥ ቢያንስ 90 ሕፃናት እንደሞቱ አውቀናል። ነገር ግን በጋዛ የሕክምና ሥርዓት ላይ በደረሰው ጉዳት ምክንያት ምን ያህሉ በደረሰባቸው ጉዳት እንደሞቱ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።

በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር መረጃ መሠረት ከጦርነቱ ጅማሬ አንስቶ ቢያንስ 50 ሺህ ሕፃናት ተገድለዋል አሊም ቆስለዋል።

መስከረም 26/2015 ዓ.ም. ሐማስ በፈጸመው የድንበር ተሻጋሪ ጥቃት 1,200 ሰዎች ሲገደሉ፤ 251 ሰዎች ደግሞ ታግተው ለተወሰዱበት ጥቃት ምላሽ እስራኤል በጋዛ ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍታ በማካሄድ ላይ ናት።

ለዚህ ምርመራ ያነጋገርናቸው ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ፍትሕ እናገኛለን የሚል ተስፋ እንደሌላቸው ይናገራሉ። አንዳንዶችም የተገደሉባቸውን ሰዎች አስከሬን መቅበር እንኳን አልቻሉም።

የላያን እና የሞሐመድ አስከሬን በሐሚድ ጎዳና ላይ ለቀናት ወድቆ ቆይቷል ነበር። ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለአጭር ጊዜ በቆየው የተኩስ አቁም ጊዜ አስከሬናቸው በጎረቤቶቻቸው እንዲቀበር ተደርጓል።

ከግድያው አንድ ዓመት በኋላ ቢቢሲ እስኪያናግራቸው ድረስ ቤተሰቡ የላያን እና ሞጘመድ ሞትን የሚያሳየው ምሥል ስለመኖሩ አያውቁም ነበር።